የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት መርሀግብር በታዳጊ አገሮች ዉስጥ አካሂዶ በቅርቡ ይፋ ባደረገዉ ጥናታዊ ዘገባ መሠረት ኢትዮጵያ ማንበብና መጻፋ የማይችልዩ ሰዎች በብዛት ከሚገኝባቸዉ የመጨረሻዎቹ የአለም አገሮች ዉስጥ ከማሊና በቅርቡ ነጻነቷን ከተቀዳጀችዉ ደቡብ ሱዳን ቀጥላ በሦስተኝናት ደረጃ ላይ ትገኛለች ብሏል። በዚህ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት መርሀግብር ጥናት መሠረት ከአጠቃላዩ የኢትዮጵያ ህዝብ ዉስጥ ማንበብና መጻፍ የሚችለዉ 28 በመቶዉ ወይም 25 ሚሊዮን ህዝብ ብቻ እንደሆነ ታዉቋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዉስጥ በህዝብ ብዛት ሁለተኛ እንደሆነችና 90 ሚሊዮን ህዝብ እንዳላት መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በጥናቱ ዉስጥ ከተካተቱት 184 የአለማችን ታዳጊ አገሮች ዉስጥ ሁሌ ስማቸዉ በድህነት ተርታ የሚነሳዉ ኒጀር፤ ቡርኪናፋሶና ቻድ መሀይምነትን በማስወገድ ከኢትዮጵያ በላይ የተቀመጡ ሲሆን ኢትዮጵያ ከ184ቱ አገሮች ዉስጥ 182ኛ ደረጃ ላይ ተመድባለች። በዚህ ምደባ መሠረት ባለፉት ሃያ አመታት መንግስት አልባ ሆና የከረመችዉ ሶማሊያ የአፍሪካ የእድገት ምልክት ናት ተብሎ ከተሰበክላት ኢትዮጵያ ሁኔታ ህዝቧን ማስተማር መቸሏ የአለም ባንክንና ሌሎች እርዳታ ሰጪዎችን ጨምሮ ብዙዎችን እያነጋገረ ነዉ።
የወያኔ ባለስልጣኖች በተደጋጋሚ ጸረ ህዝብ ለመሆኑ በምሳሌነት የሚጠቀሙት የደርግ ስርአት እንኳን 60 በመቶ ኢትዮጵአዉያንን ከመሀይምነት በማላቀቁ አለም አቀፍ ሽልማት መሸለሙ የሚታወቅ ሲሆን ይህ ቁጥር ዛሬ ወደ 28 በመቶ ማሽቆልቆሉ የወያኔን የትምህርት ፖሊሲ ከፍተኛ ጥያቄ ዉስጥ ከትቶታል።ከፍተኛ የአሜሪካና የአዉሮፓዉ ህብረት ባለስልጣኖች ለኢትዮጵያ የሚሰጠዉ የዉጭ ብድርና ዕርዳታ አብዛኛዉ የሚዉለዉ ለጤናና ለትምህርት ዘርፎች ነዉ እያሉ ቢናገሩም ሀያ አመት ሙሉ የሰጡት ዕርዳታና ወያኔም በአስር እጥፍ አሳድግያለሁ የሚለዉ የትምህርት ተቋማት ብዛት መሐይምነትን ለመቅረፍ ያደረገዉ ምንም አስተዋጽኦ አለመኖሩ ብዙ ታዛቢዎችን ያሳሰበ ጉዳይ ሆኗል።