በዘረኛው መለስ ዜናዊ ትዕዛዝ በሽብርተንነት የ11 አመት እስር የተፈረደባቸው የስዊድን ጋዜጠኞች ጉዳይ አለም አቀፍ ትክረት መሳቡን ቀጥሎአል

ሥልጣንን በሃይል የሙጥኝ ብለው የአገራቸውን ሃብትና ንብረት ሲቦጠቡጡ በኖሩት የሰሜን አፍርካና የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች አምባገነን መሪዎች ላይ የደረሰው ህዝባዊ ቁጣ ያስደነበረው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ፤ የመረጃ ፍሰትን ለመገደብ በሁለቱ የስዊድን ጋዜጠኞች ላይ በደመ ነፍስ የወሰደ የድንጋጤ እርምጃ አገዛዙን በመላው አለም ይበልጥ እያጋለጠው እንደሚገኝ ጉዳዩን የተከታተለው የዝግጅት ክፍል ባልደረባችን ገለጸ።

በስዊድን አገር በሚታተሙ ታዋቂ ጋዜጦች፤ ሬዲዮኖችና ቴለቪዥኖች ላይ  በተከታታይ እየወጡ ያሉ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፤ በወያኔ እስር ቤት ታጉረው ያሉት ሁለቱ የስዊድን ጋዜጦኞች በኢትዮጵያ ውስጥ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ነጻነትና መረጃን የማግኘት መብቶች ያሉበትን አስከፊ ገጽታ አመላካች ናቸው ተብለዋል።

የም ዕራባዊያን ጋዜጦችና ፖለቲከኞች ዘረኛውና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ሥልጣን ላይ በተፈናጠጠበት የመጀመሪያዎቹ አመታት “አፍሪካን ለመለወጥ ብሩህ አዕምሮና ተስፋ ካላቸው ጥቂት መንግሥታት ተርታ የሚመደብ ነው” በማለት ሲያሞካሹት እንደነበር እየገለጹ ያሉት የስዊድን ጋዜጠኞች ፤ የመለስ ዜናዊ እውነተኛ ባህሪ የሆነው አምባገነንነትና ጨቋኝነት ከምርጫ 97 ጀምሮ እራሱን እየገለጸ መሆኑን በዜጎቹ ላይ እያደረሰ ያለውን አፈና፤ እሥራትና ግዲያዎችን በማስረጃ በማጣቀስ የሰላ ሂስና ትችት እያቀረቡበት ነው።

ህወሃት ያካሄድ በነበረው የጸረ ደርግ ትጥቅ ትግል ሌሎችን እያጋፈጠ ከግንባር ይሸሽ እንደነበር የቀድሞ የትግል ጓዶቹ የሰጡትን ምስክርነት እያጣቀሱ መለስ ዜናዊን ማብጠልጠል የጀመሩት የስዊድንና የሌሎች ስካንዲነቪያን ጋዜጠኞች፤ ዘጎቹን አፍኖ ለመግዛት የሚጠቀምበትን ር ህራሄ የሌለው የጭካኔ እርምጃውን በሁለቱ የአውሮፓ ዜጎቻቸው  ላይ ወስዶአል በማለት ይከሳሉ።

ይህ በዚህ እንዳለ እኛ መታሰር አለም  በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰትና የፕሬስ ነጻነት አፈና ለማወቅ ችሎአል ሲሉ በእስር ላይ የሚገኙት ሁለቱ የስዊድን ጋዜጠኞች መናገራቸውን ሲ ኤን ኤን ዘግቦአል።

ሲኤን ኤን የማርቲን ሺቢየ እናት የሆኑትን ካሪን ሽብየን አነጋግሮ እንደዘገበው ማርቲን ሽብየና ጆን ፔርሰን የአለም ህዝብ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰትና የፕሬስ አፈና ለመረዳት በመቻሉ፣ ተልኮአቸው መና እንዳልቀረ ይረዳሉ ብሎአል።

“ጋዜጠኞቹ ንጹሀን ናቸው፣ ምንም ወንጀል እንዳልሰሩ ያምናሉ” ያሉት ካሪን፣ እስረኞቹ በኢትዮጵያ የፍርድ ሄደት ተስፋ የቆረጡ በመሆኑ ይግባኝ ላለማለት ወስናዋል በማለት ለሲ ኤን ኤን ተናግረዋል።

ጋዜጠኞችን ለመፍታት ያለው ብቸኛ አማራጭ ይቅርታ መጠየቅ ነው የሚሉት የስዊድን ባለስልጣናት፣ ይህ ማለት ግን ጋዜጠኞች ጥፋተኛ ናቸው ማለት አለመሆኑን ገልጠዋል።

ጋዜጠኞች ጥፋተኞች ነን ብለው ካላመኑ እንዴት ይቅርታ ሊጠይቁ እንደሚችሉ የተገለጠ ነገር ባይኖርም በበታቸኝነት ስሜት የሚሰቃዬው መለስ ዜናዊ ጠላቶቼ ናቸው በሚላቸው ላይ የበላይነቱን ለማሳየት ያለምንም በቂ ማስረጃ አስሮ ይቅርታ እንዲጠይቁ ማድረግ ልማዱ እንደሆነ የሚያውቁ ኢትዮጵያዊያን ስለ ሁኔታው አልተገረሙም።

ግንቦት 7 በሁለቱ ጋዜጠኞች ላይ የተሰጠውን የፍርድ ውሳኔ በመቃወም መግለጫ ባወጣበት ወቅት መለስ ዜናዊ ውሎ ሳያድር ከአለም አቀፍ ህብረተሰብ የሚደርስበትን ውግዘት ለመገላገል ይቅርታ አስጠይቆ እንደሚለቃቸው ተንብዮ እንደነበር አይዘነጋም።

መለስ ዜናዊና የወያኔ ሹመኞች ሁለቱን የሲዊድን ጋዜጠኞች በማሰር ያተረፉት ነገር ቢኖር ዜጎቻችንን በምን አይነት እስር ቤት ውስጥ አስረው እንደሚያሰቃዩ የአለም ህዝብ እንዲያውቅ ማድረግን ብቻ እንደሆነ የምናገረው ዘጋቢያችን ካሪን ሽበየ ለ ሲ ኤን ኤን በሰጡት ቃል 250 የሚደርሱ እስረኞች በአንድ ክፍል ውስጥ እንደሚታሰሩና መኝታ ፈልጎ ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ እስረኞች እንደሚሰቃዩ ከሰለባዎቹ ስዊድናዊያን ማረጋገጣቸውን መናገራቸው በቂ ማስረጃ ነው ብሎአል።