በዘረኛውና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ እግር ለተተካው የወያኔ ጠቅላይ ሚንስትር ቤተመንግሥቱን እንድታስረክብ የተጠየቀቺው አዘብ መስፍን አስከዛሬ ድረስ ፈቃደኛ መሆን ባለመቻሏ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ቀድም ሲል ይኖርበት ከነበረበት ብስራተገብርዔል አካባቢ እየተመላለሰ ለመስራት መገደዱን ለማወቅ ተችሎአል።
አዘብ መስፍን ቤተመንግሥቱን የሙጥኝ ብላ አለቅም ያለቺበትን ምክንያት በቅርበት የሚያውቁ ምንጮች እንደገለጹት መለስ ዜናዊ በታዛዥነቱና በታማኝነቱ ለዚህ ሥልጣን ላበቃው ሃይለማሪያም ደሳለኝ ለ21 አመታት የኖረችበትን ቤትና ግቢ ለቆ መውጣት እንደመደፈር ቆጥራ ነው።
የመለስ ዜናዊን ከዚህ አለም በሞት መለየት ተከትሎ ህወሃት ኢህአደግ ውስጥ በተፈጠረው ክፍፍል የአዘብ መስፍን አንጃ የሆኑት በረከት ስሞን፤ ተፈራ ዋልዋና አዲሱ ለገሰ አዜብ ላልተወሰነ ጊዜ እዚያው ቤተመንግሥት ውስጥ እንድትቆይ ለሃይለማሪያም ደሳለኝ መመሪያ ሰጥተውታል ተብሎአል።
በዚህም ምክንያት ሃይለማሪያም ደሳለኝ ” ተጠናቂቄ ወደ ቤተመንግሥት ልግባ” የሚል ጥያቄ እስከዛሬ እንዳላነሳ ነገር ግን ጠቅላይ ሚንስቴር ከሆነ ወዲህ በተመደበለት ልዩ ጥበቃና አጀብ ከሚኖርበት ሰፈር ወደ ሥራ ሲወጣና ሲገባ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ በመፈጠሩ የአካባቢው ህዝብ የተሰማውን ቅሬታ ለማርገብ ለቤተመንግሥቱ ቀረብ ያለ ቦታ እንዲሰጠው ይህ እስኪሆን ድረስ የጥበቃው ጋጋታ እንዲቀንስለት ሰሞኑን ለበረከት ስሞን አቤት ማለቱን ታማኝ ምንጮች አያይዘው ገልጸዋል።
የሃይለማሪያም ደሳለኝን ከከተማ እየተመላለሰ መሥራት የታዘቡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ከአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር በስተጅርባ ሥልጣንን የሚቆጣጠረው ህወሃት ግለሰቡን በመሳሪያነት ብቻ ሊገለገልበት ሲል ነው የሾመው በማለት ጉዳዩን መነጋገሪያ እንዳደረገው ታውቆአል።
ይህ በዚህ እንዳለ ሰንደቅ የተባለው ጋዜጣ አዜብ መስፍን ቤተመንግሥቱን ለተተኪው ጠቅላይ ሚንስትር ለማስረከብ ፈቃደኛ ባለመሆኗ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶአታል ሲል የዘገበ ሲሆን
ማስጠንቀቂያው በማን እንደተሰጠና በማስጠንቀቂያው መሰረት ርክክቡ ባይፈጸም ምን እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ወይም ለአፈጻጸሙ የጊዜ ገደብ ይኑር አይኑር የገለጸው ነገር የለም።
ጋዜጣው አክሎም ሶስት መኖሪያ ቤቶች በተለዋጭነት ለአዘብ እንደተዘጋጀላት አንዱን መርጣ እንዲትገባበት ቢነገራትም ባልታወቀ ምክንያት ቤቶቹን ለማየት እንኳን ፍቃደኛ እንዳልሆነች ገልጾአል።
የሰንደቅ ጋዜጣን ዘገባ ዋቢ በማድረግ ተሰጣት ስለተባለው ማስጠንቀቂያ ከምንጮቻችን ለማጣራት ሞክረን በዙሪያዋ ባሉ ቱባ ቱባ ወያኔ ባለሥልጣናት ድጋፍ ማንንም ከመጠፍ ለማትቆጥር አዜብ ማስጠንቀቂያውን ሊሰጣት ማን እንደሚችል ጥያቄ እንደሚፈጥርባቸው ገልጸው ሆኖም ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በባላንጣነት የሚያይዋት የአቦስብሃት ቡድን ተገፍትራ ከቤተመንግሥቱ እንድተወጣ የማየት ጉጉቱ ቢኖራቸውም ተሰጣት የተባለውን አይነት ማስጠንቀቂያ የመስጠቱ ድፍረትም ሆነ ብቃት የላቸውም ብለዋል።