በምእራብ ጎጃም ሁለት የወያኔ ሹሞች ሲገደሉ ሁለት ፖሊሶችና አንድ ሌላ ጄሌ መቁሰላቸው ተዘገበ

በአማራ ክልል ሥር በሚገኘው የምዕራብ ጎጃም ዞን በይልማና ዴንሳ ወረዳ በአዴት ከተማ በተነሳ የህዝብ ተቃውሞ ሁለት የወያኔ ሹሞች ሲገደሉ ሌሎች ሁለት ፖሊሶች እና ሌላ ጄሌ ባለስልጣን ከፉኛ መቁሰላቸውን የግንቦት 7 ዘጋቢ ከስፍራው በላከልን ዜና ገለጸ።

እንደዘጋቢያችን ሪፖርት ባለፈው ረቡዕ ጥር 2 ቀን ለወያኔ በጄሌነት አድረው ህዝባቸውንና አገራቸውን በመበደል ላይ የሚገኙት የወረዳው ባለስልጣናት የጨረቃ ቤቶችን ለማፍረስ በተንቀሳቀሱበት ጊዜ፣ ህዝቡ ቤታችንን አታፈርሱም በማለት አጥብቆ ተቃውሞ ነበር።

መለስ ዜናዊ የሚያወጣቸውን ፖሊሲዎች በሃይል ለመተግበር እንዲያስችለው በየክልሉ አሰልጥኖ ባሰማራቸው አነጣጥሮ ተኳሾች የተማመኑ የወረዳው የወያኔ ጄሌ ባለስልጣናት ግን፤ ለህዝቡ ተቃውሞ የተለመደውን ንቀት በማሳየት ለተቃውሞ የተሰበሰበውን ህዝብ በፖልስ ሃይል ለማባረር በመወሰናቸው ውዝግቡ እየተካረረ ሂዶ ድንጋይ እስከመወራወር እንደደረሰ ተዘግቦአል።

የህዝብ ቁጣ ገንፍሎ ድንጋይ መወራወር መጀመሩ ይበልጥ ያበሳጫቸው የወረዳው ባለስልጣናት አጃቢ ፖልሶች ወደ ህዝብ መተኮስ በመጀመራቸው ከተሰብሳቢው ህዝብ አንዱ በያዘው ዱላ የአንድ ፖልሲ ጠመንጃ በመቀማት የወረዳውን  ግብረሀይል ይመራ የነበረውን የወረዳው የኢንዱስትሪ ሀላፊ ይበሉ ደሴን ተኩሶ እንደገደለና አጠገቡ የነበረውን የከተማውን አፈ ጉባኤ እንድሪስን ክፉኛ አንዳቆሰለ ለማወቅ ተችሎአል።

የወያኔ አለቆቻቸው በከፈቱላቸው የሃብት ዘረፋና ሙስና ልባቸው ያበጠው የወረዳው ሹሞች የህዝቡን ተቃውሞ ከምንም ባለመቁጠር በገጠሙት ግብግብ ቤቱ እንዳይፈርስበት ለመከላከል በቆረጠው የአዴት ከተማ ነዋሪ ይህንን የመሰለ  ቅጣት መቅመሳቸው መላውን ያካባቢውን ህዝብ እንጀት እንዳራሰና ወሬውም ወዲያው በመላው ወረዳና አካባቢው እንደተሰራጨ የግንቦት 7 ዘጋቢ አረጋግጦአል።

ጀግናው የአዴት ከተማ ነዋሪ በገዛ አገሩ ከሰራው ቤት ሊያፈናቅሉት በተላኩት የወያኔ ጄሌዎች ላይ የተቀዳጀው ይህ ድል ለሌሎች ክልሎችና ከተማ ነዋሪዎች ታላቅ አርአያነት ሊኖረው የሚችል እንደሆነ የዘገበው ዘጋቢያችን ፤ ዱላ የያዘው የአዴት ነዋሪ በዱላው ዱላ ያልነበረው ደግሞ ከፊት ለፊቱ ባገኘው የድንጋይ ናዳ  በወያኔ ተላላኪዎች ላይ ባደረሰው ጉዳት ከተገደሉት 2 ሹሞች በተጨማሪ ሁለት ፖልሶችና አብረዋቸው በነበሩ ሌሎች የወረዳው የወያኔ ጄሌዎች ላይ ቀላልና ከባድ የመቁሰል አደጋ እንዳደረሰባቸው ገልጾአል።

የገዛ ወገኖቻቸውን በማፈንና በማሰቃዬት የመለስ ዜናዊን የሥልጣን እድሜ ለማራዘም በሆዳቸው ተገዝተው ወያኔን እያገለገሉ ያሉ ፖሶች በወሰዱት የአጸፋ እርምጃም በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ድርሷል ተብሎአል። አብዛኞቹ ቁስለኞች በሞጣ ሆስፒታል ተወስደው እየታከሙ ሲሆን፣ ጉዳት የደረሰባቸው የወያኔ ተላላኪዎች  እና ፖሊሶች ደግሞ ወደ ፈለገ ህይወት ሆስፒታል መወሰዳቸውን ተያይዞ የደረሰን ዜና ያመለክታል።

በአዴት ከተማ ነዋሪዎችና በወያኔ ተላላኪዎች መካከል የተነሳውን ግጭት ለመቆጣጠር ግጭቱ በተነሳ በሰዓታት ጊዜ ውስጥ የፌደራል ፖሊስ ተልኮ አካባቢውን የተቆጣጠረ እንደሚገኝና ይህ ዜና እስከተጠናከረበት የዛረው ቀን ድረስ ውጥረቱ እንዳልረገበ ታውቆአል።

አካባቢውን በመቆጣጠር ላይ ያለው የፌደራል ፖሊስ መሳሪያ  ቀምተው ባለሥልጣናቱን የገደሉትን ግለሰቦች በማደን ላይ ናቸው የሚለው ዘጋቢያችን ፖሊስ በርካታ ሰዎችን እንዳሰረም አረጋግጦአል። ከሟቾቹ አንዱ የሆነው ይበሉ ደሴ በቅርቡ ከጎንች ቆለላ ቀበሌ ወደ አዴት ከተማ ተዛውሮ የመጣ ሆድ አደር የወያኔ ጀሌ ነው ተብሎአል።

የአዴት ወረዳ ህዝብ በምርጫ 97 ወቅት ሙሉ በሙሉ ቅንጅትን የመረጠ እንደሆነ ይታወሳል።