ወያኔ በሙስሊም ሃይማኖት ውስጥ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት ተወገዘ። በቀበሌ የተደረገው የሃይማኖት መሪዎች ምርጫ ተቃውሞ ገጥሞታል

አርብ ጥቅምት 9 ቀን በአዲስ አበባ፣ በደሴ፣ በከምሴ፣ በባቲ፣ በድሬዳዋ፣ በሃረር፣ በጅማ እና ሌሎችም በርካታ የኢትዮጵያ ከተሞችና ገጠሮች የሚገኙ ሙስሊሞች ተቃውሞዓቸውን አሰምተዋል። በአዲስ አበባ አንዋር መስጊድ የተገኘው ሕዝበ ሙስሊሙ ብዛት በመቶ ሺዎች የሚቆጠር መሆኑ በቦታው የነበረው ዘጋቢያችን ገልጾልናል።

የትናንትና አርቡ ተቃውሞ ወያኔ ያቀነባበረው የውሸት የመጅሊስ ምርጫ ተደረገ ከተባለ  ከመስከረም 27  ወዲህ የተደረገ የመጀመሪያ ታላቅ ሕዝባዊ ተቃውሞ መሆኑ ምሳሌነቱ ከፍተኛ ነው ተብሏል። የሕዝበ ሙስሊሙ በዚህን ያህል ብዛትና በመላው አገሪቱ ተቃውሞው ማሰማቱ መስከረም 27 የተደረገው ምርጫ የሕዝበ ሙስሊሙ ድጋፍ የሌለው መሆኑን አቢይ ምስክር ነው ተብሏል።

ዘጋቢያችን በአንዋር መስጊድ አግኝቶ ያነጋገራቸው አቶ ያሲን ከማል “ከምርጫው በላይ ያበሳጨኝ የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብዬ ኃይለማርያም ደሣለኝ ንግግር ነው” ካሉ በኋላ “ ‘ፍየል ከመድረሷ ቅጠል መበጠሷ’ እንደሚባለው አፉን በእኛ ላይ አሟሸብን” ብለውታል በቁጭት እየተንገበገቡ።

እንደ አንዋር መስጊድ ሁሉ በኑር መስጊድ የተገኘውም ሕዝብ እጅግ ብዙ እንደነበር የደረሱን መረጃዎች ያረጋግጣሉ።

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ለመብቶታቸው መከበር በተደራጀ ሁኔታ መታገል ከጀመሩ ዓመት ሊሞላቸው የተቃረበ ሲሆን በሰላማዊ መንገድ ለሚያቀርቡት ጥያቄ ወያኔ የሰጣቸው ምላሽ እስር፣ ድብደባ እና ዘለፋ ነው። በአገሪቷ ውስጥ ለእምነት መብታቸው በመቆማቸው ብቻ በሺህ የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ወደ ወህኒ ቤቶች ተወርውረዋል።

በሙስሊሙ ላይ የሚደርሰው የመብት ረገጣ እየከፋ በመጣ መጠን የሙስሊሙ ትግልም እየከረረና እየመረረ መጥቷል። በሣምንታት በፊት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ለወያኔ ቢጫ ቀለም ያለው ወረቀትና ፊኛ በማውለብለብ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸው ይታወሳል።

ሙስሊሙ ለሚያደርገው ሰላማዊ ትግል ተገቢውን ምላሽ እያገኘ ባለመሆኑ ትግሉ ከዚህም በላይ ሊከርና ሊመር እንደሚችሉ የፓለቲካ ተንታኞች እየተናገሩ ነው። እንዲያውም የዒድ በዓልን ምክንያት በማድረግ ትግሊ ከመስጊድ ወደ አደባባይ ሊወጣ ይችላል የሚል አስተያየት ተሰንዝሯል።

የአገራችን ሌላው አቢይ እምነት የሆነው የኦርቶዶክስ ክርስትና አማኒያንም በጳጳስ ሹመት ጉዳይ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል። ወያኔ በቀድሞው የወያኔ ጳጳስ ምትክ ሌላ የወያኔ ጳጳስ ለመተካት እያደረገ ያለው ጥረት በርካታ ክርስቲያኖችን እያበሳጨ ይገኛል። የቤተክነት ቀኖና ተጥሶ በጳጳስ ላይ ጳጳስ መሾሙ ሳያንስ አሁን ቀድሞ የተፈጸመው ጥፋት በማረም ፋንታ በጥፋት ላይ ጥፋት እየተደገሰ መሆኑ ክርስቲያኑን በእጅጉ አሳዝኗል።

ስለሆነም ሁለቱ የአገራችንና የዓላማችን ታላላቅ ሃይኖቶች ለመብቶቻቸው በጋራ የሚቆሙበት ሁኔታ ተፈጥሯል ይላሉ የፓለቲካ ሳይንስ ባለሙያዎች።

የኢትዮጵያ ክርቲያኖችና ሙስሊሞች ሲደጋገፉ መኖራቸው ያስታወሱ እነዚህ ባለሙያ ተንታኞች በተለይ አሁን በተፈጠረው ሁኔታ የሁለቱ ሃይማኖቶች አማኞች መደጋገፍና መቀራረብ ለአገራችን እድገት መልካም አጋጣሚ ሊፈጥር እንደሚችል ያላቸውን እምነት ይገልፃሉ።