ባለፉት ሃያ አመታት ዉስጥ አንድም ቀን የተቃዉሞ ድምጽ አሰምቶ የማያዉቀዉ የወያኔ ፓርላማ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ለሹመት በላካቸዉ ዳኞች የብሔር ስብጥር ላይ ቀኑን ሙሉ ሲጨቃጨቅ መዋሉ ብዙዎችን እንዳስገረመ የግንቦት 7 ዘጋቢ ከአዲስ አበባ በላከው ዘገባ ገለጸ።
የወያኔ ፓርላማ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ መለስ ዜናዊ የላከለትን ሁሉ ያለምንም ክርክርና የሃሳብ ልዩነት ተቀብሎ ሲያጸድቅ እንደኖረ እየታወቀ ከሰሞኑ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ለሹመት የላካቸዉን ዳኞች የብሔር ስብጥር አስመልክቶ ያካሄደዉ የመረረ ክርክር መነሻው ምን እንደሆነ የህዝብ መነጋገሪያ ሆኖአል ያለው ዘጋቢያችን ከፓርላማው ውሎ ቦኋላ ያነጋገራቸው አንዳንድ የፓርላማዉ አባላት ሳይቀሩ በሁኔታው መገረማቸውን አክሎ ገልጾአል።
የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት አዛዥነት ቦታ ላይ ሲሰጡ የኖሩ ሹመቶችን፤ የካቢኔ ሚንስትሮችን ፤ አምባሳደሮችን የተለያየ የንግድና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ስልጣን እርከኖች ላይ የነበሩትን ሹመቶች አስመልክቶ አንድም አስተያየት ሰጥቶ የማያውቀው የወያኔ ፓርላማ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ለሹመት ባቀረባቸው 45 ዳኞች የብሄር ማንነት ላይ ሲነታረክ መዋሉ ምናልባትም አዲሱን ጠቅላይ ሚንስቴር ስልጣን ላለመቀበል ወይም ለመጋፋት የተወሰደ እርምጃ ሳይሆን አይቀርም የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ።
ያለፈው ሃሙሱን የፓርላማ ዉሎ በቅርብ የተከታተሉ ሰዎችን በይበልጥ ያስገረመዉ ፓርላማዉ አለልማዱ ሲከራከር መዋሉ ሳይሆን በትግራይ ልጅነት የተሰባሰቡ ጥቂት ስግብግብ ግለሰቦች ያሰኛቸዉን ሲሾሙና ሲሸልሙ ትንፋሽ ያልተነፈሰዉ ፓርላማ ዛሬ በጣት የሚቆጠሩ ዳኞች ሹመት የብሔር ስብጥር ሚዛናዊ አይደለም ማለቱ መሆኑን አዲስ አበባ ዉስጥ በየቦታዉ እየተዘዋወረ የህዝብ አስተያየት የሰበሰበዉ ዘጋቢያችን በላከልን ዜና ገለጾአል።
በተለይ አንድ በቅርቡ ከመከላከያ ሠራዊት የተሰናበቱ ከፍተኛ መኮንን ለዘጋቢያችን በሰጡት ቃል በቅርቡ ፓርላመዉ ባልተሰበሰበበትና አገሪቱን የሚመራ ጠ/ሚኒስትር በሌለበት ቦታ ከ38 ተሿሚ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ዉስጥ ለ25 የትግራይ መኮንኖች የተሰጠዉን አጠያያቂ ሹመት ጉዳይ መመልከት ያልፈለገዉ ፓርላማ በዳኞች ሹመት ጉዳይ ሲከራከር መዋሉ እጅግ እንዳሳዘናቸዉ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ዉስጥ የመከላከያ ሠራዊቱ፤ የፖለስ ሠራዊትና የድህንነት መስሪያ ቤት በመለስ ዜናዊ ግዜም ሆነ ዛሬ ሙሉ በሙሉ የሚመራዉ በትግራይ ተወላጆች መሆኑን የግንቦት ሰባት ድምጽ በተደጋጋሚ መዘገቡ አይዘነጋም።