ወያኔ ታሪክን የማፍረስ ዘመቻውን ቀጥሏል!!

ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ ገና ከጫካ ሳይወጣ በስትራቴጂ ደረጃ የነደፈዉን ኢትዮጵያንና ታሪኳን የማጥፋት ዘመቻውን አሁንም እንደቀጠለ ነው። የወያኔ ዘረኞች የኢትዮጵያ ህዝብ የትግልና የመስዋዕትነት ምልክት የሆኑትን ጅግኖች ታሪክና የወያኔ አስራ ሰባት አመት የጫካ ትግል አሻራ ያላረፈባቸዉን ሰማዕታቶቻችንን የገድል ታሪክና ሀዉልት እያጠፋ በምትኩ የኔ ናቸዉ የሚላቸዉን የእነ አባ ጳውሎስን ዝከረ ሀውልትና የእነ መለስ ዜናዊን ምስሎች ብቻ በመዲናችን በአዲስ አበባ በማስቀረት፤ አዲስ አበባን የሀዝብ ሳይሆን የወያኔ ታሪክ ማስታወሻ እያደረጋት ነዉ። ወያኔ በላፈዉ አመት አጋማሽ ላይ በልማት ስም በታሪካዊዉ ዋልድባ ገዳም ላይ የጀመረዉን የአገር ታሪክና ቅርስ የማጥፋት ዘመቻ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ አልበገረም ባይነት ታሪክ ተምሳሌት የሆኑትን የሰማዕቱን የአቡነ ጴጥሮስን ሀዉልት የባቡር ሀዲድ እሰራለሁ በሚል ሰበብ ለማፍረስ በዝግጅት ላይ ነዉ። ይህ የወያኔ የጥፋት ዘመቻ ደግሞ እኛ ካላቆምነዉ በቀር የማንነታችን መገኛ አረአያ የሆኑትንና የአበውን ጀግንነት፤ አልበገርም ባይነትና እምቢተኝነት የሚስታውሱን ግዙፍ የታሪክ ማስታወሻዎቻችን የወያኔ ቡልዶዘሮች ሰለባ የሚሆኑበት ቀን ሩቅ አይደለም። ይህን ዘረኛ አገዛዝ በቶሎ ማሰወገድ አለብን ሰንል ግባችን እድገትና ዲሞክራሲ ብቻ ሳይሆን በወያኔ እየላላ ያለዉን አንድነታችንን ማጥበቅና ወያኔ በየቀኑ እያወደመ ያለዉን የታሪክ ቅርሶቻችንን በፍጥነት ማዳንና መጠበቅ ጭምር ነዉ።

የጣሊያን ፋሺስቶች አቡነ ጴጥሮስን “አርበኞች የሀዝብና የአገር ጠላት” ናቸዉ ብለዉ የሚያስተምሩ ከሆነ ዛሬዉኑ ከእስር ይፈታሉ ሲሏቸዉ አምላኬ ይህንን አላስተማረኝም ብለዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶች እነዚህ ፊት ለፊታችን የቆሙትና ከሩቅ አገር የመጡት ፋሺስቶች ናቸዉና የኢትዮጵያ ህዝብና መሬት ከእነዚህ ሀገር ቀሚዎች ስጦታ እንዳይቀበል” ብለዉ በህዝብ ፊት በጥይት ተደብድበዉ የሞቱ ጅግና ናቸዉ። ወያኔ የእኚህን ጀግና ሰዉ ታሪክ ሰበብ እየፈጠረ የሚያፈርሰዉ እንደም የእሱ አሻራ ስላላረፈበት በሌላ በኩል ደግሞ ህዝብ ይህንን ሀዉልት በተመለከተ ቁጥር የሚማረዉ አልበገርም ባይነትንና አልገዛም የሚል እምቢተኝነትን ስለሆነ ነዉ። ለዚህ ነዉ ወያኔ እንኳን በቁም ላሉት ሞተዉ ላንቀላፉት ጀግኖቻችንም የማይተኛዉ።  ወያኔን የመሰለ አገር በቀል ወራሪ ሀይልን ለአንዴና ለመጨረሻ እናጥፋ ሰንል እንደዚህ አይነቱን በማንነታችንና በታሪካችን ላይ የሚፈጸመዉን በደል ስር ከመስደዱና ትውልድን ከማጥፋቱ በፊት ለማስቆም ነዉ።

ወያኔ በተለመደ ቅጥፈቱ ሀውልቱ ተመልሶ ይመጣል እያለ የሚናገረው ህዝብን ለማዘናጋት እንጂ ከቶዉንም እውነቱን አይደለም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ እንደዚህ አይነቱን አይን ያወጣ ቅጥፍት ሃያ አንድ አመት ሙሉ አይቷል። ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን ቅጥፈታቸውን ተረድቶ በምንም ነገር ሳይታለል አባቶቹ አስቀምጠውለት የሄዱትን የታሪክ አሻራዎች የመጠበቅ ግዴታ አለበት። የነጻነት ታሪክ አሻራና ቅርስን እያፈረሱ የሚሰሩት ልማት ከቶ ጥፋት እንጂ ልማት አይደለም። ትላልቅና አጅግ ዉስብስብ ለሆኑ ችገሮች መፍትሄ ያለዉ የምህንድስና ሙያ አዲስ አበባን ያክል ትልቅ ከተማ ዉስጥ አንድ ሳይሆን በብዙ ሺ የሚቆጠሩ መንገዶችንና የባቡር ሀዲዶችን የታሪክ ቅርሶቻችንን በማይነካ መንግድ እንዲሰሩ ማድረግ ይችላል። የአቡነ ጴጥሮስ ሀዉልት የቆመዉ አቡኑ ያንን ታሪካዊ ንግግር ባደረጉበትና ፋሽስቶች በጥይት በደበደቧቸዉ ቦታ ላይ ነዉና የኢትዮጵያ ህዝብ በእሳቸዉ ሀዉልት ላይ የተነጣጠረዉን የወያኔ ጠመንጃ ማክሸፍ ግዴታ አለበት።

ህወአት/ወያኔ ውብ ታሪካዊ ቦታዎችን፣ መታሰቢያ ቅርሶቻችንን ከኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ ጋር የተያያዙ ናቸዉ ያላቸዉን ቦታዎች ሁሉ ከኢትዮጵያ ካርታ ላይ  እየፋቀ የአምባገነኑን የመለስ ፎቶ፤ የአባ ጳዉሎስ ሀዉልትና የከሀዲ ጄኔራሎችን ምስል እያስቀመጠ ነዉ። በአጠቃላይ የወያኔ ዘረኞች እዉነተኛዉን የኢትዮጵያ ታሪክ በእነሱ የዉሸትና የፈጠራ ታሪክ እየተኩ ነዉ። ይህ የጥፋት ዘመቻቸዉ ስር ከሰደደና መጪዉን ትዉልድ በዚህ ጥፋታቸዉ እየበከሉ የሚያሰተምሩ ከሆነ ጥፋቱን ማረም እጅግ በጣም ይከብዳልና የኢትዮጵያ ህዝብ ነገ ዛሬ ሳይል ወያኔ በያዘው የጥፋት ዘመቻ ላይ ሆ! ብሎ በመዝመት ታሪካችንን ና ሀገራችንን ከወያኔ አምባገነኖች መንጋጋ ማስለቀቅ ወቅቱ የሚፈልገው ግድ ነው። ይህን ባለማድረጋችን ደግሞ የታሪክ ተጠያቂዎች ያደርገናል።

በመጨረሻም ወያኔዎች ሊረዱት የሚገባቸዉ አንድ ሀቅ ቢኖር ግዜና ትውልድ እንደሚፋረደቸውና የጀግናውና የታጋዩ አቡነ ጴጥሮስ ሀውልት በማፍረስ ሀውልቱን እንጂ እሳቸዉ የተሰዉለትንትን አላማ ከቶ ሊያፈርሱት እንደማይችሉ ነው። ይህ የሚያሳየን ገድለ-ታሪክ ታሪክን አምጦ ወልዶ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ በጀግነነት ገድል ተጽፎ፣ ተቀልሞና ተከትቦ መቀመጡን ነው፤ ከዚህ በተጨማሪ ወያኔዎች ኢትዮጵያ ዉስጥ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ ለዘላለም ሲከበር የሚኖርን ትልቅ የጀግንነት ስራ፤ ሀውልትን በማፍረስ ማጥፋት አንደማይችሉ ሊረዱ ያገባል እንላለን። ይልቁኑ ሃውልቱን ለማጥፋት የሚቆፈረው ጉድጓድ የወያኔ ማንነት የመጨረሻ መቀበሪያ የሚሆንበት ግዜ ሩቅ አለመሆኑን እያንድንዱ የወያኔ አባልና ደጋፊ አበክሮ ሊገነዘበዉ ይገባል።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!