ትውስታየ በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር

የእሳት እራት

ትውስታየ በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር

የምድር ፈራጅ ሆይ ከፍ ከፍ በል፤

ለትዕቢተኞች ፍዳቸውን ክፈላቸው።

አቤቱ ህዝብህን አዋረዱ፤

ርስትህንም አስቸገሩ።

መዝሙረ ዳዊት 93/4 ቁ 2-5

በ1993 ዓ.ም በካርታ ሥራ ድርጅት አዳራሽ ውስጥ ትልቅ ስብሰባ ይካሄዳል ተብሎ ውጭ ጉዳይ ሥራ በዝቶበት ሰንብቷል። አምባሳደሮች ከያሉበት በአስቸኳይ እንዲመጡ በተላከላቸው ደብዳቤ መሰረት ገስግሰው አዲስ አበባ ከተዋል። ወጪያቸው በሙሉ በመሥሪያ ቤቱ ይሸፈናል ስለተባለም ለእንቁጣጣሽ አዲስ ልብስ የተገዛለት ህጻን የሚፈነድቀውን ያህል በደስታ ተሳክረዋል። በዋንው መሥሪያ ቤት ውስጥም ከሶስተኛ ጸሃፊ በላይ ያሉ ብቻ በስብሰባው እንዲሳተፍ ማስተወቂያ በመለጠፉ ቀሪዎቹ የእንጀራ ልጅን ስሜት ተላብሰው በትዝብት ይመለከቱ ነበር።

አምባሰደሮቹም አንገታቸውን በካራባት አስረው ለንጉስ ሰርግ የተጠሩ እድምተኞችን መስለውና ከጣሪያ በላይ እየተሳሳቁ በተራ በተራ ወደ አዳራሹ እየገቡ ፊት ለፊት ከተደረደሩ ወንበሮች ላይ ይኮለኮላሉ። ከዚያም ግማሹ እየተሳለቀ፤ ቀሪው እየተሳተፈ ፤ሌላውም እያሳተፈ ስብሰባው ለድፍን አስራ አምስት ቀናት ተካሄደ።

የመጨረሻውን ቀን ስብሰባ መለስ ዜናዊ ስለሚመራው ተሰብሳቢው በሙሉ እርሱ ወደአለበት ተጠራ። እርሱ ህዝብ ወደአለበት መመጣትን ባለመፍቀዱ ብዙሃኑ ወደ እርሱ በሰልፍ ሄደ። ስዩም መስፍንም ከዚያ አለ። አንዴ ምንስቴር ዴእታ ሌላ ግዜ ደግሞ አምባሳደር ሲሉት ሁሉንም ይሁን ብሎ ተቀብሎ ባስቀመጡት የሚገኝ የቤቱ ጌጣ ጌጥ ተቀዳ ዓለሙም ከዚያ አለ።

መለስ ያለማቋረጥ ሲናገር ስዩም መስፍን በግንባሩ ወደ ቁልቁል የሚንዥቀዥቀውን ላብ ጠረጴዛ ላይ ባስቀመጣት መሃረብ መልሶ መላልሶ እየጠረገ ሳይታክት ይጽፋል። ከመለስ አንደበት ይሄ ነው የሚባል በጎ ነገር አይወጣም ስዩም ግን አንዷንም ቃል አይገድፍም። ተጀምሮ እስኪፈጸም ኮስተር ብሎ ይጽፋል። ደቂቃን ሠራተኞች በመለስ ንግግር ሳይሆን በስዩም መስፍን እንዲያ ሳይታክት መጻፍ በእጅጉ ተገረሙ። ምን የሚጻፍ በጎ ነገር አግኝቶ ይሆን በማለት ብዙዎች መገረማቸውን ተናግረዋል።

መለስ እንዲህ አለ “እናንተ አገሪቷን እያከሰራችሁ ነው። ዲፕሎማሲያችን ኢኮኖሚክ ዲፕሎማሲ ነው። በነገራችን ላይ “ኢኮኖሚክ ዲፕሎማሲ” የሚሉት ልመናን ነው። ኢኮኖሚክ ዲፕሎማሲያችንን አልሠራችሁም። ማምጣት የሚገባችሁን “ሃርድ ካሽ” አላመጣችሁም። በዓመት 240ሚሊዮን ብር በጀት እየበላችሁ ምንም “ሃርድ ካሽ “ አላመጣችሁም። ዋና ስራችሁ “ሃርድ ካሽ” ማምጣት ነው ሌላ ምንም ስራ የላችሁም። ዝም ብሎ ባንዲራ ማውለብለብ ምንም ዋጋ የለውም። በእናንተ ምክንያት ከስረናል ብሎ አምባሳደሮቹ ላይ አፈጠጠ። ”እንዲህ ሳያቋርጥ ሲናገር ስዩም መስፍንም ሳያቋርጥ ይጽፋል።

አንድ አምባሳደር እጁን አውጥቶ እንዲህ ሲል ጠየቀ “የኢኮኖሚው ዲፕሎማሲ ያልተሳካልን ምናልባት ፖለቲካው ላይ አተኩረን ይሆን ?” ሲል ፈራ ተባ እያለ ጠየቀ።

መለስ ለአምባሳደሩ ጥያቄ እንዲህ ሲል መለስ ”እናንተ ፖለቲካውን ሰርታችሁት አይደለም እስከ ዛሬ ይህች አገር የቆየችው። ከእናንተ በላይ የዚህችን አገር ፖለቲካ የሚሰሩልን አሉ። እርሱን በተመለከተ የምንፈልገውን ነገር በተሻለ ፍጥነትና በተሻለ የጥራት ደረጃ እዚህ ካሉ ከየአገራቱ አምባሳደሮች እናገኛለን። ”

ሌላም ጥያቄ ተከተለ ለምሳሌ ጋና ካለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምን ዓይነት “ሃርድ ካሽ ማግኘት እንችላለን። እዚያ ያለው እምባሲ ባንዲራችንን እያወለበለበ ኢትዮጵያን ከማስተዋወቅ ውጪ ምን ሊሰራ ይችላል?”

መለስ ዜናዊ ነፍሱ በተቃርኖ የተሞላች ነች። ዛሬን እስካደረ ድረስ ለነገ የሚል ደግ አስተሳሰብ ያለው ጤነኛ ሰው አይደለም። እናም ስለ “ሃርድ ካሽ” ያወራውን በተመለከተ የተጠየቀውን ጥያቄ እንዲህ ሲል መለሰ “እኛ እያልን ያለነው ገንዘብ ሊሰጡ የሚችሉ አገራት ውስጥ የምትሰሩትን አምባሳደሮች ነው። ሃርድ ካሽ የማታመጡ ከሆነ ምን ልትሰሩ ነው ታዲያ ? ካሁን በኋላ ኪሳራውን ይዘን ለመቀጠል አንችልም” ብሎ አስፈራራ።

በዲፕሎማሲው መንደር ውለው የማያውቁ ካድሬዎችን አምባሳደር አድርጎ ሹሞ ሲያበቃ ይህን አልሰራችሁም ያን አላደረጋችሁም ብሎ መቆጣት ድንፋታ ይባላል። መለስ እንደልማዱ ደንፍቶ ደንፍቶ ሲያበቃ ስብሰባው ተፈጸመ ተባለ።

አንዱ አምባሳደር “እንግዲህ ሃርድ ካሽ ካልተገኘ የራሴን ደሞዝ አጠራቅሜ ይዤ እመጣለሁ” ብሎ ቀለደ ሲባል ሰምተናል። ይህ ግን ቀልድ አይደለም። ምሬት ነው።

በዚህ ስብሰባ ላይ እኔ አልተሳተፍኩም። ከእነዚህ ሰዎች ጋር አብሮ ከመስራት ተሰድጄ ርቄ ብኖር ይሻለኛል ብሎ ቀየውን መንደሩን ጥሎ ወደ ሩቅ አገር የተሰደደው አለቃየ ከስብሰባው በኋላ ስንጫወት የነገረኝን መንደርደሪያ አድርጌ ወደ ራሴ ጉዳይ እዘልቃለሁ።

የራሴ ጉዳይ እንዲህ ይጀምራል፤

እግዜርን ፍራ። እግዜርን መፍራት ስታውቅ ሰው ትሆናለህ። ልጄ እባክህ ሰው ሁን እያለ ያሳደገኝ አባቴ አሁን በህይወት የለም። እግዜሩን ፈርቶ እኔንም እንድፈራ አድርጎ ኑሮ ሲያበቃ በቅርቡ አረፈ።

ማህበረ ሰቡም ገና ድሮ ህጻን ሳለሁ ፈሪሃ እግዚአብሄር ከሚገለጽባቸው ነገሮች መካከል አንዱ በአገር ላይ የተሾመን ሁሉ ማክበር ነው ብሎ አስተምሮኛል። መንግስቱ ኃ/ማሪያምን ያስነሳው አምላክ ነው። መለስ ዜናዊንም ያመጣው እርሱ ፈጣሪ ነው። እርሱ ያመጣውን እርሱ እስኪመልሰው ድረስ ጸጥ ለጥ ብለን ተገዝተን እንድንኖር ትእዛዝ እንዳለ እየተነገረኝ ለአቅመ አዳም ደረስኩ።

ታልቁ መጽሃፍም ትእዛዙን የሚጠራጠር አንዳች አያገኝም ብሎ አስፈራርቷል። የተሾመን ማክበር ለእርሱም መታዘዝ ፈጣሪን መፍራት እንደሆነ ከመቀበል ወጪ የተለየ እውቀት የሌላቸው ወላጆቼ ይሄን እውነት ነው ብለው ተቀብለውና መክረው አሳድገውኛል።

ሀ ሁ ብየ ፊደል ቆጥሬ አ ቡ ጊዳንም ዘልቄ የእውቀቴን ልቀትና ጥልቀት ላሳፋ አስቤ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ገባሁ። ከዚህ የዘላለም የሰው ልጆች ማደጊያ ሥፍራ ከፍ ባለ ማእረግ ተመረቅሁ። ከዩንቨርስቲ ካገኘሁት እውቀት ላይ የአቶ ሃዱሽ ገ/እግዚአብሄር መልካም ፈቃድ ታክሎበት በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ተቀጠርኩ። ሃዱሽ ገ/እግዚአብሄር ውጭ ጉዳይ የሚቀጠሩ ሰዎችን የጀርባ አጥንት/ታሪክ የሚያጠና ነው። ይህ ሰው በአቦጊዳ ላይ ሸፍቶ የኖረ ቢሆንም ትንጥየ “ጌታ” ሁኖ በሰዎች እድል ፈንታ ላይ ወሳኝ ሁኗል። ይቀጠር ያለው እየተቀጠረ አይቀጠር ያለው ደግሞ እየተከለከለ ለረዥም ግዜ በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውስጥ ሰርቷል። ይህ ሰው ክፉ አይደለም። ታዞ ሥራውን የሚሰራ በሰገባው የተገኘ ታማኝ አገልጋይ ነው። የጌቶቹን ትእዛዝ ተቀብሎ በራሱም ትንሽየ “ጌታ” ሆኖ እድል ፈንታቸውን የሚወስንላቸውን እጩ ተቀጣሪዎች የስም ዝርዝር ጽፎ የያዘበትን ዶሴ ይዞ ታች ላይ ሲል ከፍ ያለ የሥራ ኃላፊነት ያለውን ሰው ይመስል ነበር። ህወሃት አገሪቷን ከተቆጣጠረ ወዲህ ያገኘው የሞራል ልዕልና ካልሆነ በቀር በኑሮው የደላው ነገር ያለ አይመስልም። ህወሃቶች “አማራ ብርቱ ጠላትህ ነው ኦሮሞም ቢሆን አይተኛልህም” ብለው የነገሩትን ነውር ትምህርት አምኖ እርሱንም ትጥቅና ስንቁ አድርጎ የጀርባ አጥንት እያጠና በዜጎች እድል ፈንታ ላይ ውሳኔ ሰጪ በመሆኑ ደስ ብሎት የሚኖር ምስኪን ሰው ነበር። አሁን የት እንዳለ አላውቅም ምን አልባት የአንዱ አምባሰዳር ጠባቂ አድርገውት ይሆን ይሆናል። ምንአልባትም በአንዱ ኤምባሲ የጸጥታ ጉዳይ አማካሪ ሁኖ ይሆናል። በቦታውና በሰገባው የተገኘው አቶ ሃዱሽ ገ/እግዚአብሄር ይቅርና ዘውዱ የተባለው ነፍሰ ገዳይ በአማካሪ ማዕረግ ኬኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተመድቦ ብዙ ኢትዮጵያዊያንን ሲገድል አልከረመም ? አሁንስ ዱባይ ላይ የህወሃት ተወካይ ሆኖ “እየሰራ” አይደል ? በዱባይ “ዜድ” ቴሌቶን አቋቁሟል የሚባለውስ እርሱ አይደል ?የጸጥታ አማካሪ ማለት እንዲህ ያለውን ሥራ የሚሰራ ነው እንጂ ሌላ አይደለም። አቶ ሃዱሽ ግን ደክሟል ሩጦ ለመያዝ፤ አልሞ ለመቶኮስ፤ ጨብጦ ለመያዝ ጉልበቱ ያለው አይመስለኝም። የቀረው እድሜም ለንስሃ ከመሆን የሚዘል አይደለም።

ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ውስጥ መስራት ገንዘብ ምንስቴር ወይም ደግሞ ት/ት ምንስቴር ውስጥ እሰራለሁ እንደማለት ቀላል አይደለም። ውጭ ጉዳይ መሥራት ማለት በሁለት ስለታም ጥርሶች ውስጥ እንደመኖር ነው። የውጭ ሰዎች እንደ ህወሃት ካድሬ እየቆጠሩ በጎ ባልሆነ ዓይን ያዩሃል እዚህ ውስጥ ያሉት ደግሞ የድርጅታቸው አባል መሆንን ባለመውደድህ በጥርጣሬ እየተመለከቱህ በገዛ አገርህ ሃዘን በዝቶብህ ትኖራለህ።

አንድ የህወሃት ካድሬ በአንዲት ምሽት የሚያጠፋትን የምታክል ደመወዝ እየተከፈለኝ ለመስራት ተስማምቼ በውጭ ጉድያ መሥሪያ ቤት ስቀጠር በርቀት ያየሁትን ተስፋ እውን ለማድረግ አስቤ ነበር። ተስፋየን እውን ለማድረግ በጣም መራርና ከባድ የሆነውን ኑሮ ተያያዝኩት። ወሩ በገባ በሃያኛው ቀን ኪሴ ውስጥ የሚቀረው ገንዘብ ቁርስ፤ምሳና እራቴን ለመብላት አልበቃ እያለኝ ተቸገርኩ። ጠጪ አይደለውም። ገንዘብ እንዲሁ በቀላሉ የማባክንም ሰው አይደለውም። ብዙውን ግዜ ደግሞ እጾማለሁ። እንዲህም ሁኜ ከ600 ብር ተቆራርጦ የሚደርሰኝ 520 ብር ጨርሶ ከወሩ ጥግ አያደርሰኝም። ከወሩ ውስጥ አምስቱን ቀናት ራቴን ዳቦ በሙዝ እየጨረግድሁ አድራለሁ። አንዳንዴም አጋጣሚ ሆኖ ከደላኝ አቦካዶ ገዝቼ እርሱን በዳቦ ገምጬ ተመስገን ብየ እተኛለሁ። በእንቅልፍ ከመውደቄ በፊት ግን ውጭ ስመደብ ይሄ ሁሉ እንደሚቀየር ስለሚሰማኝ ሥራየን ብቻ በርትቼ መሥራት እንዳለብኝ ለራሴ ነግሬ ለጥ እላለሁ። ሲነጋም ተነስቼ ፊቴን ተጣጥቤ በእግሬ ወደ ብሮየ አዘግማለሁ። እግረ መንግዴን ግቢ ገብርኤል ጎራ እልና ጠበል እጠጣለሁ። እርሱ ቁርስ መሆኑ ነው። ጠበል ስጠጣ ለምን እንደሆነ አላውቅም ሳይርበኝ እስከ ምሳ ሰዓት እቆያለሁ። 11% ኢኮኖሚው አደገ በሚባልበት አገር ውስጥ አንድ የመንግስት ሰራተኛ በዚህ ሁኔታ ይኖራል።

እስኪ ዘወትር ኢኮኖሚያችን በ11% አድጓል እያለ የሚያደርቀኝና ከእኔው ጋር አንዲቷን ቢሮ ወደ ሚጋራኝ ግለሰብ እንሂድ።

“ተራራውን አንቀጥቅጬአለሁ” ከሚለው ህወሃት ከተሰኘው ደርጅት ጋር ከትግል ሜዳ ያልዋለ ነገር ግን ከከተማ ሁኜ ስረዳ ነበርኩ የሚል አንድ አባል አብሮኝ አለ። ይህ ሰው “የነጻነት ታጋዮች” ነን ባዮች አገሪቷን ከተቆጣጠሩ በኋላ በለስ ቀንቶት በሚያስገርም ፍጥነት ትልቅ ህንጻ አሠርቶ ለውጭ አገር ሰዎች አከራይቶት በየወሩ 42 ሺህ ብር ይሰበስባል። አትገረሙ። 42 ሺህ ብር ብዙ አይደለም። በእነዚህ ቡድኖች በዚያች አገር ላይ የሚፈጸሙ በጣም በጣም የሚያስደንቁ ነገሮች ሞልተዋል።

ይህ ሰው አለቃ የለውም። አለቃ ያለኝ እኔ ነኝ። እርሱ ደስ ባለው ሰዓት መኪናውን አስጓርቶ ልቡ ወደ መራው ይሄዳል ባሰኘው ሠዓት ደግሞ ይመለሳል። እኔ ከማን ጋር ሻይ እንደጠጣሁና የት እንደዋልኩ ፌርማቶሪ ተመድቦ መግቢያ መውጪያን ይከታተላል። እርሱና መሰሎቹ አሳዳጅ እኔ ተሰዳጅ ሁነን በኢትዮጵያችን እንኖራለን። ሁለት የተለያየን ዜጎች በኢትዮጵያ አለን። ኢትዮጵያ የሁላችንም አገር ብትሆንም እነርሱ ግን የሌላ ባእድ አገር የሚገዙ ይመስላቸዋል። እኔም ለእነርሱ እንደ ባእድ ነኝ።

የእነርሱ ላልሆነች አገር ደግሞ የሚያሳስባቸው ምንም ነገር የለም። እኔን የመሰሉ ብዙ ሚሊዮናት ሲራቡ፤ሲጠሙ ፤ሲታረዙ፤እነርሱ ይስቃሉ እንጂ ትንሽም ደንገጥ አይሉም። በበሉትና በጠጡት መጠን እነርሱ እድገታችን ነው የሚሉትን እየለኩት ያደርቁናል እንጂ የእለት ጉርሱን አጥቶ በየሜዳው ወድቆ የሚቀረው የአገሪቱ ዜጋ አይታያቸውም። ይህ እውነት ሲነገራቸው ጠላት ያደርጉሃል እንጂ አያዳምጡህም።

ይህ ሰው እንደፈለገ እየሆነ “ይህች ደግሞ ምን አላት” ብሎ የሚንቃትን የወር ደመወዙን ሳይቦዝን ይቀበላል። መቸስ የአገሪቷ ህግ እርሱን ለመሰሉት ሁሉ መጠቀሚያ እኔን ለመሰሉት ደግሞ መጠቂያ ሁኖ ተሰርቷል። በዚያች አገር እኔንና እርሱን እኩል የሚገዛ ህግ የለም። እርሱና መሰሎቹ ከህግ በታች ላለመሆን “ነፃ” ወጥተው ከህግ በላይ ሁነዋል። እርሱንና እኔን እኩል የሚገዛ ሥርዓት ቢሰራ ጥቅሙ ስለሚቀርበት እንዲያ ያለ ሥርዓት እንዲፈጠር ፈጽሞ አይፈልግም። እንዲህ ያለ ነገር የሚጠይቅ ካለም ወዲያውኑ በጠላትነት ይፈረጃል። አሸባሪም ይባልና የመከራ እንጀራን ይበላል የመከራ ጽዋንም ይጎነጫል።

ሰውየው የሥራ ደረጃው አንደኛ ጸሃፊ ነው። በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የሥራ እርከኖች ከምሩቅ አታሼ ጀምሮ አታሼ ፤ሶስተኛ ጸሃፊ፤ሁለተኛ ጸሃፊ፤አንደኛ ጸሃፊ ፤አማካሪ፤ምንስትር አማካሪ ከዚያ እድለኛ የሆነ ካተገኘም አምባሳደር ይሆናል። እነዚህን የውጭ ጉዳይ እረከኖች አልፎ በችሎታውና በልምዱ ለአምባሳደርነት ደረጃ የበቃ ሰው አሁን ባለው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ውስጥ የለም። በእርግጥ አምባሳደር ቆንጅት የምትባል አለች። እርሷ የጊዜው ፖለቲካ ገብቷትና ዓለማችን የደረሰችበትን የእድገት ደረጃ ተርዳታ አገራችንን ትጠቅማለች ተብላ የቆየች አይደለችም። ሴትየዋ ግዜ ተወስዶ የተተየቡ ደብዳቤዎችን “እዚህ ጋ ንጉሱ ‘ሠ’ ነው መግባት ያለበት እዚህ ጋ ደግሞ ዓይኑ ‘ዓ’ ነው መግባት ያለበት እያለች ለንጉሱ ‘ሠ’ እና ለዓይኑ ‘ዓ’ እያለች ደብዳቤዎችን ቀዶ ከመጣል በቀር ይሄ ነው የሚባል እውቀት የላትም።

ሌላ እውቀቷ ደግሞ “ኦባሳጆ እኮ ወሬኛ ነው። ጋዳፊ ባለጌ ነው። አለባሽር የዋህ ሰው ነው። ቻርሌስ ቴይለር የነጭ አሽከር አጨብርባሪ ነው” ማለትን ግን ተክናበታለች። ይህ ደግሞ ሃሜት ነው።

በሶስቱም ሥርዓት በዚያ መስሪያ ቤት ለመቆየት የቻለችው ሃሜተኛ እና አደር ባይ በመሆኗ እንጂ ለዲፕሎማሲ የሚሆን እውቀት ኑሯት አይደለም። እርሷ ሂሊናዋ ስለማይጠይቅ ለመልአክም ይሁን ለሰይጣን ለመስራት ልቧ ፈቃደኛ ነው። በንጉሱ ዘመን ዲፕሎማት ነበረች፤ መንጌ ንጉሱን ገድሎ ሲመጣ ደግሞ ከፍ ብላ አምባሳደርነትን ተቀብላ ኖረች፤ ህወሃት ደግሞ ደርግንም ኢትዮጵያንም አንድ ላይ በልቶ ሲመጣም እርሱን ተቀብላ ደርግን እያማች አብራ ቀጠለች። ህወሃት የአጼ ሃይለ ስላሴ ሃውልት በአፊሪካ አዳራሽ አያስፈልግም ሲል እርሷም አዎን አያሳፈልግም ብላ ኑሯዋን ትኖራለች። እርሷ አማራ ነች ቢሆንም ግን እነመለስ “አማራና ኤምፔሪያልዝም የትግሬ ቀንደኛ ጠላቶች ናቸው” ብለው የጻፍትን ሰነድ ያየችው አይመስለኝም። ምክንያቱም ማንበብና መጠየቅ እጣ ክፍሏ አይደሉም።

የትምህርት ደረጃዋን በተመለከተ ድሮ በንጉሱ ዘመን ከእንግሊዝ አገር በሴርትፊኬት ተመርቃለች። ከዚያ ልቃ ሂዳ ቀለም አልቆጠረችም።

ከእንግሊዝ አገር ሰርቲፊኬቷን ይዛ እንደተመለሰች እንዲህ የሚል ማመልከቻ ጻፈች፤

“ከእንግሊዝ አገር ያገኘሁት ስርቲፊኬት ከኢትዮጵአያ ድግሪ ጋር የሚተካከል በመሆኑ በዲግሪ እንዲያዝልኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ”

ይህ እንግዲህ ንጉሱ ሳይወርዱ የተጻፈ ማመልከቻ ነው። የንጉሱ ሹምም እውቀቷን ሳይሆን ጀርባዋን አይተው ቀጠሯት።

የስድስት ወር የምስክር ወረቀት እንደምን ሁኖ ድፍን አራት ዓመት ተለፍቶ ከሚገኝ ድግሪ ጋር እኩል ይሁንልኝ ተብሎ ይጠየቃል ?ለዚያውም በንጉሱ ዘመነ መንግስት። “ክብርት” አምባሳደር ቆንጅት ስነጊዮርጊስ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ካላት መልስ እንድትሰጥበት እጠይቃለሁ። አምባሳደሯ በህይወት ዘመኗ ትዳር አልያዘችም። አምባሳደር የሚል ቅጽል ባይኖራት ኑሮ ወ/ት ተብላ ትጠራ ነበር። እደለኛ ነች መደበቂያ ቅጽል ማንጠልጠልን ችላበታለች።

የወ/ሪት ቆንጂትስ ይሁን አስራ ሁለተኛን ጨርሳ እንግሊዝ አገር ሂዳ ጥቂት ተምራ ሰርቲፊኬት አምጥታለች ደግሞም ነጉሱ “ሠ” እና ዓይኑ “ዓ”ን ጠንቅቃ ለይታለች። በዘመነ ህወሃት ፌደል ቆጥረው መጨረሳቸው በውል ሳይለይ በህግ ማስትሬት ድግሪ የታደሉ ብዙ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሞልተው ተርፈው የለም እንዴ? አገሪቷስ የምትመራው እንዲህ የአገሪቷን የትምህርት ስርዓት በሚያፈርሱ ቡድኖች አይደለም እንዴ ? ለምሳሌ በአሁኑ ሰዓት በስዊድን የኢትዮጵያ ልዩ መልእክተኛ መብራት በየነን ማየት ይቻላል።

“ንግባኢኬ ሃበ ጥንተ ነገር”ይላል አንድ መጽሃፍ ወደ ቀድሞ ነገራችን እንመለስ ማለት ነው።

የቢሮየ ተጋሪ ደመወዙ ተጨምሮበት በወር ከ43 ሺህ ብር በላይ ገቢ ያገኛል። እኔ በወር የተጣራ 520 የኢትዮጵያ ብር ሲደርሰኝ እርሱ ያን ያክል ማግኘቱ በዜጎች መሃከል እየተፈጠረ ያለውን የሃብት ክፍፍል ልዩነት ለማሳየት ጥሩ ምሳሌ ነው። እርሱም የመጀመሪያ ዲግሪ አለው። እኔም ከአዲስ አበባ ዩንቭርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪ አለኝ። ታዲያ ይሄ ሁሉ ልዩነት እንዴት ተፈጠረ ? እንደሰው ለፍቶ ጥሮ ግሮ በላቡ በወዙ አግኝቶ ልዩነቱን ፈጥሮ ቢሆን መልካም ነበር። ነግሩ ግን እንዲያ አይደለም። ዝርፊያ ነው። አገሪቷ የእነርሱ ስለማትመስላቸው የመንግስትን ስልጣን ተገን አድርገው ኮንትራባንድ ይነግዳሉ። መሬት ይነጥቃሉ ይሽጣሉ። ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ማንኛውንም ወንጀል የተባለ ነገር ሁሉ ይፈጽማሉ። በአጠቃላይ አገሪቷን ባለው መንገድ ሁሉ በመቀራመት ተግባር ላይ ተጠምደዋል። የአገሪቷን መሬት እንደልባቸው ለመሸጥና ለመለወጥ ህወሃቶች መብቱ አላቸው እኔ ያ መብት እንዳይኖረኝ በህግ ደህና ተደርጌ ታስሬአለሁ። እነርሱ የዜጎችን መሬት ነጥቀው ይሸጣሉ ይለውጣሉ። እኔ ግን ወላጆቼ ያወረሱኝን መሬት እንኳ እንዳልሸጥ እንዳልለውጥ ህግ ተሰርቶልኛል። የህወሃት ዓባል የሆነ ሁሉንም ነው። ለእነርሱ ወሰንና ገደብ የለም እነርሱ ከሁሉ በላይ ናቸው።

መጥኔ ለህወሃቶች !!! መጥኔ ለእነርሱ !!!ብለን እንቀጥል።

እኔ የህወትን በጎ ነገር የማውቀው የለም። የዚህ ድርጅት አባል መሆን አሳፋሪ ነው። ህወሃቶች ግን እፍረትን አያውቁም። እንዲያውም በነውራቸው ኮርተው በትግራይ 100% በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ደግሞ በ99.6% ተመርጠናል በማለት አገሪቷን በግምት እየገዟት ይገኛሉ። ምን ያድርጉ ሰው የሌለበት ባዶ ቤት አገኙ ያንንም ቤት ጠያቂ ጠፋ እነርሱም በዚያ ጌቶች ሆኑ

አሁንም ወደ ቢሮየ ተጋሪ ሰው እንመለስ። ከዚህ ሰው ጋር ብዙም ማውራት አልወድም። ክፉ ትእቢተኛ ነው። ሃይማኖቱን የማያውቅ ወይም ደግሞ የዓለሙን ነገር በደንብ የማይገነዘብ ዞንቢ ነው። ለሰው ልጆች ክብር የሚባል ነገር በውስጡ አልተፈጠረም። እኔን የሚያክል ልጅ ወልዶ ሲያበቃ ከአንደበቱ የሚወጣው ነውር አስደንጋጭ ነው። በሽምግልናው ወቅት እንኳ ራሱን መግራት ያልቻለ ግለሰብ ነው። እርሱን ብቻ የሚያውቅ ሰው በትግሬዎች ላይ ብርቱ ጥላቻን ያሳድራል። እርሱን የመሰሉ ብዙ የትግሬዎችን መልክ የሚያጠፉ ከንቱ ግለሰቦች ሞልተዋል። እኔ ተወልጄ በኖርኩበት አካባቢ ትግሬዎች የሚገለጹት በታማኝነታቸው፤በታታሪነታቸው፤በየዋህነታቸው እና በግልፍተኝነታቸው እንጂ በጨካኝነት፤በስግብግብነት ፤በሌብነት እና ጥላቻን በመዝራት አልነበረም። አሁን የቢሮየን ተጋሪ የመሰሉ ህወቶች ያስተዋወቁን ትግሬዎች እኛ ድሮ የምናውቃቸውን አይደለም። ከህወሃቶች በፊት እኛ የምናውቃቸው ጥሩ ትግሬዎች አሁን የት እንዳሉም አላውቅም። ምን አልባት እነዚህ ተኩላዎች የዋሃን ርግቦችን በልተው ጨርሷቸው እንደሆነም አላውቅም።

ይህ የቢሮየ ተጋሪ አንዳንዴ ያለ ሥራ ወደ ውጭ አገር መሄድ ፈልጎ ከተከለከለ ስዩምን ደደብ አህያ እያለ ይሳደባል። መለስን ደግሞ ጀግና እያለ ያሞካሻል። እንደፈለገ ቢል እኔ ግን ምንም አስተያየት አልሰጥም። እኔ ዝም የምለው እርሱ ወሬ ከእኔ ቀድቶ ለሌሎች ያስተላልፋል ብየ ሳይሆን ተፈጥሮየ ስለሆነ ነው። የሰውን ስም እያነሳሁ በእንዲህ ዓይነቱ ነውር ነገር ውስጥ መሳተፍ አይመቸኝም።

እንዲሁ ዝም አንዳልኩ አራት ዓመቱ ደረሰና ወደ ውጭ አገር የመመደብ ምኞቴ እውነት ወደ መሆን ተቃረበ። የት አገር ይመድቡኝ ይሆን እያልኩ ማሰብን ተያያዝኩት። ኤምባሲዎቻችን ውስጥ ያሉ ክፍት ቦታዎችን አጠናሁ። አንዳንድ አገሮችንም መርጬ ለኑሮ መልካም ይሆኑ እንደሆነ አጠናሁ። ነገሮች ሁሉ መልካም መሰሉኝ። በነገራችን ላይ አንድ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሠራተኛ ወደ ውጭ አገር ያሉ ኤምባሲዎች ከተመደበ ከሲኦል ወደ ገነት እንደተዛወረ ይቆጠራል። በዘመድ አዝማድ መካከልም ፍጹም ደስታና እፎይታ ይሆናል። ድሮ ድሮ ወደ ውጭ አገር መላክ እንደ ግዞት ይቆጠር ነበር ሲባል ሰምቼ ነበር። የህወሃት እድገት ያመጣው አንዱ ፈተና አንድ ሰው ከቀየው ከመንደሩ ተነቅሎ ሲሄድ ፍጹም ደስታንና እፎይታን የማግኘቱ ሚስጢር ነው።

እኔም ወደ ውጭ መሄጃየን ግዜ እያሰብኩ ለቤተሰቦቼ አይዟችሁ ያዘመመ መኖሪያችን የሚታደሰብት ግዜው ደርሷል እያልኩ አጽናናቸው ጀመር።

ወላጆቼም በተስፋ ተሞልተውና ደስ እያላቸው ይመርቁኝ ጀመር። ሊወድቅ ያዘመመን ቤት ስጠግንላቸው እየታየኝ እኔም ውስጤን ደስ ሲለው ተሰማኝና መስሪያ ቤቴንም ወደደኩት። ይሄን እድል ለሰጠችኝ አገር ታምኜ ማገልገል እንዳለብኝም ራሴ ለራሴ ቃል ገባሁ።

ሙዝ በዳቦ ከመብላት ልላቀቅ መሆኔንም እያሰብኩ ዘና አልኩ። ከምደባየ ስመለስም እንደ ቢሮየ ተጋሪ በወር 42 ሺህ ብር ማከራየት የምችለው ዓይነት ቤት ባይኖረኝም ከግለሰብ ኪራይ ቤት ወጥቼ የራሴ ማደሪያ ሊኖረኝ እንደሚችል አለምኩና ደስ አለኝ። በዚያች አገር ከዚህ በላይ ምን እንዳስብ ይጠበቅብኝ ይሆን ? ሌላ ነገር ማሰብ ወንጀል የሆነበት አገር ውስጥ ምን ላስብ እችላለሁ ?

እንዲህ ምድባየን በተስፋ እየጠበኩ ባለበት ወቅት የ1997 ዓ.ም ምርጫ ተቃረበ ቀስ በቀስም ቅንጅት የተባለ ድርጅት መጣ። ሁሉም በያለበት ሁኖ ክርክሩን ተከታትሏል። ግሩም ድንቅ ክርክርና ውድድር ነበር። የኢሕአዴግ ቱባ ቱባ ባለስልጣኖች በቴሌቭዥን መስኮት ብቅ እያሉ ክርክር ሳይሆን ስድብ መሰል ነገር ያዙ። የቅንጅት ተከራካሪዎች በትምህርት ደረጃቸው የላቁ በመሆናቸው ለክርክሩ አንብበው ተዘጋጅተውበትና የሚናገሩትን አውቀው ሲመጡ ስዩምን ጨምሮ የኢሕአዴግ ዋና ዋና የተባሉ ሰዎች ትእቢታቸውንንና ባዶነታቸውን ብቻ ይዘው መጡና አይቼ በትካዜ ተዋጥኩ። ከዚያም “ኢንተርሃሞይ” የተባለ ባእድ ቃል በመጨመር የክርክሩን ድባብ አጨለሙት። የውጭ ጉዳይ ሠራተኛ መሆኔን የሚያውቁ “ለመሆኑ እነዚህ ናቸው እንዴ አገር የሚመሩ” እያሉ ለሚጠይቁኝ መልስ መስጠት ተሳነኝና ዝም ማለትን ምርጫየ አደረኩት።

ለሚነሳው ጥያቄ ሁሉ መልሳቸው የደርግና የትምክህተኛ ጥያቄ እያሉ በመሳደብ ጥሩ ደጋፊዎቻቸውን ሁሉ አሳፈሩ። እኔም አፈረኩባቸው። እነርሱ ግን እፈረት አያወቁም። እንዲያውም በነውራቸው እርስ በርሳቸው ሲሞጋገሱ ሰምቼ በጣም ተገረምኩ። ነውራቸው ክብራቸው የሆኑ ዜጎች በአገዛ አገሬ ላይ መሰልጠናቸውን ሳይ አዘንኩ።

የቢሮየ ተካፋይም “አይ በረከት ወንድ ነው። ልክ ልካቸውን ነገራቸው እኮ። ይሄ ትምክህተኛ ሁሉ ስልጣን እንዲሁ ሊወስድ ይፈልጋል እኮ እያለ ይፎክራል። ደግሞ አያፍሩም መሬት ይሸጥ ይላሉ እነዚህ የኤምፔሪያልዝም ርዝራዦች” እያለ ቅንጅቶችን ይሳደባል። እርሱ ግን ሁለተኛ ቤት ሊሰራበት መሬት ለመግዛት ላይ ታች ይላል። ህወሃቶች እንዲህ ናቸው። ሌላውን ይከለክላሉ እነርሱ ግን በዚያ ሥፍራ ዋነኛ ተዋኒያን ይሆናሉ። ብዙዎቹ ይሄ ነውር መሆኑን የሚረዳ ሂሊና የላቸውም። አገርንም የሚያፈርስ ተግባር መሆኑን አይረዱትም። ወይም ለመረዳት አይፈልጉም።

በተቻለኝ ሁሉ ከዚህ ሠው ጋር ምንም ዓይነት አገራዊ ጉዳይ ላለማውራት እጠነቀቃለሁ። የእነርሱ አገር እና የእኔ አገር የተለያየች ሁናለች። እኔ ስለእነርሱ አገር ማውራት ፍላጎት የለኝም። ስለዚህ ዝም ማለት የተሻለ አማራጭ ነው ብየ አምን ነበር።

አንድ ቀን ስለ ባድሜ ጉዳይ ተነሳና አፌን ከፊቼ አስተያየት ሰጠው። ወደ ጦርነቱ መገባቱ ትክክል ነው ብየ አላምንም አልኩ። ከተዋጋንና ያ ሁሉ ሰው ከሞተ በኋላ ደግሞ አልጀርስ ድረስ ሂዶ ይግባኝ የማይባልበት ስምምነት መፈራራም ትክክል ነው ብየ አላምንም ስል ጨመርኩ።

እንዴት ? አመራሩ አምኖ ትክክል ነው ብሎ ያደረገውን አለማመን እኮ ችግር አለው። ይህ ማለት ደግሞ በአመራሩ ችሎታና ብቃት ላይ ጥራጣሬ አለህ ማለት ነው ሲል ደመደመው።

ከዚህ በኋላ ምን መነጋገር ይቻላል። ለማንኛውም ጉዳዩ ከሮ ሌላ ነገር እንዳያስከትል ስለሰጋሁ እንዲህ አልኩት ይሄ የመጠርጠር ያለመጠርጠር ጉዳይ ሳይሆን በነገሩ አጀማመርና አፈጻጸም ላይ ግልጽነት ስለሚጎለው እውቀት የለኝም ለማለት ነው ።

ይገርማል አለ።

እዚህ ውስጥ ምን የሚገርም ነገር አለው ስል ጠየኩት።

ብዙ የሚገርም ነገር ብሎ ዝም አለ። ከዚህ በኋላ አልተነጋገርንም።

ይህች እለትና ይህች ንግግር ተስፋየንና ምኞቴን ያመከነች መሆኗን የተገነዘብኩት ብዙም ሳልቆይ ነው።

የአዲስ አበባ ህዝብ በሙሉ ቅንጅትን በመምረጡ በህወሃት ፤የውጭ ጉድይ ሰራተኛ ደግሞ በስዩም መስፍን ጥርስ ውስጥ ገባ። ስዩምም ከሠራተኛ አስተዳደር የሠራተኞችን ስም ዝርዝር አስመጥቶ ከእነዚህ ውስጥ ባስቸኳይ 10% ይባረር ሲል መመሪያ ሰጠ። 10%ቱን ረሽኑ ቢልስ ማን ይከለክለው ነበር ?

በቃ አስር ፐርሰንቱን አባርሩ ብሎ ቀጭን ትእዛዝ አስተላለፈ። ከአራት መቶ ሃያ ሰራተኞች መካከል 42 ሰው መባረር አለበት። በተለይ አማራ፤ኦሮሞና ጉራጌ ትኩረት ተደረገበት። ከተባረሩት 42 ሠራተኞች መካከል አንድም ትግሬ አለመኖሩ ነገሩ በሌሎች በተለይም በአማራ በኦሮሞና በጉራጌ ብሄር አባላት ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ታወቀ። የተባረሪውም ያልተባረረውም ሠራተኛ በትግሬዎች ላይ ቂም እንዲይዝ አላደረገም ማለት አይቻልም። የህወሃትም ምኞትና ፍላጎት ይሄው ነው። ትግሬዎችን ከሌላው ህዝብ ለይቶ የሥርዓቱ ተጠቃሚ አድርጎ ማሳየትና በሌላው ህዝብ እንዲጠሉ ማድረግ። በዚህ ረገድ ይሳካላቸው አይሳካላቸው ወደፊት የሚታይ ይሆናል። ጥላቻ ሥጋ ለብሶ ቁሞ እንዲሄድ ህወሃቶች ቀንና ማታ እየሰሩ ነው። ሥጋው ነፍስ የዘራ እለት ግን አገራችን ብዙ ሳታለቅስ አትቀርም። እግዜር እዚያ ደረጃ አያድርሰን ከማለት በቀር አሁን ምን ማድረግ እንዳለብን እንኳ አናውቅም። ለማንኛውም ትግሬዎች ሆይ ዝም አትበሉ። በእናንተና በሌሎች መካከል መለስ ዜናዊ የሚገነባውን የጠብ ግድግዳ ለማፍረስ መነሻ ግዜው አሁን ነው።

እኔ አማራም ኦሮሞም ነኝ። ኢሕዴግንም አምርሬ የምጠላ አልነበርኩም። እንዲህም በመሆኔ የመባረሩ ነገር እኔን ይመለከታል ብየ አላሰብኩም። እኔ ለመንግስት ታማኝ አገልጋይ መሆኔን ስለማውቅ መባረሩን እንደ እኔ ዝም ማለትን ልማድ ላላደረጉ ትቼ ጥቅሜን ብቻ ማሰብ ያዝኩ። አለቃየ በሥራ አፈጻጸም የሰጠኝ ውጤት ከፍተኛ ነው። ምንም የሚያሳስበኝ ነገር አልነበረም። በራሴና በተሰጠኝ ውጤት ተማምኜ ምደባየን እንጂ ሌላ ለማሰብ ምክንያት አልነበረኝም። አንድም ቀን የቅንጅትን ሃስብ ደግፌ የቢሮየ ተጋሪን ከሚመስሉ ሰዎች ጋር አውርቼ አላውቅም። ስለዚህ የሚደርስብኝ ዱላ ይኖራል ብየ አልተጨነኩም። ቢሆንም ተባረርኩ።

አስር ፐርሰንቱን መርጠው የሚያባርሩ ግለሰቦች በሚስጥር ተመርጠው በስዩም መስፍን ተሰየሙ። ኋላ እንደታወቀው በመስሪያ ቤቱ ውስጥ የነበሩት ህወሃቶች በቅንጅት ነውጥ ተደናግጠው ስለነበረ ለውጥ ፈላጊ ሃይሉን በሙሉ የ“ትግሬ” ጠላት ነው ብለው ፈርጀው ለማባረር ቆርጠው ተነሱ። በወቅቱ ለውጥ ፈላጊውን መርጠው ለማባረር በትጋት የሰሩና “ህወትን መቃወም ትግሬን መቃወም” ነው ብለው የሚያምኑ ናቸው የተባሉ ግለሰቦች ስም ዝርዝር የሚከተለው ነው።

1ኛ.ወንድሙ አሳምነው

2ኛ ሙሉጌታ ዘውዴ

3ኛ.ዋህደ በላይ

4ኛ.ካሳ ገ/ዮሃንስ

5ኛ.ኑረዲን ዓሊ

6ኛ.ቢነጋ ተወልደ

ሲሆኑ ፤ከቢነጋ ተወልደ በቀር ሌሎቹ በሙሉ የህወሃት አባላቶች ናቸው። ቢነጋ ተወለደ አባል ስለመሆኑ ጥርጣሬ አለ። የዚህ ታሪክ ባለቤት ቢነጋ ተወለደ እንዲህ ዓይነት ሰብቅ ውስጥ ይገባል ብሎ አያምንም። ብዙዎች የተባረሩት ግን ቢነጋን ከሌሎች ለይተው አያዩትም። እውነቱን ቢነጋ ራሱ ካለበት ሁኖ ሊነገረን ይችላል። ኑረዲን ዓሊ ከፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል በብዙ መከራ ተንጠልጥሎ የጨረሰ ነው። በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ለመቀጠር ቢያንስ 3 ነጥብ ማግኝት ይጠበቅ ነበር። ህወሃቱ ኑረዲን ግን እንደምን ሆኖ እንደተቀጠረ ፈጣሪ ይወቀው። አብረውት የተማሩት የእርሱን ትምህርት የመቀበል አቅም ደካማነትን ሲናገሩ ስሰማ ህወሃትን በተጨማሪ ታዘብኩት።

እነዚህ በሚስጥር የተደራጁ ቡድኖች ሰራተኛው ሳያውቃቸው ውስጥ ለውስጥ የሌሎች ብሄር ተወካዮችን መርጠው እና ሴሎችን መሥርተው ጥናታቸውን ጀመሩ። ከዚያም ከሰራተኛው መካከልም ጓደኛሞችን እየከፈሉ ጓደኛህ ከመንግስት ፖሊስ በተቃራኒው ሁኖ መንግስትን የሚጎዳ ተግባር ፈጽሟል። አንተ ካሁን በኋላ እርሱን የምታድንበት መንገድ የለም። ስለአንተም የምናውቀው ነገር አለ ቢሆንም አንተ ብዙ ጉዳት አታደርስም ተሳስተህ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለን። አሁን ስለ ጓደኛህ የምታውቀውን ንገረን እያሉ ያፋጥጡ ገቡ። ያ አራትና አምስት ዓመት እየራበው በውጭ ጉዳይ ቆይቶ የምደባው እድል እንዳታመልጠው የሚፈልግ ሁሉ ሂሊናውን ለኑሮው እየሸጠ ወንድምና እህቶቹን አሳልፎ ለመሰጠት ልቡ ፈቀደና ለሚጠየቀው ሁሉ “አዎን እርሱ እንዲዚያ ብሏል። እርሷም እንዲያ ተናግራለች” እያሉ ምስክርነታቸውን ይሰጡ ጀመር። ይሄ እንግዲህ ህወሃት ብቻ ሳይሆን አገራችን እየደረሰች ያለችበትን የሞራል ዝቅጠት የሚያሳያን አንዱ ክፍል ነው። አገርም ፈረሰ የሚባለው እንዲህ ሲሆን ነው። ለሚበላና ለሚጠጣ ብሎ ወንድም ወንድሙን እህት እህቷን አሳልፈው መስጠት የጀመሩ እለት አገርም አብራ መፍረስ ትጀምራለች። ክፉ መንግስትም የዜጎችን መልካም እሴቶች እያዋረደ መንገድ ሠራሁላችሁ እያለ ዜጎችን ያደርቃል።

ህወሃቶች ወንጀል የሚሉት ቅንጅትን መደገፍ ነው። ወንጀል ሁኖ የሚቆጠረው የመንግስትን ከንቱ ፕሮፓጋንዳ አለማመን ነው። ወንጀል ሁኖ የሚቆጠረው ተውኝ እንደሰው ላስብበት ማለት ነው። ይህን የመሰለውን ነገር ነው እርሱ “እንዲህ ብሏል እርሷም እንዲህ ብላለች” እያሉ አሳብቀው እንዲባረር የሚያደርጉት። አንዱ የተባረረበት ምክንያት “መለስ መላጣ” ብሎ ተሳድቧል ተብሎ ነው። እስኪ እግዜር ያሳያችሁ የመለስን መላጣነት ራሱ መለስ ይክደዋል ?መለስ መላጣ ነው ማለት ምን የሚሉት ስድብ ነው ? እልቁንስ ስድብ የሚሆነው ስለ መለስ ቅንድብ ማማር መዝፈን እንጂ ስለመላጣነቱ መናገር አልነበረም። ምክንያቱም የመለስ ቅንድብ የሂትለርን ይመስላል እንጂ አያምርም።

አሁን በየኢምባሲው የምናያቸው ዲፕሎማት ተብየዎች አብዛኛዎቹ ለህወሃቶች ወሬ በማቀበል ወንድሞቻቸውን አሳልፈው የሰጡ ሞራለ ቢስ ግለሰቦች ናቸው። ለዚያ ነውር ተግባራቸው ሽልማት ይሆናቸው ዘንድ በየኢምባሲው ዲፕሎማት ተብለው ተሹመዋል። እነርሱም ካራባታቸውን ሸብ አድርገው ሰው መሃል ሲቆሙ ወንድምና እህቶቻቸውን አሳልፈው በመስጠታቸው የመጸጸትና የማፈር መልክ አያሳዩም።

ምንም እንኳ እንዲህ በስውር እየተጠሩ በወንድምና እህቶቻቸው ላይ መረጃ እንዲሰጡ የሚጠየቁ ግለሰቦች ስም ዝርዝር በሚስጥር ይያዛል ቢባልም በተለያየ መንገድ ማን በማን ላይ ምን እንደመሰከረ እንዲያውቅ ይደረጋል። እንዲህም በማድረግ በጓደኛሞች መካከል ጥላቻን ተከሉ። ህወሃቶች አገርን ለማፍረስ የሚጠቀሙት የታወቀው አንዱ ዜዴያቸው ይሄው ነው። ክፉ መንግስት እንዲህ በወንድማማቾች መካከል ጥላቻን ይዘራል።

ይህ ተሰውሮ የሰራተኛውን ማንነት ሲሰልል የከረመው ቡድን አጥንቶ 42 ሰራተኞችን መርጦ እንዲባረሩ አስወሰነ። እያንዳንዱ ተባራሪ ቅሬታ አለኝ ካለ ግን ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ተብሎ ለተቋቋመው ኮሚቴ ቅሬታ ማቅረብ ይችላል ሲባልም ተነገረ። የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባላት ተብለው የተሰየሙት የሚከተሉት ናቸው፤

አምባሰደር ሃሊማ መሃመድ(ኦሮሞ)

አምባሳደር ግርማ አማረ(አማራ)

አቶ ዋህደ በላይ(ትግሬ)

አምባሰደር አማን ሃሰን(ኦሮሞ)

አቶ ምንሊክ ዓለሙ(አማራ)

አቶ ዮሃንስ አብርሃ(ትግሬ)

ወ/ት ፍርዶሳ አብዱልቃድር(ትግሬ)

እነዚህ ግለሰቦች ቅሬታ ሰምተው ችግሩን ለመፍታት ለእውነት ለመቆም ሃሞት ያላቸው ግለሰቦች አይደሉም። እንዲያውም የመንግስትን ፖሊስ የተቃወመ ሁሉ መባረር አለበት ብለው የሚያምኑ ናቸው። በሁለቱ ትግሬዎች ላይ መፍረድ አይቻልም። እነርሱ የታሰሩበት የጎሳ ሰንሰለት አለ። የሌሎቹ ግን ነውራቸው ክብራቸው የሆናቸው ሆዳም የሚባሉ ናቸው። ምኒልክ ዓለሙ ከዚያ በኋላ አምባሳደር ተብሎ ተሹሟል። የሚፈልገውም እርሷን ሹመት ነበር አግኝቷታል። ሌሎቹ ግን ቀድመው አምባሰደር ተብለው የተሾሙ ሲሆኑ ህወሃቶች አማራውንና ኦሮሞውን ለማሰቃየት የሚጠቀሙባቸው ብትሮች ናቸው። ሃሊማ መሃመድን ”ከዚህ ቀደም አምባሳደር ያልንሽ በስህተት ነበር ካሁን በኋላ ተራ ዲፕሎማት ሁነሽ ትኖሪያለሽ” ብለዋት ከአምባሳደርነት ወርዳ ተራ ዲፕሎማት ሁና እየኖረች ነው።

እኔ የተባረርኩበት ደብዳቤ ሲደርሰኝ ቅሬታ አለኝ አልኩና ወደ እነዚህ ሰዎች ሄዱኩ። ከሳሼ ማነው ብየ ስጠይቅ ሚስጢር ነው አይነገርም አሉኝ። እሽ ጥፋቴ ምንድ ነው አልኩ ? ጥፋትህ መንግስትን ትቃወማለህ። በመንግስትም ፖሊሲዎች ላይ እምነት የለህም። እንዲያውም የጠቅላይ ሚንስትሩን የአመራር ችሎታ ታናንቃለህ አሉኝ። ለምሳሌ ጠቅላይ ሚንስትሩ ባድመ ላይ ያሳዩትን አቋም አንቋሸሃል አሉኝ። ምን ማለት እንደሆነ አልገባ አለኝ። ዝም ብየ እንዲህ ዓይነት ወሬ ከየት እንዳገኙ ማሰብ ያዝኩ። በእድሜው አባቴ ለመሆን ዘመን ያለው የቢሮየ ተጋሪ ጋር እንዲህ ያለ ነገር መነጋገሬ ትዝ አለኝ። እንዴት እኔን የሚያህል ልጅ ወልዶ አሳድጎ ሲያበቃ እንዲህ ዓይነት ትኝሽ ነገር አምጥቶ እኔን ለማስባረር አጉልቶና አዳብሮ ለመጠቀም ልቡ ጠነከር እያልኩ ሳስብ ዘለግ ያለ ግዜ ወሰድኩ። በባድሜ ጉዳይ ስንነጋገር “በአመራሩ ችሎታ ላይ ጥርጣሬ አለህ እንዴ” ብሎ የጠየቀኝ ቢሮየን የሚጋራኝ የህወሃቱ ሰው ነበር። በጣም ተገርሜ ሳበቃ እኔ በአመራሩ ላይ ጥርጣሬ የለኝም ስል ዋሸሁ። እነርሱም አላመኑኝም። በአመራሩ ብቃት ላይ ጥርጣሬ እንዳለህ በቂ መረጃ አለን። እንዲህ ዓይነት ጥርጣሬ ይዘህ ለመቀጠል አስቸጋሪ ስለሚሆን በዚህ ይብቃን አሉኝና አሰናበቱኝ። ከዚያም በገዛ አገሬ ይሄን ተናግረሃል ተብየ ከመባረሬ በላይ በሰብቅና የገዛ አገሩን ዜጎች በመሰለል ላይ የተመሰረት ደካማ መንግስት አገሪቷን እየመራት መሆኑ አሳዘነኝ።

ከዚያም ወደ ቢሮየ መሄድ ወደ ሲኦል የመሄድን ያክል ተሰማኝ። ሰው ካራጁ ጋር እንዴት አብሮ ይቀመጣል ?ይህ ቢሮየን የሚጋራኝ ሰው መሳይ አውሬ ያን ሁሉ ሲለፈልፍ የነበረው ወሬ ከእኔ ለመልቀም መሆኑን አሁን ተከሰተልኝ። ያችን ትንጥየ ክርክር ወስዶ ሲነግራቸው ትንሽም ቅር አለመሰኘቱ ገረመኝ። ይህ ሰው እኔን የሚያክል ልጅ አለው። እኔ እድሜየ ሃያ ሰባት ዓመት ሲሆነኝ እርሱ ከሃምሳ ዓመት በላይ ነበር። ከሃይማኖቱም ከእድሜውም ያላተማረ ክፍ ጨካኝ መሆኑን ሳስብ ሰይጣን ስጋ ለብሶ ቢሮየ ቁጭ ያለ መሰለኝ። ከሰይጣኑ በላይ ግን አገሪቷን የሚመሩት እንዲህ ዓይነት ምንምንቴ ሰዎች መሆናቸውን ሳስብ ከልቤ አለቀስኩ።

የህወሃትን እውነተኛ መልክ ዘረኝነቱን፤ ሌብነቱን፤ ሴሰኝነቱን፤ አገር አጥፊነቱንና ስግብግብነቱን ብነግረው ኑሮ በአገር ክዳትና በዘር ማጥፋት ወንጀል አስከስሶ የሞት ፍርድ እንደሚያስፈርድብኝ አሁን ገባኝ። የጠላትነት ፍጻሜው ይሄው ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ጠላቴ ካልሆነ ሌላ ማን ጠላቴ ሊሆን ነው ስል ከራሴ ጋር ሙግት ያዝኩ። አሁን ይሄን ግለሰብና ድርጅቱን ብጠላ ምኑጋ ነው ስህተት የሚሆነው ? እንደምንስ ሆኖ ልወደው ወይም ደግሞ ስሜት አልባ ልሆን እችላለሁ ?

ወደ ቢሮየ ገብቼ ይህን ምናምንቴ ግለሰብ ሳይ እገድለው ዘንድ በልቤ አሰብኩ። ሰውነቴ ሁሉ በበቀል ስሜት ተወጠረ። ይህ ሰው ተስፋየን ገድሎታል። ምኞቴንም አምክኖታል። የእኔን ህልም አምክኖ እርሱ እንዴት ነጹህ አየር እየተነፈሰ ይኖራል !? አይደረግም ስል ለራሴ ነገርኩት። እናም ይኖር ዘንድ አልፈቀድለትም እያልኩ ከራሴ ጋር እየተሟገትኩ ብሮየ ደርስኩ።

ያ ክፉ ሰው ከብሮየ የለም። ብቻየን ተቀምጬ ህወሃት በመሆንና ባለመሆን መካከል ያለውን ልዩነት ሳሰላስል ቆየሁ። እነዚህ ሰዎች ትግሬዎች ናቸው ወይስ ሌሎች ስል ከራሴ ጋር ሙግት ያዝኩ ? እነዚህን ሰዎች መቸ ነው ትግሬ ሁሉ ተሰብስቦ ወክሉን ያላቸው ?። ለማንኛውም ድሮ እኛ የምናውቃቸው እነዚህያ ጠንካራ ሰራተኛ፤ግልጽ፤ውሸት የማያውቁ፤ሃይማኖተኛ እና አልፎ አልፎ ግልፈተኛ ትግሬዎች ዛሬ የሉም። በዚያ መልክ የምናውቃቸውን ትግሬዎች እወክላለሁ የሚል አንድ ቡድን እንዴት እንዲህ በገዛ አገሬ እንዳልኖር ይከለክለኛል እያልኩ በሃሳብ ባዘንኩ። ሂሊናየን የሚያሳርፍ መልስ ግን ላገኝ አልቻልኩም።

ከሳሹና መስካሪው በሚስጢር ተይዞ 42 ሠራተኞች ጥፋተኛ ተብለው እንዲባረሩ ተደርጎ ጦማቸውን ማደረ የጀመሩት የትግሬ ነጻ አውጪዎች ነን በሚሉ ሃይሎች ነው። የእነዚህ ተባራሪ ወገኖች እውነተኛው ጥፋታቸው እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ ፍላጎት ማሳየታቸው ብቻ ነበር። ሌላ ጥፋት ሌላ የስነምግባር ጉደለት የሌለባቸው ንጹሃን በእውቀታቸውም በስነ-ምግባራቸውም እንከን የማይወጣላቸው የአገሪቷ ልጆች ነበሩ። ግና ምን ያደርጋል ተባረሩ። በአገሪቷ ውስጥም ሰርተው እንዳይበሉ የሥራ መልቀቂያ እንዳያገኙ ተፈረደባቸው።

እኔም ጥፋተኛ ተብየ ከተባረርኩ በኋላ የሥራ ልምዴን የሚገልጥ ደብዳቤ እንዲሰጠኝ ስጠይቅ “በገዛ ፈቃዴ ሥራየን ለቅቄአለሁ” ብለህ አመልክትና እንጽፍልሃለን ብለው በበደል ላይ በደል ፈጸሙብኝ። መባረሬ በደል ነው። ካባረሩኝ በኋላ ሌላ ቦታ ሰርቼ እንዳልኖርበት ማድረግ ግን ከበደል በላይ ሁኖ ሮሮ ሆነብኝ። ለማን አቤት ይባላል ? ሁሉም ቦታ እነርሱ ናቸው። ከእነርሱ ጋርም ያሉ በርካታ ሆድ እንጂ ሂሊና የሌላቸው ብዙ ሌሎች አሉ። ለምንም የማይሆኑ ። እንዲህ ብቻየን በሃሳብ ስናውዝ መለስ ተ/ማሪያም የተባለውን የመሥሪያ ቤቱን ባልደረባ አገኘሁት።

መለሰ ተ/ማሪያምና እኔ የአንድ ዓመት ምሩቃን ነን። እርሱ በስነ-ጽሁፍ ተመርቆ ውጭ ጉዳይ ፕሬስ መምሪያ ውስጥ ይሰራል። እኔና እርሱ የምንካፈለው የጋራ ነገር አለን።

ጠላ እየሸጡ ያስተማሩትን እናቱን ለመርዳትና ኑሯቸውን ለመቀየር ቤታቸውንም ለመሥራት ያለውን ምኞት ይዞ ውጭ ጉዳይ መሥራት ከጀመረ እነደ እኔ አራት ዓመት አልፎታል። እርሱም እንደ እኔ ዳቦ በሙዝ ተመግቦ ተመስገን ብሎ መኖርን ልማዱ ያደረገ ነበር። ሆኖም ግን ምኞቱን እውነት ሳያደርግ ከ42ቱ ተባራሪዎች መካከል አንዱ አደረጉት። እርሱም እንደ እኔ ነገሩ ሁሉ ግራ ገብቶታል።

አንተም እንደ እኔ የእሳት ራት ሆንክ ሲል ጠየቀኝ።

አዎን የእሳት ራት ሁኜያለሁ።

መለሰ ተ/ማሪያም ከእኔ በላይ ተስፋ ቆርጧል። ”በዚህ ዓለም ከእነዚህ ሰዎች ጋር መኖር አያስፈልግም። እዝህ መሥሪያ ቤት በመሥራቴ ያተረፍኩት ፀፀት እንጂ ተስፋ አይደለም። ተስፋው የሞተ ሰው ያው የሞተ ነው። በሥጋው ቢኖርም ያው እንደሞተ ነው። እንድኖር ያደረገኝ አንድ ተስፋ ነበር። አሁን ያ ተስፋ ሙቷል። አልቋል። ተፈጽሟል። ከእነዚህ ሰዎች ጋር መኖርና መሥራት ሥቃይ ነው የሆነብኝ። ሁል ግዜ መሠቃየት ደግሞ ይታክታል” አለ በአሮጌ ጫማው የሚደፈጥጣትን አንዲት ትንሽ ጠጠር ወደ ታች ወደ ውስጥ ይበልጥ እየደፈቃት።

ምን ማለቱ እንደሆነ የገባኝ ከውጭ ጉዳይ ከተባረረ በኋላ አሰላ ሂዶ ከሚስኪን እናቱ ቤት ራሱን ሰቅሎ መሞቱን ከሰማሁ በኋላ ነው። መለሰ ተ/ማሪያም ጥሩ አንባቢ ጸሃፊና አስተዋይ ሰው ነበር። ለዚህ ጎበዝና ጥሩ ጸሃፊ ልጅ መሞት ሃላፊነቱን የሚወስዱት የመስሪያ ቤቱ የብአዴኑ ተወካይ ዘሪሁን ረታ አሁን አምባሰደር በሎሳንጀለስ ፤ተቀዳ ዓለሙ፤እና ህወሃት የተባለው ድርጅት ነው። ሆድ አደሮቹ ዘሪሁን ረታና ተቀዳ ዓለሙ አማራ ሁነው በአማሮች ላይ እንዲህ ዓይነት ህገ-ወጥ ድርጊት ሲፈጸም ቀንደኛ አስፈጻሚ ሁነው እየሰሩ ነው። እነዚህ ሰዎች “አማራ የትግራይ ህዝብ ቀንደኛ ጠላት ነው” ተብሎ በህወሃት የተጻፈውን ሰነድ አላነበቡም ማለት አይቻልም። በደንብ አንብበዋል ግን እንዲህ ዓይነት ነውር ከሆዳቸው አይበልጥባቸውም።

ተቀዳ በሦስቱ ሥርዓቶች የሠራ ነው። የእርሱ እድሜ ያላቸው “ፋኖ ተሰማራ እንድ ሆች ሚን እንደ ቼ ጉቬራ” ብለው ሲነሱ ተቀዳ ለንጉሱ ታማኝ ሁኖ ይሰራ ነበር። ደርግም መጥቶ ገንጣይ አስገንጣይ እያለ ሲፎክር አብሮ ይፎክር ነበር። አሁን ደግሞ ከህወሃት ጋር ሁኖ ደርግን እያማ የመ/ቤቱ ጌጣ ጌጥ ሁኖ አለ። አንድ ግዜ ሚንስቴር ዴእታ ሌላ ግዜ ደግሞ ወርዶ አምባሳደር ሁን ሲሉት እየሆነ በከተቱት ሰገባ ውስጥ ሳይጨንቀው እየገባ የሚኖር ግለሰብ ነው። ይህ ግለሰብ ምቾቱ እስካልተጓደለ ድረስ ግድየለውም። ከስዩም የተራረፈውን እየለቃቀመ ደርግን በሃሜት ደሙን እየጠጣ ይኖራል። ”አማራ የትግሬ ጠላት ነው” ሲሉትም “እውነት እኮ ነው” እያለ ኑሮውን ይኖራል እንጂ ሌላ አይናገርም።

ዘሪሁን ረታም ህወሃቶች ከገቡ በኋላ የመጣ ነው። ዘሪሁን ረታ አጭርና ብልጣ ብልጥ ነው። በመስሪያ ቤቱ ሠራተኞች ዘንድ ቀራጩ ዘኬዎስ ተብሎም ይጠራል። ቤተክርስትያን አካባቢም አይጠፋም። ዘሪሁን ረታ የአስተዳደርና ፋይናንስ አገልግሎት ኃላፊ ሁኖ ሲሰራ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ላይ ባላ አንድ ፎቅ ቤት ሰርቶ ቢጨርስም ካዛእንቺስ አካባቢ የመንግስት ቤት ውስጥ ይኖራል። ላፍቶ ላይ ያሰራውን ቤት ያዩ ሰዎች በጣም ተገርመው የገንዘቡን ምንጭ ቢፈልጉ ቢፈልጉ ሊያገኙ አልቻሉም። የዘሪሁን ደሞዝ ቢበዛ ሶስት ሺህ የኢትዮጵያ ብር ነው። ሙሉ ደመወዙን ሳይበላ ሳይጠጣ ለመቶ ዓመት ቢያጠራቅም እንኳ እንዲያ ያለ ቤት ሊሰራ አይችልም። ታዲያ ጥያቄው ያን ሁሉ ብር ከየት አምጥቶ ነው ያን “ground plus “ ህንጻ ሊሰራ የቻለው ? ዘሪሁን ረታ ዘው ብሎ የገባበት የሙስና አዘቅት መኖሩን ላፍቶ ከተማ ላይ ጉብ ያለው ቤቱ ይመሰክርበታል። ከዚያ አዘቅት ውስጥ መቼም ቢሆን የሚወጣ አይደለም። እዚያው ሆኖ ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት እያለ ከመኖር ውጪ ሌላ አማራጭ ያለው አይመስልም። ከዚያም በዚያች በምናምን በሞላት ቦርጩ ላይ ያንጠለጠላትን ካራባት እየነካካ እንደ አደይ አበባ ፈክቶና አምሮ ደግ ዘመን እንዲመጣ እየጸለየ ይኖራል እንጂ ሌላ አይናገርም። ለነገሩ ህንጻ ሠርቶ የማከራየት ነገር ከተነሳ “አምባሳደሮችን” ለምሳሌ ተሾመ ቶጋን፤ገነት ዘውዴን፤ አዲስዓለም ባሌማን ጠቅሰን እነዚህ ግለሰቦች ከየት አምጥተው ቦሌ ላይ ህንጻ ሊሰሩ ቻሉ ብለን ብንጠይቅ መልስ የሚሰጠን ይኖር ይሆን ?

በእነዚህ ሰዎች አስፈጻሚነት 42 ሰራቶች ተባረርን። መለስ ተ/ማሪያምም ሞተ። አቶ አክሎግ እምሩም ሞተ።

መለሰ ተ/ማሪያም ቅንና ትሁት ሰው ነበር። የሰው ልጆችን በምንም ሁኔታ ለማስቀየምም ሆነ ለመጉዳት የማይፈልግ በጥንቃቄ ለመኖር ጽኑ እምነት የነበረው ሰው ነበር። ይሄ ጽኑ እምነቱ ነው ማንንም ሳይጎዳ ማንንም ሳይጠቅም ታንቆ እንዲሞት ያደረገው። ብዙዎቻ መሞቱ ካልቀረ ለምን ለዚያ ደረጃ ካደረሱት ሰዎች መካከል አንዱን ገድሎ አይሞትም ብለው እንደተናደዱበት አውቃለሁ። መለሰ ተ/ማሪያም ግን ማንንም በምንም ሁኔታ ለመጉዳት ፍላጎት አልነበረውም። ይሄ የእርሱ እምነት ነው። በዚህ መሠረት ለዚህ ያበቁትን ሰዎች ለሂሊና ፍርድ ትቷቸው ዳግም ላይመለስ ሂዷል።

ሰዩም መስፍን እንኳ ደም በማፈሰሰ ከኖረ ድርጅት ውስጥ የወጣና ደም ማፈሰስ ልማዱ ስለሆነ ሂሊናው ይወቅሰዋል ብለን አንጠብቅም። ስዩም ማታ የተኛትን ሴት ቀን በመርዝ ለመግደል ወደ ኋላ እንደማይል ከቀድሞ ጓዱ ሰምተን ተገርመናል። ከእርሱ ምንም በጎ ነገር አይጠበቅም።

ተቀዳ ዓለሙ፤ ዘሪሁን ረታ እና ሌሎች ግን ስሙ !!! ዓይኖቻችን በእናንተ ላይ ናቸው !!! “አማራ የትግራይ ህዝብ ቀንደኛ ጠላት ነው” ብሎ ከሚያስብ ሃይል ጋር ነው አብራችሁ የተሰለፋችሁት። እናንተ አማሮች ናችሁ። እናንተም አይደለንም አላላችሁም። ግን ምን ዓይነት አማሮች ትሆኑ !? በእርግጠኝነት እነስዩም መስፍን “አህያ” እያሉ የሚሳድቧችሁ እንደእናንተ ዓይነቱን ነው። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን “አህያ” እንደማይሉ እኔ እነግራችኋለሁ። ፍትህን አጉድሎ፤ነጻነቴን ገፎ እና አማራን እንደጠላት ቆጥሮ በዚህ አገር ላይ ከሰለጠነ ኃይል ጋር አብሬ ከምኖር ብሎ ራሱን በእሳት ያጋየውን መምህር የኔሰው ገብሬን የሚያከብሩትን ያህል ለእናንት ቅንጣት ታክል ክብር እንደሌላቸው እኔ እንግራችኋለሁ። እናንተን አቶ ሃዱሽ ሳይቀር ይንቋችኋል። ምክንያቱም እነርሱ የሚያምኑበትን ሲያደርጉ እናንተ ልታምኑ የማይገባችሁን አለቦታችሁ አለሰገባችሁ ተገኝታችሁ ለምትበሉትና ለምትጠጡት ስትሉ አንገታችሁን ደፍታችሁ መኖርን መርጣችኋል። ስለዚህ በእነርሱ ዘንድ ትናቃላችሁ በሌላው ዘንድ ደግሞ ትወገዛላችሁ።

እኔና ሌሎች አርባ አንድ ሠራተኞች ተባረን ጦም ማደር የጀመርነው እናንተ ዓይናችሁ እያየ ነው። መለስ ተ/ማሪያምም ተስፋ ቆርጦ ራሱን አንቆ የገደለውም በእናንተ ዓይነት አሳሞች ምክንያት ነው።

በነገራችን ላይ ከተባረሩት መካከል የሞተው መለሠ ተ/ማሪያም ብቻ አይደለም። አቶ አክሎግ እምሩም ሙቷል። የአማሟቱ ሁኔታ ግልጽ አይደለም። እንደተሰማው ከሆነ ተከራይቶ የሚኖርበት ቤት ውስጥ ሞቶ ተገኝቷል። አቶ አክሎግ እምሩ በውጭ ጉዳይ ሚንስትር ከአስር ዓመት በላይ አገልግሏል። አቶ አክሎግ እምሩ ከአስር ዓመት በላይ በውጭ ጉዳይ የሠራ ቢሆንም ከትምህርቱና ከሥራ ልምዱ ጋር የሚመጥን የሥራ ደረጃ ላይ አልነበረም። ምክንያቱ ደግሞ ከእለታት አንድ ቀን ሸራተን ይሁን ሂልተን ሆቴል ውስጥ ተደርጎ በነበረው ግብር ላይ አቶ አክሎግ ገስግሶ ሂዶ ስዩም መስፍንን “እኔን መቸ ነው የሚመድቡኝ ሲል ይጠይቀዋል” ሰዩምም እንዴት ደፍሮ እንዲህ ይጠይቀኛል ብሎ ቂም ቋጠረበት። ከዚያች ጥያቄ በኋላ አቶ አክሎግ እምሩ ከደረጃው ዝቅ ብሎ ወደ ማይመጥነው ቦታ ተመድቦ እንዲሰራ ተደረገ። ቅንጅት ሲመጣ ምክንያት ተገኘና ከተባራሪዎቹ አንዱ ሆኖ አረፈው። ከተባረረም በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሞቶ ተገኘ ተብሎ ሰማን። በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውስጥ ብዙ ሠራተኞች በድንገት ሞተዋል። ለምሳሌ ደሳለኝ ዓለሙ የዓለም አቀፍ ዳይሬክቶሬት ተ/ዋና ዳይሬክተር ሆኖ በመስራት ላይ እያለ መታመሙ ሳይሰማ ሞተ መባሉን ሰምተናል። አምሳሉ መለስም እንዲሁ በድንገት ሙቶ ተገኝቶቷል።

አሁን አሁን የገባኝ የህወሃት እና የሌሎች ኢትዮጵያዊያን ልዩነት የጭካኔና የሂሊና ጥያቄ ጉዳይ ነው። እነርሱ የጭካኔያቸው መጠን ልክ ሲያጣ እኛ የሚጨክን ልብ ማጣታችን። እኛ የሂሊናና የሞራል ጥያቄ ወጥሮ ይዞን ሰውስ እግዜርስ ምን ይለናል የምንል ሲሆን እነርሱ ከእነዚህ ነገሮች ጋር ፈጽሞ አለመተዋወቃቸው ነው።

እናም 42 ሠራተኞችን ለቃቅመው አባረሩ። እኔም የአገሪቷን አመራሮች ብቃት ትጠራጠራለህ ተብየ እንድባረረ ተፈረደብኝ። አንድ ጓደኛየም የተባረረበት ምክንያት ጠቅላይ ሚንስትሩን ሰድበሃል ተብሎ ነው። ምን ብሎ እንደተሳደበ ሲጠየቅ አንድ ቀን ተናድጄ ይሄ “ክፉ መላጣ”ብየዋለሁ ብሏል። ሌላውም የተባረረውም ከጓደኞችህ ጋር ስታወራ የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት “immature” ነው ብለሃል ተብሎ ነው።

ከዚህ በኋላ ልቤ ቂም እንደቋጠረ ተነሳሁና ወደ ወላጆቼ ክፍለ ሃገር ሄድኩ። ሁላችንም ተያይዘን ሃዘን ተቀመጥን። ምኞታችን ሲሞት፤ ተስፋችን ሲጨልም በራሳችን ላይ ትቢያ ነስንሰን ማቅም ለብሰን ሃዘን ብንቀመጥ የሚፈርድብን ይኖር ይሆን ?

ልጄ አንተንም አባረርሁ ሲል ተክዞ ጠየቀኝ አባቴ።

አዎን እኔንም አባረሩኝ።

አየህ እነዚህ ሰዎች እንዲመጡ ትንቢት ተነግሯል። እንደመጡም የሚሄዱበት ግዜም እንደሚመጣ ተነግሯል። ጉንዳኖች ናቸው። ጉንዳን ሲገባ ጸጥ ብሎ ይገባል የሚፈጅውንም ፈጅቶ በየት በኩል እንደሄደ ሳይታወቅ ይጠፋል።

ይህን ትንቢት ማን እንደተናገረው የሚታወቅ ነገር የለም። በአገራችን እንዲህ ያሉ ምንጫቸው ያልታወቁ ብዙ የታመኑ ትንቢቶች አሉ።

ልጄ አንተ በእግዚአብሄር ታምናለህ አለኝ አባቴ። አዎን በእግዚአብሄር እንድታምን ሆነህ ነው ያደከው። አንተ ከእነዚህ ሰዎች የምትለየው በዚህ ነው። አንተ በእግዚአብሄር ታምናለህ እነርሱ ግን አግዚአብሄር ከላይ ሁኖ ሁሉን እንደሚያይ ነገም እንደሚፈርድባቸው አይረዱትም። አንተ ከእነርሱ ከፍ ትላለህ። አዎን እነርሱ ከሰው ልጅነት ስብእና የወረዱ እንደ አራዊት ኑረው እንደአራዊት የሚሞቱ ናቸው። ልጄ ሌላ ክፍ ነገር እንዳታስብ።

እናቴ እንደተከዘች ከበርጩማዋ ቁጭ እንዳለች ደጅ ደጁን ትመለከታለች እንጂ አስተያየት አትሰጥም። ህወሃቶች አባት፤እናትንና ልጅን ባንድነት ያስለቅሳሉ ያሳዝናሉ። ከተባረርነው መካከልም አግብተው ልጅ ያላቸው የሚጦሯቸው አባትና እናትም ያላቸው አሉ። ህወሃቶች የሚያስለቅሱት ሁለት ትውልድን ብቻ ሳይሆን አያት፤አባትና የልጅ ልጅን ነው። ፕሮፌሰር መስፍን በአንድ ወቅት ሦስት ትውልድ በአንድነት ያለቀሰበት ዘመን ብለው መናገራቸው ይሄው በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ተገልጧል።

ይህችን ጦማር ስጽፍ አባቴ ዳግም ወደማይመለስበት ዓለም ሂዷል። የትንቢቱንም ፍጻሜ አላየም። እኔ የትንቢቱን ፍጻሜ አያለሁ ብየ ተስፋ እያደረኩ ነው። እንደ ጉንዳን እንደገቡ እንደ ጉም ብን ብለው እነደሚጠፉ እያሰብኩ በተሰፋ እየኖርኩ ነው። ተስፋየም እውነት እንዲሆን የምችለውን አደርጋለሁ።

እግዚአብሄር ከላይ ከሰማይ ሁኖ እንባችንና ሃዘናችንን ይመለከታል። ዝም አይልም። እኔም ዝም አልልም። ለሞት የሚያደርስኝ እንኳ ቢሆን እነዚህን ምናምንቴ ቡድኖች ግዜው ሲደርስ ከመፋለም ወደ ኋላ አልልም። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እግዜር ባኖረኝ መንገድ እየኖርኩ ነው። ስሜን አልናገርም። ለምን ብየ ጠላቶቼ የት እንዳለሁና ምን እንደምሰራ ይወቁ። የብእር ስሜን እነሆኝ። ነጻነት ለሁላችን ይሁን ነኝ።

ቸር እንሰንብት!!

ነጻነት ለሁላችን ይሁን ነኝ።