ስብሐት ነጋ “የኢትዮጵያ ህዝብ ለድሞክራሲ ብቁ አይደለም” ሲል የጀርመን ሶሻል ዲሞክራሲ ፓርቲ ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ መናገሩ በስብሰባው ላይ የተገኙትን ኢትዮጵያዊያን ማስቆጣቱ ታወቀ

ከዚህ ቀደም በተለያዪ መድረኮች ላይ ኢትዮጵያ ዉስጥ በግለሰቦች ላይ ሳይሆን በሂደት ላይ የተመሠረተ አስተማማኝ ዲሞክራሲ ገንብተናል ብሎ ይፎክር የነበረዉ ስብሐት ነጋ የጀርመን ሶሻል ዲሞክራሲ ፓርቲ  በጠራዉ አለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ተገኝቶ “የኢትዮጵያ ህዝብ ለዲሞክራሲ ብቁ አይደለም” በሎ በመናገሩን ስብሰባው ላይ የተገኙ ኢትዮጵያዊያንን እንዳስቆጣ በርሊን የሚገኘው የግንቦት ሰባት ተባባሪ ዘጋቢ በላከልን ሪፖርት ገለጸ።

በዚህ ኢትዮጵያን፤ ኬንያንና ማላዊን አንደዋነኛ ተጋባዥ አደርጎ ባሰተናገደ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ የተገኘዉ ስብሐት ነጋ – በአንድ ሰዉ ሞት የተነሳ የድርጅት አላማ ሰለማይለወጥ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የፖሊሲ ለዉጥ አይኖርም ብሎ ከተናገረ በኋላ ንግግሩን ሲጨርስ “የኢትዮጵያ ህዝብ ለዲሞክራሲ ብቁ አይደለም” በሎ በመደምደሙ ዉይይቱን ለመከታተል አዳራሹ ዉስጥ ተገኝቶ የነበርው ቁጥሩ በዛ ያለ ኢትዮጵያዊ ቁጣውን በጩሄት በመግለጹ አስተናጋጆቹ እንደተደናገጡ ተያይዞ የደረሰን ዘገባ አመልክቶአል።

ስብሐት ነጋ አፋቸዉ እንዳመጣ ከሚዘላብዱና የኢትዮጵያን ህዝብ መሳደብ ከሚወዱ ወንጀለኛ የወያኔ መሪዎች አንዱ መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም የራሱን ጅልነትና ለህዝባችን ያለውን ንቀት በእንዲህ አይነት አለም አቀፍ መድረክ ላይ ይገልጻል ተብሎ እንዳልተጠበቀ በስብሰባው ላይ የተገኙ ኢትዮጵያዉያን ተናግረዋል። ስብሐት ነጋ ለህዝባችን ያለውን የንቀትና የእብሪት ንግግር ተናገሮ ሳይጨርስ በቁጣ ደማቸው የፈላ ኢትዮጵያዉያን ከመቀመጫቸዉ ብድግ ብለው ባንዳነቱንና በወያኔ የሥልጣን ዘመን ለተገደሉ ኢትዮጵያዊያን ተጠያቂ መሆኑን ጋባዦቹ ፊት በመናገር አዋርደውታል።

ስብሃት ነጋ ወያኔን በመምራት አገራችን ላይ ዘረኛ ሥርዓት እንዲነግስ ካደረጉ የህወሃት ቁንጮዎች አንዱ መሆኑን እየታወቀ ድህሬ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ አገራችን ወዴት ልታመራ እንደምትችል ለጀርመን የምክር ቤት አባላት በኢትዮጵያ አለም አቀፍ የሰላምና የልማት ኢንስቲቲዩት በእንግሊዘኛው አጠራሩ  Ethiopian International Institute for Peace and Development ሥም መጋበዙ በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ የሚከታተሉ ጀርመናዊያንን  አስገርሞአል።

በጀርመን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ አክቲቪስቶች የሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲው ስብሃት ነጋንና ሞገስ ተክለሚካኤል የተባሉትን ቱባ ቱባ የወያኔ ባለሥልጣናት ህወሃት ውስጥ ያላቸውን የሃላፊነት ድርሻ እያወቀ ገለልተኛ አስመስሎ መጋበዙን በመቃወም ደብዳቤ ያስገቡ እንደሆነና ስለኢትጵያ መጻዕ እድል የሚያሳስበው ወዳጅ አገር እንዲህ አይነት ስህተት ይሰራል ተብሎ እንደማይጠበቅ መግለጻቸውን ለማወቅ ተችሎአል።

ባለፈው ጥቅምት 9 በርሊን ላይ የተደረገውን ስብሰባ የመሩት አንድ የጀርመን ምክር ቤት አባል ይህንን ስብሰባ የጠራነዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ከመለስ ዜናዊ ሞት በኋላ ሊኖር የሚችለዉን ለዉጥ ለማወቅ ነበር፤ ሆኖም የኢትዮጵያው ተወካይ ምንም አይነት የፖሊሲ ለዉጥ አይኖረም በማለታቸዉ ኢትዮጵያን የሚመለከተዉ አጀንዳ ተዘግቷል በማለት ተስፋ መቁረጣቸውን ፊትለፊት ገልጸዋል።