በሕዝብ ውስጥ ፍርሃትን ማንገስ የተለመደ የአምባገነኖች የመጨቆኛ መሣሪያ ነው። ፍርሃት ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ዜጎች ተዋርደው፣ ተረግጠውና ተቀጥቅጠው እንዲገዙ የማድረግ አቅም አለው። ፍርሃት ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ገዢዎች የሌላቸውን ጉልበት ያላቸው ያስመስላል።
ሆኖም ግን ፍርሃት ያቆመው ሥርዓት ለመናድ ጊዜ አይፈጅበትም። ፍርሃት ያቆመው የበርሊን ግንብ በሰዓታት ውስጥ ፈራርሷል። በፍርሃት ሕዝባቸውን አንቀጥቅጠው የገዙ የቱኒዚያው ቤን ዓሊ፣ የግብጹ ሙባረክ እና የሊቢያው ጋዳፊ ፍፃሜያቸው እንዴት እንደነበር ከጥቂት ወራት በፊት ያየነው ነው። ሕዝባቸውን በፍርሃት ቀፍድደው በመግዛት የታወቁት የየመኑ አብዳላ ሳልህና የሶሪያው ባሽር አልአሳድም ሊደረመሱ ተቃርበዋል።
ኢትዮጵያዊያንን በፍርሃት ቀፍድዶ እየተጫወተብን ያለ የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ ውድቀትም ተመሳሳይ እንደሚሆን ጥርጥር የለንም።
“ፍርሃትን እንዴት ነው የምናሸንፈው?” ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ወቅታዊና አስፈላጊ ነገር ነው።
በግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ እምነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍርሃትን ማሸነፊያ መንገዶች ከሌሎች መማር አያስፈልገውም። ፍርሃትን ማሸነፊያ መንገዶች ከራሳችንን ጀግኖች መማር እንችላለን ብሎ ግንቦት 7 ያምናል፤ የሚከተሉትንም ለአብነት ይጠቅሳል።
አብነት አንድ
የዳውሮው ወጣት መምህር የኔሰው ገብሬ ፍርሃትን እንዴት ሊያሸንፍ ቻለ?
መምህር የኔሰው ገብሬ ከሥራ ተባሯል፤ ታስሯል፤ ተንገላቷል። በደል አንገሽግሾታል። ኅዳር 1 ቀን 2004 ዓ.ም. በእርሱ ላይ እንደደረሰው ሁሉ ያለአግባብ የታሰሩ ወዳጆቹ ወደ ሚቀርቡበት የወረዳው ፍርድ ቤት አመራ። ዳኛው የታዘዙትን ተጨማሪ ቀጠሮ የመስጠት ውሳኔ አስተላለፉ። የየኔሰው ፍርሃት እዚህ ጋ አበቃ። ከፍርድ ቤቱ እንደወጣ ወደ አካባቢው አስተዳደር ቢሮ ሄደ። ባለስልጣኖቹ ስብሰባ ላይ ናቸው። የአስተደደሩ ቢሮ በረንዳ ላይ
“በደል በዛ!!! ፍትህ በሌለበት አገር መኖር አልችም!!! በዚህ ሁኔታ መኖር ኑሮ አይባልም!!! ግፍና መከራ እያየሁ መኖር አልችልም!!!”
እያለ ቤንዚን በራሱ ላይ አርከፍክፎ እሳት ለኮሰ። ኅዳር 4 ቀን 2004 ዓ.ም. ኢትዮጵያም አንድ በፍትህ እጦት የተከፋና የተቆጣ ልጇን አጣች። ለእኛ ግን ትምህርት ሆነ። የየኔሰው ገብሬ ቁጣ በውስጡ የነበረው ፍርሃትን አሸነፈ።
አብነት ሁለት
አዴት በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን የምትገኝ ከተማ ናት። ጥር 2 ቀን 2004 ዓ. ም. የወረዳው የወያኔ ሹማምንት እንደልማዳቸው “ህገ ወጥ ግንባታ” በሚል ሰበብ የድሆችን ቤት ያፈርሳሉ። እናቶችና ህፃናት አለቀሱ። ነገር ግን የድሆች ዋይታ ለቤት አስፈራሾቹ ሹማምት ጆሮዎች የሚጥሙ ሙዚቃዎች ናቸውና ሥራቸውን አላሰናከላቸውም። የአዴት ከተማ ወጣቶች “መውደቂያ ሳትሰጧቸው የድሆችን ጎጆዎች አታፈርሱ” ሲሉ ተቃወሙ። ሹማምንቱ ግን በፓሊሶች ታጅበው በማንአለብኝነት ቤቶቹን ማስፈረስ ቀጠሉ።
ቤቶቻቸው እየፈረሰባቸው ያሉት ዜጎች እና የከተማው ወጣቶች ከመለማመጥ ወደ መሰዳደብ፤ ትንሽ ቆይቶም ወደ ድንጋይ መወርወር ተሸጋገሩ። ፓሊሶች ለድንጋይ ውርወራ የጥይት ምላሽ ሰጡ። የአንዳንዶቹ ወጣቶች ፍርሃት እዚህ ጋ አበቃ!!!
ከተበዳዮች ጥቂቶቹ የፖሊሶችን ጠመንጃ በዱላ ቀሙ። የድሆች ቤቶች አፍራሽ ግብረኃይልን ሲመሩ የነበሩትን ተኩሰው ገደሉ፤ ሌላኛውን ክፉኛ አቆሰሉ። የቆሰለውም የወያኔ ሹም ጥቂት ቆይቶ ሞተ። የአዴት ወጣቶች የፓሊሶቹን መሳሪያዎች ነጥቀው ተሰወሩ። የበደል መብዛት የአዴት ወጣቶች ፍርሃትን እንዲያሸንፉ አደረጋቸው።
በዳውሮ እና በአዴት የተፈጸሙት ነገሮች በርካታ የጋራ ባህሪያት አላቸው።
ይህ ነው ሕዝባዊ አመጽ ማለት። ይህ ነው ሁለገብ ትግል ማለት። ይህ ነው ግንቦት 7 እንዲመጣ የሚታገለው ኢትዮጵያዊ ጀግንነት።
ሁኔታዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው። ኢትዮጵያዊያን “የነፃ አውጪ” መምጣትን መጠበቅ እየተው ነው። ግለሰብን ነፃ የሚያወጣው ራሱ ግለሰቡ ነው። ሕዝብን ነፃ የሚያወጣው ራሱ ሕዝቡ ነው። ግለሰብም ሕዝብም ነፃ የሚወጣው በቅድሚያ ፍርሃትን ሲያሸንፍ ነው።
ስለሆነም ወያኔ በዘራብን ፍርሃት ላይ እናምጽ። በፍርሃታችን ላይ ባመጽንባት ቅጽበት ወያኔ የለም። ያለእኛ ፍርሃት ወያኔ የጠዋት ጤዛ ነው፤ አሊያም ጉም ነው። ያለ እኛ ፍርሃት ወያኔ ትቢያ ነው።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !!!