በአወልያ ኮሌጅ ተማሪዎች የሚያደርጉትን አድማ እንደቀጠሉ ነው። በነቄምት ዩኒቨርሲት 2 ተማሪዎች መገደላቸው ተዘገበ

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥን ኢሳት እንደዘገበው ከሳምንት በፊት የተጀመረው የአወሊያ ኮሌጅ ተማሪዎች ተቃውሞ እየከረረ በመሄዱ የወያኔ  የጸጥታ ሀይሎች በተማሪዎች ላይ ስለሚወስዱት እርምጃ ግራ ተጋብተው የኮሌጁን ግቢ ዘግተው ተቀምጠዋል።

መንግሥት ተብዬው አገዛዝ ያሰማራቸው የኮሌጁ ባለሥልጣናት አለአግባብ የትምህርት ይዘቱን በመቀየራቸውና መምህራንን በማባረራቸው የተቆጡት የኮሌጁ ተማሪዎች ተቃውሞአቸውን ማሰማት ከጀመሩበት ያለፈው ማክሰኞ ጥር 1 ቀን ጀምረው ምግብ እንዳላገኙና  ግቢያቸውን ለመልቀቅም ፈቃደኞች እንደልሆኑ የገለጸው ኢሳት የአወልያ ኮሌጅ እና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በትናንትናው ዕለት ለተለያዩ የእስልምና ተከታዮች የስልክ ጥሪ በማድረግ  ለዝሁር ጸሎት  እንዲቀላቀሏቸው ጠይቀዋል ተብሎአል።

ኢሳት ተማሪዎቹን ለማግኘት በተደጋጋሚ ስልክ እንደደወለና የተደወለበት ስልኮች “ጥሪ አይቀበልም” የሚል መልስ ከማግኘት ውጭ ሊሳካለት እንዳልቻለ ገልጾአል።

ወያኔ የአገዛዝ እድሜውን ለማራዘም ዘጎችየ በባህልና በቋንቋ ከመለያየት አልፎ ለዘመናት አብሮ የኖረውን ሙሲልም ሃይማኖትን ከክርስቲያን ጋር ለማጋጨት እንደሚንቀሳቀስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አንዱን  ሙስሊም ከሌላው ለማጋጨት አክራሪ የሚል ታርጋ እየለጠፈ በአህባሽ እምነት አራማጆችና ዋህብይ ብሎ በሚጠራቸው ምዕመናን መካከል የጠብና የግጭት ግንብ እየገነባ መሆኑን ደጋግመን መዘገባችን ይታወሳል

ይህ በዚህ እንዳለ ሰሞኑን ለቀምት ከተማ በሚገኘው የወለጋ ዩኒቨርስቲ ግጭት መፈጠሩን ተከትሎ ሲራጂ እና ከማል የተባሉ ሁለት የሕግ ተማሪዎች መገደላቸውን ኢሳት ዘግቦአል።

ተማሪዎቹ የተገደሉት በፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት እስካሁን የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም፤ ውስጥ አዋቂዎች ”ተማሪዎቹ የሞቱት በምግብ መመረዝ ነው”ማለታቸውን ፍኖተ -ነፃነት የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል።

የሟች ተማሪዎቹ የቀብር ሥነ ሥርዓት ባለፈው ማክሰኞ ጥር 1 ቀን ተፈጽሟል። ኢሳት ሰለጉዳዩ የዩኒቨርሲቲውን ሀላፊዎች ለማነጋገር በተደጋጋሚ ሞክሮ ፤ሀላፊዎቹ ስልካቸውን ለማንሳት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት እንዳልተሳካለት ገልጾአል።

አንድ ስሙ እንዲገለጽ ያልፈለገው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባል፦ የሁለቱ ተማሪዎች መሞት ከምግብ መመረዝ ጋር የተያያዘ ነው በማለት ሁኔታውን ለማስተባበል እንደሞከሩ ገልጾ ተማሪዎቹ የሞቱት በምግብ መመረዝም ይሁን በግቢው ውስጥ ተነስቶ በነበረው ግጭት፤ አገዛዙን ከተጠያቂነት እንደማያድነው የህግ ባለሙያዎች አስተያዬታቸውን መስጠታቸውን ዘግቦአል።

ሰሞኑን በወለጋ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎችና በፌዴራል ፖሊሶች መካከል በተፈጠረ ግጭት የመማር ማስተማሩ ሂደት እንደተቋረጠ ኢሳት መዘገቡንም አክሎ ገልጾአል።