የግንቦት 7 ሳምንታዊ ርእስ አንቀጽ
በደረሰባቸው በደል የተቆጡ በአረብ አገራት የሚገኙ እህቶቻችን በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ ምሬታቸውና ቁጭታቸውን እየገለጹ ነው። በቅርቡ በአባይ ግድብ ሰበብ የእነዚህ ምስኪን ኢትዮጵያዊያንን የድካም ውጤት ለመዝረፍ ወደ አረብ ኤምሬት ያመራው የዘረኛው መለስ ዜናዊ አገዛዝ ልዑካን ቡድን ያልጠበቀው የቁጣ ናዳ ወርዶበታል።
የአንድ ሥርዓት ምንነት በገሃድ ከሚገልጹ ነገሮች አንዱ የሴቶች መብት አያያዝ ነው። ለሴቶች ከበሬታ የሌለው፤ ሴቶችን በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚያኖር ሥርዓት፣ ውጫዊ ገጽታው ምንም ይምሰል ምን ግፈኛ ሥርዓት ነው። ለሴቶች የማይመች ሥርዓት ለሰው ልጅ በሙሉ – ማለትም ለወንዶችም ጭምር – የማይመች ሥርዓት ነው።
በዲሞክራሲና በህግ የበላይነት ላይ እንደሚያደርገው ሁሉ የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ ስለሴቶች መብት እጅግ ብዙ ያወራል። በተግባር ግን አገዛዙ ኢትዮጵያዊያን ሴቶችን መጠቀሚያ እንጂ የራሱ አካል አድርጓ አይቷቸው አያውቅም። በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያዊያን ሴቶች ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ ህሊና ሊሸከመው ከሚችለው በላይ ሆኗል።
በሁሉም የእድሜ ደረጃ ውስጥ ያሉ ሴቶች በአረብ አገራት በቤት ሠራተኝነት ለማገልገል በረሃ ማቋረጥ፤ ባህርን በታንኳ መሻገር የጀመሩት በመለስ ዜናዊ የግፍ አገዛዝ ዘመን ነው። ለቤት ሠራተኝነት በህጋዊ መንገድ ወደ አረብ አገራት ለመሄድ ትዳርን መበተን፤ የራስንና የዘመድን ጥሪት አሟጦ ከአስር ሺህዎች ብር በላይ መክፈል የተጀመረው በመለስ ዜናዊ የግፍ አገዛዝ ዘመን ነው። ወደ ምዕራቡ አገራት በትዳር ስም ለሚወስዳቸው ሰው በመቶ ሺህ የሚገመት ብር መክፈል የተጀመረው በመለስ ዜናዊ የአገዛዝ ዘመን ነው።
በውጭ አገራትም በአገር ውስጥም የእህቶቻችን ለቅሶ በርክቷል። ከፎቅ ተገፍትረው የሚወረወሩ፤ በፈላ ውሃ የሚቀቀሉ፤ አሲድ የሚረጭባቸው፤ የአሳዳሪዎቻቸው ፍላጎት ማርኪያ የሆኑ እህቶቻችን ሰቆቃ እንቅልፍ ይነሳናል። በዚህ ሁኔታ ያሉ እህቶቻችን የወያኔ ኩባንያዎች ሃብት ማጋበሻ መሆናቸው ያንገበግበናል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ክብር መደፈር የአገራችን እና የሁላችንም ክብር መደፈር ዓይነተኛ መገለጫ ነው።
የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ሀገራቸውን ሲዖል አድርጎ፣ በየባዕድ ሃገሩ በአስከፊ ሁኔታ ለመኖር እንዲገደዱ ከአደረገ በኋላ፣ በራሱ ኩባንያዎች በቪዛ፣ በተለያዩ ሰነዶች እና በደላላነት በየወሩ በብዙ ሚሊዮን የሚገመት ሃብት የሚያጋብሰው አንሶት፣ አይኑን በጨው አጥቦ በአባይ ግድብ ሰበብ ገንዘብ ሊያፍስ በሄደበት ነው የእህቶቻችን ቁጣ የገነፈለው።
በሴቶች ላይ የሚደርሰው ግፍ በዝቶ ገደቡን ሲጥስ የሚያስነሳው ማዕበል ማንም አያቆመውም። የሰሜን አፍሪቃና የመካከለኛው ምሥራቅ አብዮቶችን በአንክሮ የተከታተለ ማንኛውም ሰው ከሚገረምባቸው ነገሮች አንዱ ሴቶች ያሳዩት ቆራጥነትና እልህ ነው።
በቱኒዚያ የወጣቶች እንቅስቃሴ ውስጥ ወጣት ሴቶች ከመጀመሪያው ጀምሮ የአመራር ቦታ በመያዝ ተሳትፈዋል። በግብጽም የወጣት ሴቶች እልህ ከወንዶቹ በልጦ ታይቷል። ዜጎቿ በኑሮ ደረጃ፣ በባህልም በትምህርትም ከሌሎች ባነሰ ደረጃ ላይ ይገኛሉ በሚባለው የመን ውስጥም ቢሆን የሴቶች ተሳትፎ እጅግ አስገራሚ ነው። በእነዚህ አገራት በተደረጉ ሕዝባዊ ሰልፎች የበርካታ ህፃናትና አረጋዊያን መገኘት በአብዛኛው የሴቶች የተሳካ የቅስቀሳ ውጤት ነው።
የሴቶች ቆርጦ መነሳት በርካታ ቁጥር ያለው ሰው ከማሰለፍ ባሻገር ሌሎችም ተጨማሪ እሴቶች አሉት።
ከዚህ አንፃር ስናየው ሰሞኑን በአረብ ኤምሬት ውስጥ የመለስ ዜናዊ አሽከሮች በጠሩት ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ያሳዩት ቁጭትና እልህ ተስፋ ሰጭ ክንውን ነው።
በዚህ ስብሰባ ውስጥ አንዲት ወጣት “የኢትዮጵያ ባንዲራ የታለ?” ስትል ጠይቃለች። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የአገራችንና የማንነታችን ክብር መገለጫ ነው። ወጣቷ በአለችበት አገር ውስጥ ኢትዮጵያዊያን ክብር ማጣታቸው፤ ኢትዮጵያዊያን ሲሞቱ እንኳን እንደሃይማኖታቸው በክብር የመቀበር ወግ የሌላቸው መሆኑን ከሰንደቅ ዓላማ ክብር መዋረድ ጋር ማመሳሰሏ ልብ የሚነካ ንጽጽር ነው። “የመጨረሻ መሮኛል፣ መሮኛል፣ መሮኛል!!!” በሚሉ ኃይለ ቃላት ንግግሯን መጨረሷ ደግሞ ተስፋ ሰጭ ነው።
እህቶቻችን ከመረራቸው የድላችን ጊዜ ቀርቧል ማለት ነው።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ “በሴቶች ላይ የሚደርሰው ግፍ በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚደርስ ግፍ አካል ነው” ብሎ አድበስብሶ አያልፍም። በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት የሰብዓዊ መብቶች መረገጥ ማነኛው ማሳያ ነው። ይህን ጥቃት መታገል የሴቶች ወይም የወንዶች ኃላፊነት ሳይሆን የሁላችንም ኃላፊነት ነው።
በተጨማሪም ሴቶችና ወንዶች በጋራ ካልታገልን በስተቀር ትግላችንን ፈቀቅ ማድረግ እንደማንችል ግንቦት 7 ያምናል። ስለሆነም “እህቶችና እናቶች በትግላችን በንቃት ተሳተፉ፤ አብረን ታግለን ነፃነታችንን እናረጋግጥ፤ ሁላችን እንደ ዱባይዋ እህታችን ‘የመጨረሻ መሮኛል፣ መሮኛል፣ መሮኛል!!!’ ብለን ቆርጠን እንነሳ” ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!