በምዕራቡ የአገራችን ክፍል -ጋምቤላ – እሮሮ በዝቷል!!!
ለምለሟ ጋምቤላ ለነዋሪዎቿ ሲዖል፤ ለመለስ ዜናዊ ምርጦች ግን ገነት ሆናለች። ለምለሟ ጋምቤላ ነዋሪዎቿ የሚራቡባትና የሚታረዙባት፤ ባህር ተሻግረው የመጡ ቹጃሮች ግን ሲሳይ የሚያፍሱባት ምድር ሆናለች። ለምለሟ ጋምቤላ ነዋሪዎቿ ለእስርና እንግልት፣ ለመፈናቀልና መሰደድ፣ ሲከፋም ለሞት የሚዳረጉባት፤ ቹጃሮች ግን በከርሰ-ምድር ሃብቷ ሰበብ የሚራኮቱባት ክልል ሆናለች። ጋምቤላ ፍቅረ ንዋይ አዕምሮዓቸውን ያነወዛቸው ዘረኞች ባድማ ሆናለች። የትግራይ ገዢ ጉጅሌ፣ ጋምቤላ ውስጥ ገንዘብ እንጂ ሰው ያለ መሆኑ አይታወቀውም።
በጋምቤላ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ሰቆቃ ቃላት ሊገልጹት ከሚችሉት በላይ ነው። የዛሬ አስር ዓመት የአኝዋክ ወንዶች በመለስ ዜናዊ የጦር ሠራዊት አባላት እየታደኑ ተገደሉ፤ ህፃናት ታረዱ። ሴቶች በባሎቻቸውና በልጆቻቸው ፊት ተደፈሩ። አንዳንዶቹም ተደፍረውም ተገደሉ። መንደሮች በእሳት ጋዩ። ሞትና እልቂት በመላው ጋምቤላ ምድር ተዘራ። በጥቂት ቀናት ውስጥ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ አኝዋኮች ህይወታቸውን አጡ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አስከ አሁን ጥቃቱ አላባራም። በሺዎች የሚቆጠሩ አኝዋኮች በግፍ ተገድለዋል። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ የማይጠገን የአካልና የመንፈስ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በህይወት የተረፉት ጥቂቶች በወያኔ እስር ቤቶች ውስጥ እየማቀቁ ነው፣ አሊያም ተሰደዋል። ጋምቤላ ለአኝዋኮች ባይተዋር ሆናለች።
በአንፃሩ ደግሞ ለመለስ ዜናዊ ዘረኛ ቡድን እና ተላላኪዎቹ ጋምቤላ የወተት ላም ነች። የመለስ ዜናዊ የግል ዘመዶችና ሸሪኮች የጋምቤላን መሬት በብላሽ ተመርተው ደኑን እየማገዱ ከሰል በመሸጥ ከብረዋል። የደኑ መራቆት አያሳስባቸውም። የገበሬዎች መፈናቀል አያገባቸውም። መከረኞቹ አኝዋኮች ግን ከትውልድ ቀያቸው ተፈናቅለው መውደቂያ አጥተዋል። እርሻቸውና የግጦሽ መሬታቸው በትግራይ ገዢ ጉጅሌ አባላት አልያም ከሩቅ አገራት በመጡ ቱጃሮች ተነጥቀዋል። አቤት የሚባልበት ቦታ የለም።
ጂኖሳይድ ዎች፣ ሂውማን ራይትስ ዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ለጋሽ አገራት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ የረድኤት ድርጅቶች ስጋታቸውን ይገልፃሉ፤ ይመክራሉ፤ ያስጠነቅቃሉ፤ ያስገነዝባሉ፤ ሲብስባቸውም ይጮሃሉ። የሚሰማቸው ግን የለም። የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ግንባር ቀደም መሪዎችና ጀሌዎቹ በሃብት ቅርምት ላይ ናቸው።
በዚህ ሁሉ ግፍ መሃል ጋምቤላ ምጥ ላይ ነች። ጋምቤላ ለበደሏ ቤዛ ሊሆኑ የቆረጡ ልጆችን መውለድ ቀጥላለች። እናም የወያኔ መፈንጫ ሆና አትቀርም። አዎ! ጋምቤላ ምጥ ላይ ነች፤ ለእርዳታም ትጣራለች። ለጋምቤላ መድረስ ለኢትዮጵያም መድረስ ነው። የጋምቤላ እጣ ፈንታ የኢትዮጵያም እጣ ፈንታ ነው። ለጋምቤላ ጥሪ ምላሽ እንስጥ!!!
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ በጋምቤላ ዜጎቻችን ላይ እያደረሰ ያለው በደል ያንገበግበዋል። በግንቦት 7 እምነት ከአኝዋኮች ጋር የተገደልነው፣ የተገፋነው፣ የተደፈርነው፣ የተዋረድነው ሁላችንም ነን። በጋምቤላ ነዋሪዎች ላይ የደረሰው በደል በደላችን፤ ህመማቸው ህመማችን ነው። ከጋምቤላ ጋር እየተመዘበረች ያለችው ኢትዮጵያ ነች።
በጋምቤላ ክልል ውስጥ እየተፈፀመ ያለውን ግፍ በማጋለጥ ረገድ እስካሁን የአካባቢው ተወላጆች እያደረጉት ያለውን ጥረት ግንቦት 7 ያደንቃል። እየተደረጉ ያሉት ጥረቶች እንዲቀናጁ የበኩሉን አስተዋጽዖ ያደርጋል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በጋምቤላ እየተፈፀመ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲቆም እና ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ ይታገላል። የጋምቤላ ለም መሬትን በማደል ሃብታሞች ይበልጥ ሃብታም እንዲሆኑ፤ ድሆች ደግሞ የእለት ጉርሳቸውን ሳይቀር እንዲያጡ እየተደረገ ያለውን እኩይ ድርጊት በጥብቅ ይኮንናል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ የትግላችን ትኩረት የዚህ ሁሉ መከራና ግፍ ምንጭ የሆነውን ወያኔን በማስወገድ በምትኩ ፍትህ፣ ነፃነትና ዲሞክራሲ የሰፈነባት፤ ሕዝቧ በእኩልነት፣ በአንድነትና በሰላም የሚኖርባት ኢትዮጵያን በመገንባት ላይ ማነጣጠር ይገባዋል ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!