በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ ትላልቅ ከተሞች ትናንት ለ1433ኛ ጊዜ ተከብሮ በዋለው የኢዲ አል አደሃ በአል ላይ የተገኘው ቁጥሩ በብዙ መቶ ሺ የሚቆጠር ህዝብ ወያኔ በሙስሊም እምነት ውስጥ የሚያካህደውን ጣልቃ ገብነት እንዲያቆምና ባለፈው ሳምንት በየቀበለው የተደረገው ምርጫ ህጋዊነት እንደሌለው በመግለጽ የተለያዩ የተቃውሞ መፈክሮች ሲስተጋቡበት መዋሉን ለማረጋገጥ ተችሎአል።
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የታላቁ የአንዋር መስጊድ አሰጋጅ የሆኑት ሼህ ጠሀ ሞሀመድ ሀሩን ምእመናን ምንም አይነት ተቃውሞ ሳያሰሙ ሰግደው በሰላም ወደየበታቸው እንዲሄዱ በመጠየቃቸው ወደ ተቃውሞ መግለጫነት የተቀየረው የአዲስ አበባው የበአል ሥነሥራአት በህበረተሰቡ ዘንድ እንዳይታወቅ ወያኔ ቁጥጥር ሥር የሚተዳደረው የኢትዮጵያ ቴለቪዥን በምስል የተደገፈ ምንም አይነት የዘገባ ሽፋን እንዳልሰጠው ታውቆአል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ግን ህዝቡ ያሰማውን ተቃውሞ በመደበቅ በአሉ በታላቅ ድምቀት እንደተከበረና ለድምቀቱም ዋናው ምክንያት በቅርቡ የእስልምና እምነት ተከታዮች ያካሄዱት የሃይማኖት መሪዎች ምርጫ በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መንገድ መጠናቀቁ እንደሆነ በመግለጹ የህዝብ ትዝብት አትርፎአል።
በአዲስ አበባ ስታዲዬም በተከናወነው የኢድ አል አደሃ በአል ላይ የተቃውሞ መፈክር ያሰማው የአዲስ አበባ ምዕመናን “መንግሥት የለም ወይ መንግሥት የለም ወይ በማለት ሥልጣን ላይ ያለው አገዛዝ መብታቸውን እንዳላስጠበቀ ሲገልጹ የኢትዮጵያ ቴለቪዥንንና በወያኔ ሞግዚትነት ሥር የሚተዳደረውን መጀሊስ ሥም እየጠሩ ሌባ ሌባ ሲሉ ተደምጠዋል። ወያኔ ሙስሊሙን አስገድዶ በቀበሌ ያካሄደው የሰሞኑ ምርጫም ህጋዊ አይደለም የሚል መፈክር በስፋት የተደመጠ ሲሆን አህባሽ አይመራንም፤ የታሰሩት ወገኖቻችን ተወካዮቻችን እንጂ ሽብርተኞች አይደሉም የሚሉና በአስቸኳይ እንዲፈቱ የሚጠይቅ መፈክሮችም በሰፊው ተደምጠዋል።
ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ በሀረር፣ በደሴ፣ በአዳማ፤ በጂማ እና ሌሎችም ትላልቅ ከተሞች በተካሄደው ስነ ሥር ዓት ተመሳሳይ የሆነ ተቃውሞ መሰማቱን የገለጹ ምንጮች በዘንድርው የኢድ በአል ላይ የሃይማኖት መሪዎችም ሆኑ የመንግሥት ተወካዮች ቀርበው ንግግር እንኳ ለማድረግ ድፍረት እንዳጡ መስተዋሉን ገልጸዋል።
ግንቦት 7 የሙስሊሙ ህብረተሰብ ያነሳው የመብት ጥያቄ አይነት በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሰሚ አጥቶ ተዳፍኖ የኖረ መሆኑን በማመልከት አገራችን ውስጥ የዜጎችን መብት ማክበር የሚችል መንግሥት እስካልተቋቋመ ድረስ ከእንዲህ አይነት የወያኔ ጥቃት የሚተርፍ እንደሌለ በማመልከት ህዝቡ ለራሱ ነጻነት የተጀመረውን ትግል እንዲቀላቀል ጥሪ ሲያደርግ መቆየቱ አይዘነጋም።