እንደ ምንጮቹ መረጃ እጩ ጳጳሳቱ አቡነ ማቲያስና አቡነ ጎርጎሪዎስ ከትግራይ፣ አቡነ ገሪማ ከሸዋ ናቸው።
በዘመነ የቤተክርስቲያን አባትነታቸው ሙሉ አወዛጋቢ ሆነው የኖሩት አቡነ ማትያስ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት የፕትርክና ዘመን፣ መንበራቸውን በመተው የኢዲዩ አባል በመሆናቸውና በሌሎችም በርካታ ምክንያቶች ተወግዘው “አቡነ ማቲያስ” የሚለውን መጠሪያቸውን ተነጥቀው እንደነበር የውስጥ አዋቂዎቹ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚም ሌላ እኚሁ አቡነ ማቲያስ ቤተክርስቲያኒቱ ከሶስት ቦታ እንድትከፈል ምክንያት ከሆኑት መካከል ግንባር ቀደሙ ሲሆኑ በአሁኑ ሰአት በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ናቸው – እንደ ምንጮቹ።
ሌላው እጩ አቡነ ጎርጎሪዎስ በአሁኑ ሰዓት የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሲሆኑ ለእጩነት የቀረቡት ከሟቹ አቡነ ጳውሎስ ጋር ባላቸው ቅርበትና ለወያኔ ስርዓት ባላቸው ታማኝነት መሆኑ ተገልጿል።
የመጨረሻው ከአቡነ ጳውሎስ ያልተናነሰ የማእረግ ስም ያላቸውና ” ዶክተር አቡነ ገሪማ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ዋና ጸሃፊ፣የቤተክርስቲያን የውጪ ግንኙነት ሃላፊ፣ የድሬደዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ” እየተባሉ የሚጠሩት ዋነኛው እጩ ናቸው።
በዓለማዊው ሹመት ሃይለማርያም ደሳለኝ የመለስን ሌጋሲ ለማስፈጸም እንደተመደበ ሁሉ እነኚህም
እጩዎች የአቡነ ጳውሎስን ሌጋሲ በማስፈጸም የወያኔን ስርዓት እንደሚያገለግሉ ታምኖባቸው የሚመደቡ ናቸው በማለት ሌሎች የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች እየገለጿቸው እንደሆነ የምንጮቹ መረጃ ያሳያል።
በሌላ በኩል አቡነ ጳውሎስ ከሞቱ በኋላ በአቃቤ መንበርነት የተሾሙት አቡነ ናትናኤል ለአራተኛው ጳጳስ አቡነ መርቆሪዎስ” ይድረስ ለብጹእ ወቅዱስ ፓትሪያሪክ አቡነ መርቆሪዎስ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ-ኢትዮጵያ” በማለት ደብዳቤ ከመጻፋቸውም በላይ በስደት የሚገኘው ሲኖዶስ ወደ ሀገር ቤት እንዲገባ መጠየቃቸውን በጎ ነው ያሉት የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች አቡነ ናትናኤል፣ ፓትሪያሪክ በህይወት እያለ ሌላ መሾም የለበትም ከሚሉ ወገኖች ጎን መሆናቸውን ይናገራሉ።