የከሚሴ ከተማ የጦር ሜደ መሳሪያ ባነገቡ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ተወረረች – ደቡብ ወሎ ዉስጥ ዉጥረቱ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መምጣቱ ታወቀ

ባለፈዉ እሁድ የማምለክ መብታቸዉ እንዲከበር በሠላማዊ መንገድ ጥያቄ ባቀረቡ የእስልምና እምነት ተከታይ ዜጎች ላይ ተኩስ በመክፈት አራት ዜጎችን በግፍ የገደሉት የወያኔ ልዪ የጸጥታ ኃይሎች የሽብር ተግባራቸዉን በማስፋፋት የከሚሴን ከተማ ከብበዉ የከተማዋን ነዋሪ ህዝብ በማሸበር ላይ መሆናቸዉን ዝግጅት ክፍላችን ድረስ ስልክ እየደወሉ የድረሱልን ጥሪ ያቀረቡት የከሚሴ ከተማና የአካባባዉ ነዋሪዎች ገለጹ።

ይህ በያዝነዉ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በአማራ ክልል ቃሉ ወረዳ ገርባ ቀበሌ ዉስጥ የወያኔ ታጣቂዎች የጀመሩት የሽብር እንቅስቃሴ በፍጥነት ወደሌሎች አካባቢዎች በመስፋፋት ላይ መሆኑንና ነዋሪዉ ህዝብ ከተማዉን እየለቀቀ በብዛት ወደ ገጠር በመግባት ላይ መሆኑን ሁኔታዉን በቅርበት የሚከታተሉት የኢትዮጵያ ሳታላይት ዘጋቢዎች መግለጻቸውን ኢሳት ዘግቦአል።

እንደ ኢሳት ዘገባ ከፌዴራል ፖሊስ ከበባ አምልጠዉ በየጫካዉ ከተሸሸጉት ወጣቶች ዉስጥ አንዳንዶቹ ለዜና ማሰራጫው ስልክ በመደወል የከሚሴ ከተማ ብዛት ባላቸው የታጠቁ የወያኔ ፖሊሶች ስር መዉደቋንና ከቤት ወደ ቤት አሰሳ በማድረግ ወጣቶችን በማደን ተግባር መጠመዳቸውን አጋልጠዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ የወያኔ መከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አባላትን የጫኑ ካሚዮኖች በከሚሴና በደሴ አካባቢ በብዛት መታየታቸዉ የአካባቢዉን ህዝብ ክፉኛ እንዳስደነገጠዉ ለማወቅ ተችሏል። የዝግጅት ክፍላችን ከደሴ በስልክ ያናገራቸዉ አንድ አባወራ ወያኔ ጥያቄዎቻችንን የሚመለስዉ በጠመንጃ ብቻ ስለሆነ ልጆቻችንን ሊገድል ይችላል ብለን ብንሰጋም የወታደር ክምችትና የመሳሪያ ጋጋታ ለመብታችን ከመታገልና ጥያቄዎቻችንን ከማቅረብ በፍጹም አያግደንም ብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ መኖሪያ ቤቱ በፌዴራል ፖሊስ አባላት ሲከበብ በጓሮ በር ሸሽቶ ያመለጠ አንድ የከሚሴ ከተማ ነዋሪ ወጣት መንግስት ይዞ ያሰራቸዉን የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አመራር አባላትን አስካልፈታና የሙስሊሙን ህብረተሰብ የማምለክ መብት እስካላከበረ ድረስ ትግላችን ይቀጥላል ካለ በኋላ የሰሞኑ እስርና የግፍ ግድያ የብዙ አለም አቀፍ የዜና አዉታሮች አይን መሳቡና አለም አቀፍ ሽፋን ማግኘቱ እጅግ በጣም እንዳስደሰተዉ ተናግሯል።