የእሥርና እንግልት መበራከት የነጻነት ትግሉን ያጠናክራል እንጅ አያዳፍነውም!

pg7-logoበተለያየ ጊዜና ቦታ የሚኖሩ አንባገነን ገዥዎች በሙሉ ከሚመሳሰሉባቸው ባህሪያት አንዱ በሥልጣናቸው የሚመጣባቸውን ተቃወሚ ለማጥፋት በቁጥጥራቸው ሥር የሚገኘውን ማንኛውንም ዓይነት ሃይልና ጉልበት ከመጠቀም ወደ ኋላ የማይሉ መሆናቸው ነው።

የሌላውን አገር ትተን በአገራችን የታየውን የቅርብ ጊዜ ትውስታ ብቻ ብንመለከት ለወያኔ መፈጠርና ለድል መብቃት ምክንያት የሆነው ደርግ ለሥልጣኑ የሚያሰጉት የመሠሉትን ሁሉ መንጥሮ ለመጣል ከጅምላ እስርና ግርፋት እስከ ጎዳና የሽብር እርምጃ ብዙ ጉዳቶችን አድርሶአል ። አውሮጳና አሜሪካ ድረስ ተጉዘው ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ ቦኋላ ለአገራቸው ባላቸው ፍቅር የመልካም አስተዳደር ጉድለት በምድራችን ያስፈነውን ድህነትና ሃላቀርነት ከሥር መሠረቱ ለመቀየር ተስፋ ሰንገው ራዕይ ሰንቀው የተመለሱ በርካታ ወጣቶች ሳይቀሩ የሥልጣን ተቀናቃኝ ተደርገው እንደቅጠል እንዲረግፉ ተደርገዋል።

ከደርግ እስር፡ ግርፋትና ግዲያ አምልጠው መሳሪያ በማንሳት ደደቢት በረሃ የተሰባሰቡት የዛሬ ገዥዎቻችንና ነባር አባላቱ ምን ያህል ሠላማዊ ሕዝብ ህወሃትን ትደግፋላችሁ እየተባሉ እንደታሠሩ፤ እንደተገረፉ፤ እንደተገደሉና የቁም ስቅላቸውን እንዳዩ አሁን አሁን በምቾት ብዛት ዘንግተውት ካልሆነ በቀር ያኔ ትግል ላይ በነበሩበት ዘመን ነጋ ጠባ ሲያራግቡት የነበረ ጉዳይ ነው። በለስ ቀንቶአቸው የመንግሥት ሥልጣን ከተቆጣጠሩ ቦኋላም በተለይ በመጀመያዎቹ የድል አመታት ታስረው ሰቆቃ የተፈጸመባቸውን በቴለቪዥን መስኮት እያቀረቡ ብሶት ከማናዘዝ አልፈው የሟቾችን አስከሬን እያስቆፈሩ በማውጣት አለም ጉድ እስኪል ዘመድ አዝማድ ተሰባስቦ በእንባ እንዲራጭ አድርገዋል ። ይህንን ድርጊታቸውን የተመለከተ በርካታ ህዝብ ከአሁን ቦኋላ በአገራችን ምድር የሥልጣን ዕድሜ ለማራዘም ሲባል የሚታሠር፤ የሚገረፍ ሰቆቃ የሚፈጸምበትና ለሞት ወይም ለስደት የሚዳረግ አንድም ዜጋ አይኖርም ሲል ተስፋ አደርጎ ነበር።

ደርግ እስከነ ወንጀሉ ወደ ታሪክ ትቢያነት ከተቀየረ ቦኋላ ላለፉት 24 አመታት በዓይናችን እየተመለከትነው ያለው ገሃዱ እውነታ ግን፣ ሕዝብ ተስፋ ያደረገውና የጠበቀው ሳይሆን ግልባጩ ሆኖ በሌላ ዙር የአምባገነንነት የሃይል እርምጃ ሥር ቁም ስቅሉን እያዬ ነው። ድህረ ምርጫ 97 በአዲስ አበባና በሌሎች ትላልቅ ከተሞች አጋዚ በተባለ ልዩ ቅልብ ጦር የተፈጸመው የጅምላ ጭፍጨፋ ፤ በጋምቤላ አኝዋኮች ላይ የደረሰው አሳዛኝ የዘር እልቂት፤ በኦጋዴን ሱማሌዎች ላይ ላለፉት አመታት በተከታታይ እየደረሰ ያለው ሰቆቃ፤ በሠላም ከሚኖሩበት የደቡብ ክልል አማርኛ ተናጋሪዎችን ለማፈናቀል የተወሰደው የሃይል እርምጃ ያስከተለው መጠነ ሰፊ ጉዳት ፤ አንድን የህብረተሰብ ክፍል ከተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት ጋር በመፈረጅ በኦሮሚኛ ተናጋሪዎች ላይ የወረደው እስርና እንግልት ብዛት፤ በየማጉሪያው ተወርውረው ያሉት ጋዜጤኞችና የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች፤ የፖለቲካ ድርጅቶች አባላት ፤ ደጋፊዎችና መሪዎች ብዛት ወያኔ ከደርግ ያልተናነሰ እንዳውም በአንዳንድ መልኩ የባሰ አምባገነን ሆኖ መውጣቱን የሚያረጋግጡ፣ ማስረጃዎች ናቸው።

በርካታ የትግራይ ወጣቶች ግንባር ቀደም የህይወት መስዕዋትነት የከፈሉበት የእኩልነትና የፍትህ ትግል በጥቂት የህወሃት መሪዎችና የሥልጣን ጥቅም ተካፋዮቻቸው ተቀልብሶ ዜጎች ለነጻነታቸውና ለክብራቸው ሲሉ ወደ ሌላ ዙር ጦርነት እየተገፉ ባለበት በአሁኑ ሰዓት በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶችና ጎልማሶች ተቃዋሚን ትደግፋላችሁ በሚል ጭፍን ውንጀላ ወደ ተለያየ የማጎሪያ ካምፖችና እስር ቤቶች እየተጋዙ ስቃይ እየተፈጸመባቸው መሆኑን ማየትና መስማት ከማሳዘን አልፎ የሚያስቆጭ ተግባር ሆኖአል ።

ሥልጣን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ በምርጫ የሚያዝበትን ሥርዓት በአገራችን ለማስጀመር በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የሚንቀሳቀሱትን ሃይሎች የሚደግፉትን ለማሸማቀቅ በሽብርተኝነት ለመወንጀል የተደረገው ሙከራ ያልተሳካለት ወያኔ በምንም ማባበያ አልበገር ያሉትን በሺዎች የሚቆጠሩ አገር ወዳድ ዜጎችን በግንቦት 7 ሥም የዕድሜ ልክ ዕስራት ፈርዶባቸው በየዕስር ቤቱ እያማቀቃቸው ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አርበኞች ግንቦት 7ን ልትቀላቀሉ ነው በሚል ጥርጣሬና ስጋት ብዙዎችን ከድንበር አካባቢ እያገዘ ወደ ማጎሪያ ሥፍራው በማጓጓዝ የተለያዩ ድብደባና ማሰቃየት እየፈጸመባቸው ነው።

አርበኞች ግንቦት 7 ከራሳቸው የግልጥቅም የአገርንና የወገንን ክብርና ነጻነት አስቀድመው ሲንቀሳቀሱ በወያኔ እጅ ለወደቁትና በየእስር ቤቱ ተወርውረው የተለያየ አካላዊና መንፈሳዊ ሲቃይ እየደረሰባቸው ላሉ ወገኖቻችንን በሙሉ ከፍተኛ አክብሮት አለው። እነዚህ ወገኖቻችን የዚህ ወይም የዚያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት አባል ናቸው ሳይል ከአምባገነናዊ አገዛዝ እራሳቸውንና ወገናቸውን ለማላቀቅ ሲንቀሳቀሱ ለከፈሉትና በመክፈል ላይ ላሉት መስዕዋትነት ባለውለታነታቸው አጥንቱ ድረስ ዘልቆ እንደሚሰማው በይፋ መግለጽ ይወዳል። የእስርና እንግልት መበራከት የነጻነት ትግሉን እንዲፏፏም ያደርገዋል እንጂ እንደማያደናቅፈው ለአፍታም የማይጠራጠረው ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 አገራችንን ከፋሽስቱ የወያኔ አገዛዝ ለማላቀቅና ፍትህ እኩልነትና ነጻነት የሰፈነበት የበለጸገች አገር ለመመሥረት የጀመረውን ትግል አጠናክሮ በመቀጠል የወያኔ ሰለባ የሆኑትን ጀግኖቻችንን እንደሚታደግ በልበ ሙሉነት ያረጋግጣል።

በቃሊት፡ በዝዋይ፣ በቂሊንጡ፣ በሸዋ ሮቢት፣ በማዕከላዊና በትክክል በማይታወቁ ተለያዩ የወያኔ ማሰቃያና ማጎሪያ ቦታዎች በመሰቃየት ላይ ያላችሁ ሁሉ አረዓያነታችሁና ዋጋ እየከፈላችሁለት ያለው የነጻነት ትግል ከዳር እስኪደርስና አሳሪዎቻችሁና ገራፊዎቻችሁ ህግ ፊት ቀርበው የሥራቸውን ዋጋ እስኪያገኙ ለአፍታም ቢሆን እንደማናንቀላፍ ቃል እንገባለን።

በእሥርና በመንገላታት እየከፈላችሁት ያላችሁት መሰዕዋትነት የነጻነት ትግሉን ወያኔ እንደተመኘው ማዳከም ሳይሆን፣ እያጠናከረ መሄዱን ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!