ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በሃይማኖት ላይ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት አጠናክሮ ቀጥሏል:: ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አሁንም የወያኔ ቀኝ እጂ ፓትሪያርክ እየተፈለገ ነው

ሁሉ ነገር ውስጥ ጣልቃ ካልገባ ሞቶ የሚያድር የሚመስለው የወያኔ ዘረኛ አገዛዝ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን በማጠናከር አዲስ ፓትርያርክ ለማስመረጥ አስመራጭ ኮሚቴ እንዲቋቋም ማድረጉን ከአዲስ አበባ ዘጋቢያችን በላከልን ሪፖርት ገለጸ። እንደ ዘጋቢያችን ሪፖርት የተወሰኑ ጳጳሳት ድርጊቱን በግልጽና በጽኑ የተቃወሙ ሲሆን በአስመራጭ ኮሚቴነት የተሰየሙት አባላት አብዛኞቹ የሟቹ አቡነ ጳውሎስ ቀን እጂ የነበሩ ሆድ አደሮች መሆናቸው ታውቋል።

ዘጋቢያችን እንዳለው ይህን የማናለብኝ ድርጊት ከተቃወሙት መካከል አቡነ ገሪማ፣አቡነ አትናቲዎስ፣አቡነ ቄርሎስ፣አቡነ ቀውስጦስና አቡነ ሉቃስ ይገኙበታል። በተለይም በቅርቡ በዩናይትድ ስቴትስ ተደርጎ በነበረው የእርቀ ሰላም ጉባኤ ላይ ተሳትፈው የተመለሱት አባቶች አስመራጭ ኮሚቴ ባቋቋመው በዚህ የሲኖዶስ ስብሰባ ላይ አልተሳተፉም።ቀሪዎቹም ረግጠው በመውጣትና በዝምታ ተቃውሟቸውን መግለጻቸውም ታውቋል።

ተቃውሟቸውን ከገለጹት አባቶች መካከል የዘጋቢያችን ምንጭ ያነጋገራቸው አንድ አባት በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል የተጀመረው የእርቀ ሰላም ውይይት አንዳች እልባት ሳያገኝ ወኪል ለማስቀመጥ  በወያኔ  በኩል የሚደረገው መሯሯጥ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸው ይህ የቤተክርስቲያኒቱን አንድነት ከመጉዳት ሌላ ለማንም፣ ለወያኔም ጭምር የሚያስገኘው ጠቀሜታ የለም ብለዋል።

ከቤተክርስቲያን ሲወጡ ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው አንድ ምእመን በበኩላቸው ይሄ መንግስት ስጋዊ ፍላጎታችንን አሟልተን እንዳንኖር ፖለቲካዊ አፈናና ኢኮኖሚያዊ ጫና እያደረሰብን ኑሯችንን የቁም ገሃነም ሲያደርግብን የየትኛውም ሃገር ህዝብ ሊታገሰው በማይችል ትእግስት ታገስነው፤ አሁን ደግሞ እሱ አልበቃ ብሎት በመንፈሳዊ ሃብታችን በሃይማኖታችን መጣ አሁንም እንደለመድነው ዝም ካልነው ሰው ከሚያሰኙ ባህሪያት ምን ሊቀረን ነው? በማለት አንስተው እርሳቸው ከእንግዲህ የወያኔ መንግስት ለማስወገድ ለሚደረገው ትግል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ለራሳቸ ቃል መግባታቸውንና የኢትዮጵያ ህዝብም ይህንን ዘረኛና የክፋት ምንጭ የወያኔ ስርዓት ለማስወገድ እንዲነሳ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል ያለው ልዩነት በሰላም ተፈቶ የቤተክርስቲያኒቱ  አንድነት እንዲጠበቅ ጸሎት እያደረጉ ባሉበት በዚህ ፈታኝ ወቅት ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ አገኛለሁ ብሎ ችግሩን ይበልጥ እንዲባባስ እያደረገ ባለው ዘረኛ፣ስግብግብና ጸረ-ሃይማኖት በሆነው የወያኔ መንግስት ላይ ቁጣቸው እየተባባሰ መምጣቱ ታውቋል።

የወያኔ አገዛዝ ወኪል ፓትርያርክ ለማስቀመጥ ይረዱኛል ብሎ ካስመረጣቸው የአስመራጭ ኮሚቴ አባላት መካከል ሶስት አራተኛው የአንድ ብሄረሰብ አባላት መሆናቸው የታወቀ ሲሆን ቀሪዎቹ  ደግሞ ለቀድሞው ፓትሪያርክ አቡነ ጳውሎስ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከቤተ ክህነት ወጪ እንዲሆን አድርገው ሃመር መኪና የመሸለምን ቀዳሚ ተግባር ሲያከናውኑ የነበሩ ህሊናቸውን የሸጡ ግለሰቦች መሆናቸውን ዘጋቢያችን ገልጿል።