በወያኔ አገዛዝና በኦጋዴን ነፃነት ግንባር መካከል ናይሮቢ ዉስጥ ተጀምሮ የነበረዉ የአርቅ ንግግር ዉጤት አልባ ሆኖ መክሸፉን የወያኔ ባለስልጣኖች አመኑ

በኬንያ መንግሰት አስተባባሪነት እዚያዉ ኬንያ  ናይሮቢ ዉስጥ በወያኔ አገዛዝና በኦጋዴን ነፃነት ግንባር መካከል ተጀምሮ ሲካሄድ የነበረዉ የእርቅ ንግግር ያለ ምንም ዉጤት መጠናቀቁን አንድ የወያኔ አገዛዝ ቃል አቀባይ አዲስ አበባ ዉስጥ በሰጠዉ መግለጫ አሰታወቀ።

በጄኔራል መሐመድ ኡስማን ከሚመራዉ የኦብነግ አንደኛዉ ክንፍ ጋር በመከላከያ ሚኒስትሩ በሲራጅ ፈረጃ ተወክሎ ሲደራደር የነበረዉ የወያኔ አገዛዝ ለድርድሩ መክሸፍ ምከንያት የሆነዉ የኦብነግ ህገ መንግስቱን ተቀብሎ በህገ መንግስቱ ስር ለመስራት ፈቃደኛ አለመሆኑ ነዉ ያለ ሲሆን ኦብነግም በበኩሉ የወያኔ አገዛዝ ለዉይይት የማያመቹ ደንቃራ የሆኑ ቅድመ ሆኔታዎችን በመደርደር የጋራ ዉይይቱ እንዳይሳካ ሆን ብሎ ችግር ፈጥሮአል ብሎአል።

የዉይይቱን መርህ፤ ሞዳሊቲና አጀንዳ የቀረጸዉ የድርድሩ የመጀመሪያዉ ክፍል በአጥጋቢ ሁኔታ መጠቃለሉን የገለጹት የኦብነጉ አቶ አብዱራሂም ማህዲ ሁለተኛዉ ዙር ድርድር ሲጀመር የወየኔ አገዘዝ የገባዉን ቃል መስበሩንና ከዚህ በፊት እንደሚያደርገዉ ድርድሩን እሱ ወደሚፈልገዉ አቅጣጫ ብቻ ለመዉሰድ በመፈለጉ ዉይይቱን ለማቋረጥ ተገድደናል ብለዋል። የድርድሩን መቋረጥ አስመልክተዉ ለኢሳት ቴሌቪዥን ቃለ መጠይቅ የሰጡት አቶ አብዱራሂም ማህዲ አኛ የፈለግነዉ በእኩልነትና በመተማመን ላይ የተመሰረተ ዉይይት ሆኖ ሳለ ወያኔ ድርድሩን በእሱ የበላይነት እንዳሰኘዉ መምራት በመጀመሩ ያአሁኑን ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም ሊኖሩ የሚችሉ ዉይይቶችን አደናቅፏል ብለዋል።

የወያኔ አገዛዝ ከኦብነግ ጋር ዉይይት አደረግን ሲል ይህ የመጀመሪያ ግዜዉ አለመሆኑንና ከዚህ ቀደም ወያኔ ኦብነግ ጠመንጃዉን አስቀምጦ በሰላማዊ መንግድ አገር ለመገንባት ቅርጦ ተነስቷል ብሎ በተደጋጋሚ መለፈፉ ይታወቃል፤ ሆኖም ይህ በሆነ በጥቂት ቀናት ዉስጥ አጎዴን ዉስጥ አገዛዙ ከኦጋዴን አማጽያን ጋር የተኩስ ልዉዉጥ ማድረጉን አለም አቀፍ የመገናኛ አዉታሮች መዘገባቸዉ ይታወሳል።