የግንቦት7 ጋዜጣ ቁጥር 28 ላይ ወጥቶ የነበረ ርዕሰ አንቀጽ
ስድስት ሚሊዮን ሕጻናት፣ ከአምስቱ ሕፃናት ኣንዳቸው አባት እናት የሌላቸው የሙታን ልጆች፣ የተቀሩት ሕጻናት ከሙታኑ ልጆች ልዩነት በሌለው የኑሮ መቃብር ከነወላጆቻቸው የሚኖሩባት ሃገር፣ ኢትዮጲያ። ኣስራ ኣራት ሚሊዮን፣ ሕዝብ ከስድስቱ ዜጋ አንዱ፣ በውጭ መንግስታት እርጥባን ስጋን ከነፍሱ አጣብቆ የሚያድርባት ሃገር፣ ኢትዮጲያ። ሶስት ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ፣ ከሃያ አምስቱ ዜጋ አንዱ ከአስከፊው የኤድስ በሽታ ጋር የሚኖርበት፤ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠር በሳንባ ነቀርሳ በወባ፣ በተስቦና ከአለማችን በጠፉ በሽታዎች የሚያልቅበት ሃገር፣ ኢትዮጵያ።
ወገኖቻችን ለአገራችን ሕልውና መከበርና ለነጻነታችን መጠበቅ በታሪካቸው የከፈሉትን መስዋዕትነት የሚመጥን ስልጣኔ አልተቀናጀን፤ ለአርነታቸው ያሳዩትን ቀናኢነት የሚያንጸባርቅ መብት አልተላበስንም በማለት “እምቢ ለጭሰኛነት፣ እምቢ ለገባርነት” ብለው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ብሩህ ዐምሮ የነበራቸው ወጣት ተማሪዎችና ምሁራን እንድ ቅጠል የረገፉበት፣ መስዋዕትነታቸው ከንቱ ሆኖ፣ በመሳፍንቱና በባላባቱ ምትክ ጥቂት ዘረኛ ደናቁርት ተተክተው ሃገሬውን በሙሉ ገባር ኣድርገው በሚኖሩበት ሃገር፤ ኢትዮጲያ! ለሺዎች ዓመታት ነጻነቱን በከፍተኛ መስዋዕትነት አስጠብቆ የኖረ ሕዝብ ለጥቂት ዘረኞች ባሪያ የሚኖርበት ሃገር፣ ኢትዮጲያ!ስልጣን ከማዕከሉ እጅ ወጥቶ ሕዝብ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት መንደርና ቀበሌ ድረስ ይውረድ፣ ሁሉም ቋንቋውን ባህሉን የሚጠቅምበት የሚያሳድግበት እኩልነቱ ይከበር ለሚል ፍትሃዊ ጥያቄ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ኣልቀው፣ ጥቂት ዘረኞች የሀገሪቱን የፖለቲካ ስልጣንና ምጣኔ ሃብት ተቆጣጥረው በታሪካችን አይተነው የማናውቀው በዘር ላይ የተመሰረተ አስከፊ ዘረፋና መጠቃቀም የሚያካሂዱበት ሃገር፣ ኢትዮጲያ!
ትውልድ እየተፈራረቀ ልጆቹን ያለ አሳዳጊ፣ ወላጆቹን ያለ ጡዋሪ፣ እየተወ፣ ያለስንቅና ያለበቂ ትጥቅ፣ በባዶ እጁና በባዶ ሆዱ በደሙ ዋጅቶ አጥንቱን ኣድቅቆ አብኩቶ ያስጠበቀውን ዳር ድንበር የሚንድ ፈሪ የባንዳ ውላጅ በጀግኖቹ ዙፋን ላይ የወጣበት ሃገር፣ ኢትዮጲያ! የራስዋን አስደፍራ የሌላውን ደፍራ የማታውቅ ሃገር፣ ከኣሜሪካና ከእንግሊዝ መንግስታት ጋር የነበራቸውን ወዳጅነት ሰበብ ሳያደርጉ፣ ዘረኛውን የደቡብ አፍሪካ የታገል የበረውን ኔልሰን ማንዴላን በሚስጥር የውጊያ ትምህርት ለመስጠት፣ በጥቂት የሮዴሺያ ነጮች ለሚረገጡት አፍሪካዊ ወገኖቻቸን፣ በቅኝ ግዛት ተጠፍረው ለሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአፍሪካ ሃገሮች የዲፕሎማሲና የትጥቅ ድጋፍ በማድረግ አኩሪ ታሪክ የነበራቸው መሪዎች ታሪካቸው ፍትሃዊ ሚዛን ኣጥቶ በተቀሩበት፣ ሕዝብን እየረገጡ ስልጣን ላይ ለመቆየት በሚል ስሌት ለኣሜሪካ እሽክርና አድረው የጎረቤት ሃገሮችን በመውረር በስማችን አሰቃቂ ወንጀል በጎረቤት ወንድሞቻችን ላይ የሚፈጽሙ፣ በሃገራችን ላይ በዙሪያችን የሚገኙ አገሮች ዓይናቸው እንዲቀላ የሚያደርግ በደል የሚሰሩ ከሃዲዎች ስልጣን የያዙበት ሃገር፣ ኢትዮጲያ!
“ሂዱ እናንተ ተከታዮቼ ወደ ኢትዮጲያ ኣቅኑ፣ በእዛ የሚገኘው ብጹእ የክርስቲያን ንጉስ ከክፉ ይጠብቃችሃል” በማለት ነብዩ መሐመድ ቤተሰቦቻቸውንና የመጀምሪያ የእስልምና ተከታዮቻቸውን ወደ ኢትዮጲያ በመላክ የባረክዋትን፣ ለረዥም ዘመን የክርስትናና የእስልምና ተከታዮች በሌሎች ቦታዎች ታይቶ በማይታወቅ መፋቀር በኖሩባት ሃገር ሕዝብ በሃይማኖት እንዲናከስ፣ ሞቃዲሾ ውስጥ ቅዱስ መስጊድ ውስጥ ገብቶ ህጻናትና አረጋውያንን የሚያርድ፣ በደቡብ ኢትዮጲያ በቤተክርስትያን መቅደስ ውስጥ ቀሳውስትንና ምእመናንን በቆንጨራ የሚያስጨፈጭፍ፣ ሕዝብን በዘር ለማናከስ ከሚሰራው እኩይ ተግባር በተጨማሪ በሃይማኖት እንዲባላ የሰይጣን እንጀራ ለመጋገር ሴራ ሲያቦካ የሚያድር ገዥ የተቆለለባት ሃገር፤ ኢትዮጲያ!
ገንዘብ ያለው ዜጋ ገንዘቡን የሚያሸሽባት፣ ዕውቀት ያለው ዜጋ እውቀቱን ይዞ ከኣገር የሚፈረጥጥባት፣ ሙያ ያለው አክብረው ለሚያሰሩት ሌሎች ገቶች ሙያን ለመሸጥ አገር ጥሎ የሚሮጥባት፣ ጉልበ፣ ኣቅሙ ቢኖረውም ዘዴውን ቢያውቅበትም ሁሉም ሃገሩን ጥቂት በዘረፋ ተንደላቀው ለሚኖሩና በያዙት ጠመንጃ ያሻቸውን ፈጽመው ለሚያድሩ ዘረኞች ጥሎ ለመጥፋትና በኣለም ላይ እንደ አሸዋ ለመበተን የተዘጋጀበት ሃገር፣ ኢትዮጲያ!
የመከራና የሰቆቃው ጥልቀት መዳበሻ ያጣ፣ የሲቃችን ጭላንጭሉ የማይታይበት ሃገር፣ ኢትዮጲያ! እረ እንዴት ነው ነገሩ ይህች የሚገርም የሚያኮራ እንደ እንቁ የሚያበራ ታሪክ የሚያስደንቅ መልክኣ-ምድር፣ የኣየር ጠባይና የተፈጥሮ ሃብት ያላት ሃገር፣ በማንኛውም መመዘኛ ከሲኦል ልዩነት የሌለው ሕይወት የአብዛኛው ሕዝብ እጣ መሆን የቻለው? እንዴት ነው ዛሬ ካለንበት፣ ከውርደትም ከአስከፊ ውርደት በተሞላ አሳፋሪ ሁኔታ ውስጥ መውደቅ የቻልነው? እውን ይህን የአገራችን መከራና ስቃይ፣ በየጊዜው ስልጣን ላይ በመጡ እኩይ መሪዎች ሙሉ በሙሉ አሳበን፣ ይህንን ሁሉ የሰሩት ያደረጉት እነሱ ብቻ ናቸው ብለን ተናግረን ህሊናችን በሰላም ማዋልና ማሳደር ይቻለናልን? እውን ገዥዎቻችን ሃገራችንና ሁላችንንም እንዲያዋርዱ ሳንፈቅድላቸው ብቻቸውን ተነስተው ይህን የውርደት፣ ሃገር የማጥፋት የክህደት፣ የዘረኛነትና የዘራፊነት መርሀ ግብር ማስፈጸም ይችላሉ?
ስለ ሰው ልጆች ነጻነት ብዙ በሚያስተምረው የፍልስፍና ትምህርት ዶክተር የሚል ማዕረግ የተሰጠው የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ራሱንና ተማሪዎቹን ለደንቆሮዎቹ የወያኔ ካድሬዎችና ሰላዮች በፍርሃት ኣስገዝቶ ለመኖር ሲቆርጥ ኣዋርዱኝ የሚል ፈቃድ ለኣዋራጆቹ መስጠቱ ኣይደለምን? የከፍተኛ ተማሪዎች ተቅዋማትስ? ባገኙት ዕድል የቀድሞ ተማሪዎች መብታቸውን ከማስከበር፣ ዩኒቨርስቲያቸውን የመማሪያና የማስተማሪያ ቦታ ለማድረግ የከፈሉትን መስዋዕትነት እያወቁ፣ ከእዛም በላይ እንደነሱ የእውቀት ብርሃን ለማግኘት ያልታደለውንና በሚከፍለው ግብር የሚያስተምራቸውን ድሃ ህዝብ መብት ለማስከበር ያደረጉትን የተጋድሎ ታሪክ እየሰሙ፣ ምንም ዓይነት ነጻነት በሌለበት፣ የትምህርት ደረጃው በወደቀ ዩኒቨርስቲ መማር፣ በመመረቂያ ወቅት፣ የስራ ወይም ከፍተኛ የውጭ ትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ለወያኔ ኢሕኣደግ ታማኝ ባሪያ ሆኖ ለማገልገል በፊርማቸው ሲያረጋግጡ መለስ ዜናዊን አዋርደን የሚል ፈቃድ ኣልሰጠነውም ማለት ይችላሉ? በዜግነቱ ማግኘት የሚገባቸውን መብት የወያኔ ካድረዎችን ጫማ በመሳም፣ እኒህ የቀን ጅቦች በልተው የማይጠቅማቸውን ጉቦ በመስጠት የንግድና ኢንቨስትመንት ፈቃድ፣ የሀገር ውስጥ ብድር የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የሚሞክረው ነጋዴ፣ የፋብሪካ ጌታ፣ የሕንጻ ተቁዋራጭና ሌላውም ባለሃብት በሃገሩና በራሱ ላይ ለመጣው ውርደት ተጠያቂ ኣይደለሁም ይላል? በዜግነቱ ማግኘት የሚገባውን በሃገሩ የመኖር፣ ንብረትና ቤት የማበጀት መብት ለወያኔ አስረክቦ የወያኔን ችሮታ ለመቀበል በሀገሩና በወገኑ ላይ የሚደርሰውን ስቃይ ወደ ጎን ብሎ የመሬትና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን የሚያሳድደው በውጭ አገር የሚኖር ወገናችንስ ራሴን አላዋረድኩም ለሀገሬ መዋረድ የድርሻዬን አላበረከትኩም ማለት ይችላል? የፖለቲካ ሰዎችስ? የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎችስ? ከስሜ፣ ከግል ክብሬ፣ ከግልና ከድርጅቴ ጠባብ ጥቅም በላይ የሃገርና የወገን ጥቅም ይቅደም በሚል፣ ከሸፍጥ፣ ከድህነትና ከማናለብኝነት መንፈስ ውጭ ተባብረውና ሕዝብን አስተባብረው ለመነሳት ባለመቻላቸው የመለስ ዜናዊን ኣገዛዝ ዕድሜ አልቀጠልንም? በስሙ የምንምልለትን ሕዝብ መከራ አላራዘምንም ማለት ይችላሉ? ማነው የማይጠየቅ? የመንግስት ሠራተኛው፣ ወታደሩ፣ የተቀረው ሕዝብ፣ ቄሱም ሼኩም የኢትዮጲያ ሕዝብ ለሚገኝበት እጅግ ኣሰቃቂ የሆነ የድህነት ኣዘቅት፣ የመብት ረገጣ፣ የልዑኣላዊነት መገሰስ፣ መለስ ዜናዊ ኣገራችንን እየጋታት መርዘኛና ከፋፋይ የሆነ የዘርና የሃይማኖት ጭማቂ ተጠያቂ ኣይደለንም ማለት ይችላሉ?ደረጃው ይለያይ እንጂ በሃገራችንና በራሳችን ላይ ለሚደርሰው ውርደትና ስቃይ ሁላችንም ተጠያቂዎች፣ ሁላችንም ወንጀለኞች ነን።
ይህ ሃቅ ሺህ ጊዜ ብንፍጨረጨር፣ ምንም ዓይነት ራሳችንን የማጭበርበር ክህሎት ቢኖረን የማናመልጠው ሃቅ ነው። ይህንን በፍጥነት መረዳቱ የመከራ ቀናችንን ለማሳጠር ትልቁ እርምጃ ነውና፣ ሁላችንም እራሳችንን እንጠይቅ። እነዚህ በሃገራችን ላይ የነገሱ ፀረ-ኢትዮጲያና ፀረ- ሕዝብ ኃይሎች የሚፈጽሙትንና የሚያስፈጽሙትን ግፍና በደል ለማስቆም እያንዳንዳችን ራሳችንን ምን አድርጌኣለሁ? ምን እያደረግሁ ነው? ብለን እንጠይቅ።