በግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የጥናትና ምርምር ኮሚቴ የተዘጋጀ: ሐምሌ 2002
ስለ መተባበር ጠቀሜታ በመዘርዘር ጊዜ ማጥፋት አያስፈልግም። በአገራችን ለዘመናት የተንሰራፋው የግፍ አገዛዝ ያፋፋቸው እና እኛንም በዓለም ፊት እያዋረዱን ያሉት ድህነት፣ ችጋር፣ በሽታና ማይምነት ከመቸውም በላይ ህልውናችንን እመፈታተን ደረጃ ላይ የደረሱት ችግሮቻችንን ለመቋቋም ተባብረን መቆም ባለመቻላችን እንደሆነ አከራካሪ ጉዳይ አይመስለንም። እነዚህን ችግሮች ተባብረን ለማስወገድ የወስድናቸው ተግባራዊ እርምጃዎች ባለመኖራቸው ከዓመት ዓመት እየገዘፉ መጥተው ዛሬ ሊውጡን ደርሰዋል። ከዚህ በፊት በርካታ የመተባበሪያ መልካም አጋጣሚዎችን አባክነናል። ሌላው ሁሉ ቀርቶ ባለፉት አስራ ስምንት ዓመታት ውስጥ ከመተባባበር ውጭ ዘረኛውና አምባገነኑን ወያኔን በተበታተነ ኃይል ማስቆም እንደማይቻል ሁላችንም አውቀናል። የእብሪተኛው የጥቂቶች አገዛዝ ህልውና የቆመው “በከፋፍለህ ግዛ” መርህ መሰረት መሆኑን በተግባር አይተነዋል:: ለዚህም ነው ባለፉት አስር ዓመታት ኢትዮጵያዊያን በተሰበቡበት መድረክ ሁሉ “እባካችሁ ተባብረን እንቁም” የሚሉ የተማፅኖ ንግግሮች መስማት የተለመደ የሆነው። ነገር ግን የመተባበርን ጥቅም መረዳት ብቻውን መተባበርን አይፈጥርም። ሆድን የሚያባቡ “የእንተባበር” ተማፅኖዎች በተግባር እስካልተደገፉ ድረስ ውጤታማ አይሆኑም።
እርግጥ ነው በእነዚህ ዓመታት ከቃላት የዘለሉ የትብብር ሙከራዎች ተደርገዋል። የድርጅቶች ጥምረት ለመፍጠር ተሞክሮ ጥቂት እርምጃዎችን ተጋግዘን የተጓዝንባቸው ጊዜዓት ነበሩ። ሆኖም ግን የፈጠርናቸውን ጥምረቶች ዘላቂ እና ውጤታማ ማድረግ ባለመቻላችን እርቀው ሳይሄዱ ተደነቃቅፈው ወድቀዋል። ተጋግዘን ወደፊት ከተጓዝነው በላይ ተናቁረን ወደኋላ የምንመለስበት በመብዛቱ ሕዝባችን በብሩህ ተስፋ እና በተስፋ መቁረጥ መካከል እንዲንገዋለል ተፈርዶበታል። ጥምረቶቻችንን ዘላቂና ውጤታማ ማድረግ አልቻልንም። “ምንድነው የጎደልን?” ብለን ራሳችንን በጥብቅ መፈተሽ ይኖርብናል።
ሰሞኑን የመተባበር ጥሪ ከመቼውም በላይ ጎልቶ እየተስተጋባ ነው። ጥሪውን የጎላ ያደረገው ወያኔ ከዚህ ቀደም የማናውቀውን ባህርይ ስላሳየን ወይም የማንጠብቀውን ድርጊት ስለፈፀመ አይደለም። ወያኔ የፈፀመው ምን የማይታወቅና የማይገመት ነገር አለ? የሰሞኑን የመተባበር ጥሪ የቀሰቀሰው ወያኔ በቅርቡ ምርጫ ብሎ በከወነው ትዕይንት በፈጸመው ሸፍጥ የፓርላማውን ወንበር 99.6% በመውሰዱ ምክንያት ነው ብሎ መገመት የተሳሳተ ይመስለናል። ወያኔ ከዚህም የከፋ ነገር ከማድረግ የማይመለስ እኩይ መሆኑን ብዙዎች ኢትዮጵያዊያን እናውቃለን።
አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ያንገበገበው “በምርጫ 2002” አማካይነት ወያኔ ለሁላችንም በጉልህ ያስተላለፈው መልዕክት ነው። ንቀት!!! እጅግ አዋራጅ የሆነ ንቀት!!!! “የምርጫው” ሂደትና የተጠናቀቀበት መንገድ ወያኔ ለሁላችንም ያለውን ንቀት ያለምንም መሸፋፈን በአደባባይ የገለጸበት እብሪት ነው። ከወያኔ ጋር የገጠምነው ትንቅንቅ ከዴሞክራሲ፣ ከመልካም አስተዳደር፣ ከአገር ጥቅምና ደህንነት በላይ ተሻገሮ ሰው በመሆናቸን በእያንዳንዳችን ሰብዓዊ ክብር ዙሪያ የሚያጠነጥን መሆኑን መረዳታችን ነው ሰሞኑ ብዙዎቻቸንን በጋራ ቁጣ እንድንተሳሰር ያደረገን። ቸል ብለነውና ትተነው የነበረውን የጋራ ትግል ጥያቄ የቀሰቀሰው ይህ የያንዳንዳችንን አጥንት ዘለቆ የገባ እንደሰው በክብር ሳይሆን እንደሻገተ አተላ በወያኔ እየተደፋ ያለው ስብዕናችን ነው። “መረረኝ!!! አሁንስ በቃኝ!!! ከዚህ በኋላ ከወገኖቼ ጋር ተባብሬ ይህንን የግል ውርድት ማስቆም ይገባኛል!” የሚል እምነት ነው የዛሬውን የመተባበር ፍላጎት የሚገፋው። ዛሬ ሁላችንም ከሊቅ እስከ ደቂቅ ከደሃ እስከ ሃብታም፣ በአገር ውስጥ ሆነ በስደት ኗሪ በሙሉ ወያኔ ባሰረልን የባርነት እግረ ሙቅ መታሰራችን ፍንትው ብሎ እንዲታየን የተደረገበት ወቅት ነው። ይህ ሃቅ ነው እንግዲህ የመተባበርን ጉዳይ እንደገና ወደ መድረክ ገፍተሮ ያወጣው።
“ምርጫ 2002” ከመተባበር አስፈላጊነት በተጨማሪ ለመተባበር የሚያስቸሉ ሁኔታዎችን አመቻችቷል። የወያኔ እብሪተኛ ድርጊት ወያኔን እንቃወማለን በሚሉ ድርጅቶች መሃል በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የነበሩ ልዩነቶችን ትርጉም አሳጥቷቸዋል። የ2002 ምርጫ “ወያኔ ሊሻሻል ይችላል ወይንስ አይችልም?” “ወያኔን መታገያው ስልት ሰላማዊ ነው ወይንስ የአመጽ?” በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ የነበሩ መናቆሮችን አስቁሟል። ሁሉም በሚያመቸው የትግል ስልት እና እርስ በርስ በተደጋገፈ መንገድ ወያኔ ላይ በጋራ ከመነሳት የተሻለ አማራጭ እንደሌለ አሳይቶናል።
አሁን የቀረን “እንዴት አድርገን ነው ኃይላችንን፣ እውቀታችንን ገንዘባችንን አስተባብረን የወያኔን እድሜ የምናሳጠረው?” የሚለው አጀንዳ ብቻ ነው። በወያኔ መረገጥ የተማረረው ሕዝብም ሆነ የተቃዋሚ ድርጅቶች ካለፉ የመተባበር ተመክሮዎች በመነሳት “ጊዜው የሚጠይቀውን ጥብቅ ትብብር ለማሳካት እንዴት እንችላለን?” የሚል ጥያቄ ማንሳት ጀምሯል። የወደፊቱ ትብብር እንዳለፉት ትብብሮች የታለመለትን ግብ ሳይመታ እንዳይቀር ምን መደረግ ይኖርበታል በማለት መጨነቅ ጀምረዋል። የዚህ ጽሁፍ ዓላማ እነዚህን ጥያቄዎችና ጭንቀቶች ግምት ውስጥ ያስገባና በተወሰነ ደረጃ ለውይይት መነሻ የሚሆን መንደርደሪያ ሃሳብ ለማቅረብ ነው።
እንደ ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ እምነት፣ በደንብ ካሰብንበት፣ ከተዘጋጀንበትና ከደከምንበት የታለመለትን ግብ ሳይመታ የማይቆም በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ ድርጅቶቸና በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በአንድ ዓላማ ስር የሚተባበሩበት የፀረ-ወያኔ የተባበረ እንቅስቃሴ መፍጠር ይቻላል። ይህን የተቀደሰ ሃሳብ ለማሳካት ግን ብዙ ጥያቄዎችን አንስተን በአጥጋቢ ሁኔታ መመለስ ይጠበቅብናል። ይህ ጽሁፍ ስለመተባበርና ስለድርጅቶች ጥምረት ዋና ዋና ነጥቦችን ካነሳና የዓለም ዓቀፍ ልምድንም ከዳሰሰ በኋላ ወደአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በመመለስ እስካሁን ምን ተሰራ፣ ምን ጎደለ ? ወደፊትስ ምን ማድረግ ይጠበቅብናል? በሚሉ ነጥቦች ላይ ያተኩራል። የያዝነው ርዕስ ሰፊና ሞጋች ቢሆንም በጥቂት ገፆች ለመወሰን መጣራችንን ትገነዘቡልናላችሁ ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
ከላይ እንደተጠቀሰው ስለመተባበር ጥቅም ማውራት እምብዛም ፋይዳ የለውም፤ የታወቀ ነው። ይልቁንስ “ሰዎች የመተባበርን ጥቅም እያወቁ የማይተባበሩት ለምንድነው?” የሚለውን “እንቆቅልሽ” መፍታት እጅግ መሠረታዊ ጉዳይ ነው። ሰዎች መተባበር የማይፈልጉባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ። መተባበር ፈልገው እያለም ከመተባበር የሚያግዷቸው ሌሎች በርካታ ምክንያቶች አሉ። ሶስት ዋና ዋና ችግሮችን እናንሳ
ተባብሮ ለመሥራት ፍላጎትም ዝግጁነትም ኖሮ እያለ በአስተባባሪ እጦት ምክንያት ትብብር ተግባራዊ ላይሆን ይችላል። እዚህ ላይ “አስተባባሪ” ሲባል ሰውንም ተቋምንም ይመለከታል። የኅብረት ሥራ ህግ፣ ሥርዓትና ድርጅት ይጠይቃል። በጋራ የሚሠራ ሥራ ማን ምን እንደሚሠራ እና ሥራው መሠራቱ የሚቆጣጠረው ማን እንደሆነ ግልጽ ተደርጎ ካልተጀመረ “እንተባበር” ስለተባለ ብቻ ኅብረት አይመጣም። በስፖርት – ለምሳሌ – የቡድን አባላት በጨዋታው ዓይነትና ህግ መስማማት አለባቸው፤ ቀጥሎ ደግሞ ኃላፊነቶችን መከፋፈል ይኖርባቸዋል። ለእግር ኳስ የተገናባ ቡድን ለመረብ ኳስ አይሆንም። ግልጽ የሆነ ዓላማ፣ ደንብና መዋቅር የመኖሩ አስፈላጊነት በሁሉም የኅበረት ሥራዎች ውስጥ የማይቀር ነገር ነው። በዚህ ረገድ በስፓርትም፣ በእድርም፣ በፓለቲካ ፓርቲዎችም ዘንድ ያለው ችግር ተመሳሳይ ነው።
ይህ ችግር ለመፍታት የሚያስፈለጉ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች አመራርና /leadership/ እና ማኔጅመንት ናቸው። በዚህ ረገድ ባህል እጅግ ከፍ ያለ ሚና ያለው፤ በአጭር ጊዜ ለመቀየር የሚያስቸግር ነገር ነው። በባህል ጉዳይ ወደ ኋላ እንመለስበታለን።
የኅብረት ሥራዎች ትልቁ ችግር አብረው ለመቆም በተስማሙ አባላትና አካላት መካከል ያለው የመተማመን ደረጃ ለኅብረቱ ፍሬያማ ውጤት ወሳኝ የመሆኑ ክፋት ነው። በተወሰነ መጠን ቢሆንም እንኳን በገበያ (በኢኮኖሚ) ሳይተማመኑ መተባበር ይቻላል። በፓለቲካ ውስጥ ግን ሳይተማመኑ ለመተባበር ያለው እድል እጅግ የጠበበ ነው። “ያዛልቀኝ ይሆን?” ወይስ “ይክደኝ ይሆን?” የሚለው ጥርጣሬ በጋራ ሥራ ላይ ጊዜ፣ እውቀትና ሃብት ላለማፍሰስ ሰበብ ሊሆን ይችላል። የመተማመንን እጥረት ለማስወገድ የሚረዳ አስተማማኝ መፍትሄ ባይኖርም የሚከተሉት ነጥቦች ጠቃሚ ናቸው ተብሎ ይገመታል።
2.2.1. በተቻለ መጠን ሁሉም ተሳታፊዎች የኅብረቱ ተጠቃሚዎች ማድረግ፤
2.2.2. ለአባል ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ስምና፣ ክብር ከፍ ያለ ዋጋ መስጠት (ግለሰቦችም ተቋማትም የገነቡትን መልካም ስምና ዝና /reputation/ እንዳያጡ ለውሎች ታማኝ ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል)፤
2.2.3. ስምምነቶች ሁሉ በተቻለ መጠን በጽሁፍ እንዲሆኑ ማድረግ፤
2.2.4. መሪዎችን ውል የማፍረስ አቅም ማሳጣት። ውል በቀላሉ እንዳይፈርስ በመተዳደሪያ ማጥበቅ፤ እና
2.2.5. ትብብርን በትናንንሽና ለማስፈጸም ቀላል በሆኑ ጉዳዮች ጀምሮ ደረጃ በደረጃ ማሳደግ።
ከኅብረት ሥራ የጋራ ጥቅም ቢገኝም በግል የሚያመጣው ጉዳትም አለ። እያንዳንዱ ተሳታፊ ከጋራ ጥቅም ለመጠቀም፤ ከግል ጉዳት ደግሞ ለመሸሽ ቢጥር የሚገርም ሊሆን አይገባም። ይህ የተለመደ የሰው ልጅ ባህርይ ነው። እያንዳንዱ ሰው ጥቅምና ጉዳቱም ማመዛዘኑ ተፈጥሯዊ ነው። ለኅብረት ሥራ ይኸ ተቃርኖ ችግር የሚሆነው የሥራው ውጤት በልፋት መጠን ማከፋፈል በማይቻልበት ወቅት ነው። ብዙዎቹ የኅብረት ሥራ ውጤቶች ጭራሹኑ የማይከፋፈሉ ናቸው። በዚህም ምክንያት እያንዳንዱ ጭምት ነኝ ባይ ራሱ እያሸሸ በድካም የተገኘውን ውጤት ለመካፈል ግን ቀድሞ ተሰላፊ ይሆናል።
ይህ ችግር ውብስብስ በመሆኑ ቀላል መፍትሄ የለውም። የነፃነት ታጋዮች ከግል የጥቅም ፍላጎት እርቀው ለዓላማ የመቆምን መንፈሳዊ ጽናት ሲኖራቸው ብቻ ነው ይህን ምድራዊ ፈተናን መቋቋም የሚችሉት። የርዕዮት-ዓለም ጥቅሙ እዚህ ጋ ነው። ይህንን ፈተና ሊቋቋም የሚችል ምን ዓይነት ርዕዮተ ዓለም ሊኖረን ይገባል የሚለው ጉዳይ በጥልቀት ሊታሰብበት ይገባል።
ለሁሉም የትብብር ችግሮች መፍትሄ ማመንጨት ባንችልም ቢያንስ የችግሩን ጥልቀት አውቀን መነሳታችን ቀድሞ በገባንባቸው ጉድጓዶች ውስጥ ደግመን እንዳንገባ ያግዙናል።
ጥምረት የየራሳቸው ዓላማና ግብ ያላቸው የተለያዩ ቡድኖች በሚግባቡባቸው ጉዳዮች ላይ የሚሠሯቸውን ተግባራት ለማስተባበር የቆመ የቡድኖች ኅብረት ነው።
የቡድኖች ኅብረት የሚፈልገው በአንድ ቡድን ብቻ ሊሰሩ የማይችሉ ቢሰሩም ጥራታቸውና ተፈላጊነታቸው የሚጓደል ሥራዎች ስላሉ ነው። ስለሆነም ስለድርጅቶች ጥምረት ከመታሰቡ በፊት ጥምረቱ ያመጣዋል ተብሎ የሚገመተው ውጤት በአንድ ድርጅት ብቻ መምጣት የማይችል መሆኑን፤ ቢመጣም ተቀባይነቱ አነስተኛ መሆኑ በሁሉም ተጣማሪ ድርጅቶች ዘንድ የጋራ ግንዛቤ ሲኖር ነው።
የድርጅቶች መጣመር በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት::
የእነዚህና መሰል ጠቀሜታዎች መኖር ነው ድርጅቶች በየግላቸው ተሯሩጠው ከሚያመጡት ድል ድምር በላይ በጋራ ሲሆኑ ይመጣል የሚባለው። እንደ አገራችን ያለ በበርካታ ችግሮች ለተተበተበች አገር የጥምረት ጠቀሜታ ከዚህም በላይ ነው። ሎሚና ብርቱካንን መደመር እንደማይቻል ሁሉ የአንዱ ፓርቲ ድል ከሌላው ፓርቲ ድል ጋር የማይደማመሩ ሁለት ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። ስለሆነም የጋራ የሆነ ነገር (ለምሳሌ ስፕሪስ ጭማቂ) ላይ መስማማት ያስፈልጋል። ጥምረት ይህንን ወሳኝ የሆነውን ስምምነት መፍጠሪያ መድረክ ሆኖ ያገለግላል።
ይሁን እንጂ አጓጊ ጠቀሜታዎችን በማየት የድርጅቶች ጥምረት በችኮላ የሚደረግ መሆን የለበትም። ጥምረት የታወቁ ጉዳቶችም አሉት። ከሁሉ አስቀድሞ ጥምረት ድርጅቶች ከለመዱት አሰራር ስለሚያወጣቸው ውዥንብርና መደነጋገር የሚፈጥር መሆኑ ታውቆ ቅድሚያ ዝግጅት ሊደረግበት ይገባል። በዚህ ረገድ በቂ የሆነ ቅድመ ዝግጅት ካልተደረገለት የመጣመር ሙከራ ራሱ የቅራኔ ምንጭ ሊሆን ይችላል። በጠንካራ መሰረት ላይ ያልተገነባን ጥምረት ማቆየት ራሱን የቻለ ሥራ ይሆንና ሌሎች ሥራዎችን ያዘናጋል። ተጣምረው በተፋለሱ ድርጅቶች መካከል የሚኖረው ቅራኔ ከመጣመራቸው በፊት ከነበረው የባሰ ሊሆን ይችላል። ይህ በቅርብ ጊዜ ታሪካችን ውስጥ ያየነው ጉዳይ ነው። የጥምረቱ ድርጅታዊ መዋቅር በጥንቃቄ ካልተዘጋጀ ሥራዎችን በማፋጠን ፋንታ ሊያጓትት፤ ግብዓቶችን ቆጥቦ በመጠቀም ፋንታ ለብክነት ሊያጋልጥ ይችላል። በሁሉም የጋራ ሥራዎች ላይ ያለ “ልፋት ለሱ፤ ጥቅም የጋራ” ዓይነቱ የብልጣ ብልጥነት መርሆ በድርጅቶችም ላይ ያለ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ስለሆነም በጥምረት ውስጥ ያሉት ድርጅቶች ሁሉ እኩል ከልባቸው የአቅማቸውን ያህል ይሳተፋሉ ብሎ መነሳት የዋህነት ሊሆን ይችላል። ሁሉም ድርጅቶች እኩል ስለማይሳተፉ የአንዳንድ ድርጅቶች ሚና ከሌሎቹ ከፍ ሊል የሚችል መሆኑ ከመነሻው ሊታወቅ ይገባል።
ስለሆነም ጥምረት በሚገባ ተጠንቶ ደረጃ በደረጃ የሚደራጅ እንጂ ለመተባበር ወይም “አብረን ነን” ለማለት ብቻ የሚፈጠር ተቋም አለመሆኑ መረዳት እጅግ ጠቃሚ ነገር ነው ብለን እናምናለን:: ።
የጋራ ዓላማ ያላቸው ድርጅቶች በመተጋገዝ ፋንታ ሲጎነታተሉ ማየት አዲስ ነገር አይደለም። ሸሪኮች ሊሆኑ ይገቡ የነበሩ ድርጅቶች ባላንጣዎች ሲሆኑ ጉዳቱ ጥልቅና ሰፊ ነው። ስለሆነም ለጥምረት የሚደረገው ጉዞ መጀመር ያለበት ባላንጣነትን ወይም መጎነታተልን በማስቀረት ነው። የወዳጅ-ባላንጣ በብዙ ምክንያቶች ሊፈጠር ይችላል፤ ዋና ዋናዎቹ ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል።
በወዳጅ ድርጅቶች መካከል ያለው ባላንጣነት ለማስወገድ የስኬታማ ተግባቦት (effective communication) ክህሎቶችን ማዳበር ግድ ይላል። ከስኬታማ ተግባቦት ክህሎት ዋነኛው ደግሞ ከልብ ማዳመጥ መቻል ነው። ድርጅቶች በባላንጣነት የሚያዩዋቸውን ወዳጆቻቸውን ከልብ ማዳመጥን መልመድ ይኖርባቸዋል። ከልብ ለማዳመጥ ደግሞ በሌላኛው ድርጅት ዓላማዎች ላይ ፍላጎት ማሳደር ግድ ይላል። ግድየለሽ ተኩኖ ከልብ ማዳመጥ አይቻልም። ሌላው የመደራደር ፈቃደኝነት ነው። ድርድር ደግሞ በማግኘት ስሜት ብቻ አይደረግም። በድርድር አንድን ነገር ለማግኘት ሌላ ነገር ማጣትን ሊኖር እንደሚችል ማመን ያስፈልጋል። መልካም ድርድር ከመስጠትና መቀበል አልፎ የተሻለ ጎዳና ለማግኘት መጣርን ያካትታል። “ይህ ያንተ መንገድ አይደለም፤ የኔ መንገድም አይደለም። ለሁለታችንም የተሻለ ጎዳና ነው” ዓይነት ውጤት ነው የተሳካ የድርድር ውጤት የሚባለው። የምናልመው ጥምረት እንዲህ ዓይነቱ የተሻለ ጎዳና ላይ የሚያስቀምጠን ሊሆን ይገባል።
የጥምረት ዓይነቶች በርካታ ሲሆኑ ሶስቱን ከዚህ በታች እናያለን።
1. ድጋፍ ሰጭነት/Endorsement/
- ድርጅቶች ድጋፍ ለመሰጣጠት የሚያደርጉት ልል ጥምረት ነው
- ከድጋፍ ያለፈ እምብዛም የሚያደርጉት የለም
- ከመግባቢያ ሰነድ ያለፈ ስምምነትም ላይኖራቸው ይችላል
2. ዝምድና /ተዛማጅ/Associate/
- አባል ድርጅቶች ህያው የሆነ የጋራ ተሳትፎ ያደርጋሉ
- ሥራዎች ቢቀናጁም ውሳኔዎች ግን የግል ናቸው
- በዚህ ደረጃ ላይ የጥምረቱን ሥራዎች የሚያስተባብር ከአባል ድርጅቶች የተወጣጣ አካል እና ይህ አካል የሚተዳደርበት ቢጋር /terms of refernce/ ይኖረዋል።
3. ሽርክና /Partner/
- ውሳኔዎች የጋራ ናቸው። የጥምረቱ ውሳኔዎች በአባል ድርጅቶች ውሳኔ ላይ የበላይነት አላቸው።
- ሽርክናው ራሱን የቻለ ድርጅት ሆኖ በመቋቋም የድርጅቶች ጃንጥላ ሆኖ፤ የራሱን መዋቅር ዘርግቶ ይንቀሳቀሳል። አንዳንድ የሥራ ዘርፎች (ለምሳሌ ራስን የመከላከል ሥራ፣ የውጭ ግኑኝነት፣ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች) ሙሉ በሙሉ ለሽርክናው ሊተው ይችላሉ።
የትኛው የጥምረት ዓይነት ይሻላል የሚለው ጥያቄ የሚወሰነው ለሚከተሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች በሚሰጥ ምላሽ ነው።
ሀ) አባል ድርጅቶች ምን እንዲያደርጉ ነው የሚጠየቁት?
ለ) እያንዳንዱ አባል ድርጅት ከጥምረቱ ምን እና እንዴት ይጠቀማል?
ሐ) የእያንዳንዱ አባል ድርጅትና አቅምና ዝግጁነት ምን ያህል ነው?
ሁሉም ድርጅቶች በእኩል ደረጃ ላይ ሊገኙ ስለማይችሉ ሶስቱንም የጥምረት ዓይነቶች እንደሁኔታው የምናስተናግድበትን ብልሃት መፍጠር ይኖርብናል።
በታሪክ ውስጥ የሚጠቀሱ አንዳንድ ትብብሮችና ጥምረቶች ለማመን የሚቸግሩ ውጤቶችን አስገኝተዋል። በአንዳንድ ሁኔታዎች በመሣሪያ ሊገኝ ከሚችል ድል በላይ በተቃዋሚ ድርጅቶች ተባብሮ መቆም ብቻ ሊገኝ ይችላል። ለምሳሌ ያህል የምከተሉትን ማንሳት ይቻላል።
4.1 በእንግሊዝ በ1688-1689፤ በስዊድን በ1909 በፍላጎትም በርዕዮተ-ዓለምም የማይቀራረቡ የመሳፍንትና የቡርዧ ቡድኖች ተደራድረው በፈረንሳይ የፈነዳውን ዓይነት ማኅበራዊ ነውጥ ሳያስፈልግ ለሥርዓት ለውጥ በቅተዋል።
4.2. በኮሎሚቢያ 1957-1958 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኅብረት ፈጥረው በመፈርጠማቸው የተደናገጠው በሥልጣን ላይ የነበረውን ቡድን ግማሽ የመንግሥት ሥልጣኑን በመልቀቅ የፕሬዚዳንትነት ሥልጣን ከተቃዋሚዎች ኅብረት ጋር በፈረቃ ሊለዋጥ ተስማምቷል።
4.3. በተመሳሳይ ሁኔታም በቬንዙዌላ በ1958 ተቃዋሚዎች የፈጠሩት ሰፊ መሠረት ያለው ኅብረት ሥልጣን ያለውን ፓርቲ አርበድብዶ አነስተኛ በሆነ መስዋትነት ሥልጣኑን እንዲለቅ ማድረግ ችለዋል።
4.4. በ1989 የፓላንድ የሙያ ማኅበራትና ሌሎች የፓለቲካና ማኅበራዊ ስብስቦች በሙሉ “ከሶሊዳሪቲ” ጎን በመቆማቸው ኮሚኒስት ፓርቲው ራሱን ለማዳን እንዲደራደር ማስገደድ ችለዋል። በተመሳሳይ ጊዜ ተመሳሳይ ነገር በቼኮዝላባኪያ ውስጥም ተከስቷል።
4.5. በ1994 በደቡብ አፍሪካ በኤኤንሲ ግንባር ቀደም መሪነት የተካሄዱ ጥምረቶችና ድርድሮች እጅግ ውስብስብና አስደናቂ ጥበብ የተሞላባቸበው ነበሩ። በተለይም እነዚህን ድርድሮች በዝርዝር ማጥናት እኛ ለምንገኝበት ሁኔታ ከፍተኛ ፋይዳ አላቸው ብለን እናምናለን።
ከላይ የተዘረዘሩት እና የመሳለሉ ክስተቶች በጣም አልፎ አልፎ ብቻ የሚያጋጥሙ ብርቅየዎች ከመሆናቸም በላይ እያንዳንዱ ክስተት ከበርካታ ዓለም ዓቀፍ እና አገር ዓቀፍ ሁኔታዎች የተሳሰሩ ነበሩ። ስለሆነም አንዳቸውንም መድገም አይቻል ይሆናል፤ ሆኖም ግን እያንዳንዱ ምሳሌ የአብሮ መቆምን ጉልበት አጉልተው ያሳያሉ።
በአገራቸን ታሪክ በፖለቲካ መስኩ የተደረጉ ብዙ የመተባበር ሙከራዎች አሉ። እነዚህን ሙከራዎች በሶስት አይነት መክፈል ይቻላል። የመጀመሪያው አንድ ተጽእኖ ማድረግ በሚችል ድርጅት ዙሪያ የተወሰነ የራሳቸው ነፃነት ያላቸው ነገር ግን አቅማቸው ደካማ የሆኑ ድርጅቶች የፈጠሩት ትብብር ነው። ሁለተኛው አቅማቸው ተመጣጣኝ የሆኑና ተመጣጣኝ ያልሆኑ ነገር ግን አንዳቸው በሌላው ላይ ተጽእኖ ማድረግ የማይችሉ የነፃ ድርጅቶች ትብብር ነው። ሶስተኛው አንድ ጠንካራ ድርጅት ምንም ዓይነት ነፃነት የሌላቸውን ድርጅቶች በማሰባስብ ፈጠርኩ የሚለው ትብብር ነው።
ለመጀመሪያው ዓይነት ትብብር በደርግ/ሰደድና በሌሎቹ ኢማሌድህ በተሰኘው ስብስብ ውስጥ አባል በነበሩት ድርጅቶች መሃል ተፈጥሮ የነበረው ኅብረት ምሳሌ መሆን ይችላል። ለሁለተኛው አይነት ትብብር ምሳሌ መሆን የሚችሉት ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ወያኔን ለመቃወም ተቋቁመው የነበሩትን ትብብሮች ይመለከታል። የአማራጭ ኃይሎች ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ሕብረት (ኢተፖድሕ)፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ሕብረት (ኢዲኃሕ)፣ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ (ቅንጅት)፣ ትብብር ለነፃነትና ለዴሞክራሲ በሚል ስያሜ የሚታወቁት ትብብሮች የሁለተኛው ዓይነት ትብብር አገራዊ ምሳሌዎች ናቸው። ሶስተኛው አይነት ትብብር በስሙ ካልሆነ በስተቀር በመሠረቱ ትብብር አይደልም። ለእንዲህ አይነቱ “ትብብር” ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው በወያኔ የሚዘወረው ኢህአዴግ ነው።
እነዚህ የትብብር ሙከራዎች በሙሉ በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ሊሳኩ አልቻሉም። የወያኔው ኢህአዴግ ዓይነቱ ትብብር መጀመሪያውኑ ሲታሰብ ወያኔ የራሱን ጡንቻ ካፈረጠመ በኋላ ለረጅም ግዜ ታጥሮ ከኖረበት ትግራይና የትግራይ ሪፐብሊክ ምስረታ ህልሙን በጉያው ሸጉጦ ወደ መሃል አገር ለመገስገስ ያለውን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ሲል እራሱ ጠፍጠፎ ከፈጠራቸው ድርጅቶች ጋር የተመሰረተ በመሆኑ ትብብር ከሚለው ጎራ መመደቡ ተገቢ አይደለም ይባል ይሆናል፤ ይህ አባባል እውነት ነው። ይሁን እንጂ በኅብረት ስም እንደምን ያህል ነውር እና ወንጀል መፈጸም እንደሚቻል ኢህአዴግ ምሳሌ በመሆኑ እዚህ ላይ መጠቀሱ ተገቢ ነው እንላለን።
የወያኔ የባህል ዝንባሌ ሃገር በቀል በመሆኑ ሌሎችም ድርጅቶች ቢሆኑም ለብቻቸው ስልጣን መያዝ ባይችሉ፣ አቅሙና ሁኔታው እስከፈቀደላቸው ድረስ ነፃና እኩያቸው ከሆኑ ድርጅቶች ጋር እውነተኛ ትብብር ከማድረግ ይልቅ በድብቅ ራሳቸው ከፈለፈሏቸው ወይም ከሚቆጣጠሯችው ድርጅቶች ጋር ትብብር አደረግን ማለት የሚመቻቸው ለመሆኑ ጠቋሚ ነው። ትብብር የሚደረገው ልዩነት ባላቸው ኃይሎች መሃከል ያለውን ቅራኔ አስወግዶ ለሁሉም የሚመች መንገድ ለመፈለግ መሆን ሲገባው የተለጣፊ ድርጅቶች “ትብብር” በመፍጠር የራስን አጀንዳ በሌሎች ችከሻ ማስፈፀም በመጨረሻ ለብልጣብልጡ ድርጅት ሳይቀር ችግር እንደሚፈጥር ከወያኔ የጥፋት ታሪክ መማር ተገቢ ነው። “ኢህአዴግ” እያለ ወያኔ የሚጠራውን የወሮበሎች ተቋምን በትብብር ምሳሌነቱ ማንሳት ተገቢ የመሰለንም በተመሳሳይ መንገድ ትብብርን ለአንድ ድርጅት ጠባብ ዓላማ የማዋል ዝንባሌ ከወያኔም ውጭ ይኖራል ብለን ስለምናምን ነው ።
የኢማሌድህ ትብብር በሰደድ አሽናፊነት መጠናቀቁ ብዙም ሊገርመን አይገባም። የትብብሩ ዓላማ የመድበለ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር ሳይሆን የሠራተኛውና የአርሶ አደሩን ጥቅም የሚያስከብር አንድ ሶሻሊስት ፓርቲ መመስረት ስለነበር ሰደድ ሁሉንም ጨፍለቆ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) ብቸኛ ጌታ ሆኗል። በዚህ ምሳሌም ውስጥም ቢሆን ጠቃሚ ትምህርት የለም ማለት አይደልም። ሥርዓቱ የሚያዘው በአንድ አገር አንድ ፓርቲ ብቻ እንዲኖር ቢሆንም በጋራ ለዚህ ፓርቲ መመስረት መሰባብ የጀመሩ ድርጅቶች እርስ በርስ ሳይባሉ ተከባብረወና ተስማምተው ራሳቸውን አንድ ማድረግ አለመቻላቸው ራሱ የሚሰጠን ትምህርት አለ። እንዲህ አይነቱ መጠፋፋት የርዕዮተ-ዓለም ልዩነት በሌላቸው ድርጅቶች መካከል ሊፈጸም ከቻለ የርዕዮተ-ዓለም ልዩነት አለን በሚሉና የየራሳቸውን አደረጃጀት ይዘው በሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች መካከል በመከባበርና በስምምነት ላይ የተመሰረት የትግል ኅብረት ለመፍጠር የሚኖረውን ችግር ጥልቀት መረዳት አያስቸግርም። ይህ እውነታ የሚያሳየን በኢትዮጵያ ውስጥ በጋራ ለመስራት የሚደረጉ ጥረቶች እንዲሳኩ የድርጅቶች የዓላማና የፖሊሲዎች ተመሳሳይነት ብቻውን በቂ እንደማይሆን ነው።
ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላም የተደረጉ በርካታ ተባብሮ የመስራት ሙከራዎች መሰናከል ምክንያቶች እንደ ትብብሮቹ ሁሉ በርካታ ናቸው። ችግራችን ግን በዋንኛነት ስለ ወያኔ ምንነትና ማነነት፣ ወይም በተለያዩ ፖሊሲዎች ላይ ካለን ልዩነት የመጣ አይደለም። ኢማሌድህ ውስጥ ሰደድ ሁሉንም ውጦ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምን ብቸኛ አዛዥ እንዳደረገ ሁሉ፤ ወያኔም ተለጣፊዎቹን አሰባስቦ የመለስ ዜናዊ የግል ተላላኪ አድርጎ እንዳሰማራ ሁሉ፤ ግላዊና ማኅበራዊ ስነልቦናችን እንዲሁም ባህላችን ሁሉንም ጠቅልሎ ለመቆጣጠር ፍላጎት ያላችው የፖለቲካ ሰዎችን የሚያመርት መሆኑ ከወያኔ በኋላ ለተሞከሩት ትብብሮች ውድቀት ዋነኛው ምክንያት ነው። የፖለቲካ ሰዎች ለላቀ አገራዊና ሕዝባዊ ጠቀሜታ ሲሉ እኔ ብቻ ያልኩት ካልሆነ፣ የኔ ድርጅት ይህንን ስልጣን በትብብሩ ውስጥ ካልተስጠው፣ የኔ ድርጅት የተለየ ጠቀሜታ ካላገኘ በሚሉ ድብቅ ፍላጎቶች የሚነሱ ተግባራትን መቆጣጠር ባለመቻላቸው እነዚህ ትብብሮች ለመፍረስ ችለዋል። ምክንያቶቹ ግን እነዚህ ብቻ ናቸው ግን ማለት አይደለም።
ከወያኔ ስልጣን ላይ መውጣት በኋላ ለተሞከሩ የትብብር ምስረታዎች መክሸፍ ኋላቀር አመለካከታችን ያሳደረውን ተጽዕኖ የሚያሳዩ ሌሎችን በማስረጃ የተደገፉ በርካታ ምሳሌዎች ማቅረብ ይቻላል። ሆኖም ክርክራችንን በማስረጃ ብናስደግፍም እንኳን በግለሰቦችና በድርጅቶች ላይ የተሰንዘረ ጥቃት መስሎ ስለሚታይ ሊፈጠር ይገባል ብለን ለምናልመው አዲስ የትብብር ጅማሮ እንቅፋት ይሆናል በሚል ስጋት በዝርዝር ልንገባበት አንሻም። ስለሆነም እገሌን ከእገሌ ባልለየ መልኩ ጉድለቶቻችንን ለይተን በማየት ለወደፊቱ የሚሆን ትምህርት ለመቅሰም በሚያበቃን መጠን ብቻ ጥቂት ምሳሌዎችን እናነሳለን።
“ትብብርን” ተጠቅሞ የራስን ድርጅትና ሌሎችን በእኩልነትና በመግባባት ለማስተናገድ ፈቃደኛነቱ ያልታየባቸው ሁኔታዎች ለትብብር መፍረስ ምክንያት ሆነዋል። ትብብር የሚል ቃል ተጠቅሞ ሊተባበሩ ፍላጎቱን ባሳዩ ኃይሎች መካከል ከዚህ ቀደም የነበረ ግጭትና መቃቃር መልሶ ሕይወት እንዲዘራ በማድርግ በትብብሩ ውስጥ የተካተቱ ኃይሎችን በቂምና በጥላቻ ዓይን ማየት፣ የግለሰቦችንና የድርጅቶችን ስም በመርዘኛ ወሬና አሉባልታ ማጥፋት ሌላው ችግር ነው።
ትብብርና ቂም፣ ትብብርና ጥላቻ፣ ትብብርና ንቀት፣ ትብብርና ሸፍጥ፣ ትብብርና ግለኛነት አንድ ላይ ሊሄዱ አይችሉም። ያለን ምርጫ ከሁለት አንድ ብቻ ነው። እነዚህ ሁለት ምርጫዎች ወይ ቂማችንን፣ በቀለኛነታችንን ጥላቻቸንን፣ ንቀታችንን፣ ግለኛነታችንን ታቅፈን ሁላችንም በተናጠልና በጋራ መለስ ዜናዊን የመሰለ ፀረ-ኢትዮጵያ ዘረኛ አዋርዶና ቀጥቅጦ እንዲገዛን እና በብዙ መስዋዕትነት ቀድምቶቻችን ያኖሯትን ሃገር እንዳሻው እንዲዘርፍና እንዲያፈርስ መፍቀድ አልያም ለመተባበር እንቅፋት የሆኑትን ባህላዊና ስነልቦናዊ እንከኖች ከውስጣችን መጥርግና ለነፃነት፣ ለፍትህ፣ ለእኩልነትና ለአንድነት በጋራ መቆም ናቸው።
ያነሳነው ችግር ስር የሰደደ የባህል ችግር ነውና “እባካችሁ እናጥፋው” በሚል ሰበካ ብቻ ሊጠፋ እንደማይችል እናውቃለን። ነገር ግን ችግሩ እንዳለ እስካወቅን፣ በተለይ ችግሩ ሁላችንም ይመለከታል ብለን ለመፍትሄ ከጣርን እድሉን ካገኙ አገርን የመምራት ብቃት እንዳላቸው ለሚናገሩ የፖለቲካ መሪዎች የሚሳን ሊሆን አይገባውም። ሆኖም ግን ይህንን ችግር ለመቅረፍ ራሳቸንን እንመርምር ከሚል ተማጽኖ በላይ ተሻግረን ያለፉ ትብብሮችን ያሰናከሉ ችግሮች ደግመው እንዳይከሰቱ መዋቅራዊና መርሃዊ መከላከያዎችን ማስቀመጥ ይኖርብናል። ይህን ለማድረግም ሁኔታዎች ከመቼውም በላይ የተመቻቹ ናቸው።
አዲሱ የፖለቲካ ግንዛቤ፣ በተለይ በዋንኛው የአገሪቱ የፖለቲካ ችግር ላይ ያለው ግንዛቤ ከተለያዩ ብዥታዎች ጠርቶ አንድ መስመር ይዟል። የፖለቲካችን ችግር ሕዝብ የስልጣን ባለቤት እንዳይሆን ያገዱትን መሰናክሎችን የማስወገድ ችግር ነው። በአሁኑ ወቅት ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ይሁንታ ሳይሰጣቸው በጉልበትም ሆነ በሸፍጥ ስልጣን መያዝ አለብን ወይም ይቻላል ብለው የሚያሰቡ ድርጅቶች ቁጥራቸው እየተመናመነ ነው። ይህ ስሜት ያላቸው ድርጅቶች ቢኖሩም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በአገር ውስጥና ከአገራችን ውጭ በማኅበረተሰባችን ውስጥ ዴሞክራሲን በሚመለከት የተደረሰበት ግንዛቤና ለዴሞክራሲ ትግሉ የተከፈለው መስዋዕትነት የሚያነቃንቃቸው እንዳልሆነ ያውቁታል። አንዳቸውም በአደባባይ፣ ሕዝብ ፊት ቆመው ስልጣን በጉልበት ወይም ሕዝብን ባገለለ መልኩ በፖለቲካ ልሂቃኑ መካከል በሚደረስ የውስጥ ስምምነት መያዝ ይገባዋል ብለው መናገር ከማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ስልጣን ላይም ያለው አምባገነናዊ የወያኔ ድርጅት ሳይቀር ህጋዊነቱን ከዴሞክራሲ ጋር ለማያያዝ ሲተጣጠፍ እንጂ የስልጣኔ ምንጭ ከደደቢት በረሃ አንግቤ የመጣሁት ጠመንጃዬ ነው ብሎ ደፍሮ አይናገርም። ከእንግዲህ የዴሞክራሲን ጽንስ ሃሳብ የበላይነት በኢትዮጵያ ውስጥ ማንም ሊያስቆመው አይችልም።
ከዚህም በተጨማሪም ምርጫ 2002ን ተከትሎ የመጣው እውነታ የፖለቲካ ድርጅቶችን ሆነ የማኅበረሳባችን ግንዛቤ ቀይሮታል። ወያኔ ስልጣን ላይ እስካለ በምርጫ በሚደረግ የፖለቲካ ድርጅቶች ውድድር ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር እንደማይቻል ለሁሉም ግልጽ ሆኗል። ይህ እውነታ ቀደም ብለው በነበሩ የትብብር ሙከራዎች ተከስተው የነበሩ ችግሮችን አሰወግዷቸዋል። ወያኔ ስልጣን ላይ ሆኖ በምርጫ ስልጣን መያዝ ይቻላል የሚል ቀቢጸ ተስፋ በነበረበት ወቅት በድርጀቶች መሃል የሚደረግ ትብብር ተቃዋሚዎቹ ስልጣን ቢይዙ በሥራ ላይ ለማዋል በሚፈልጓቸው በርካታ ፖሊሲዎች ላይ የጋራ አቋም ይዘው መገኘት የግድ ይላቸው ነበር። ይህ ማለት የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ፣ አስተዳደራዊ፣ የውጭ ጉዳይና ሌሎችም ፖሊሲዎች ላይ የጋራ አቋም መያዝ ይገባቸው ነበር ማለት ነው። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጀቶች መካከል እንኳን በተጠቀሱት ፖሊሲዎች ዙሪያ ቀርቶ ከዛም ባነሱ ጉዳዮች ዙሪያ ስምምነት ላይ ደርሶ ትብብር መጀመርና የትብብሩን እድሜ ማራዘም ምን ያህል አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል በተግባር ያየነው ነው።
ምርጫ 2002 ያደረገው ነገር የፖለቲካ ድርጅቶችን ለስልጣን ከሚደረግው ትግል በፊት ፊታቸውን ስልጣን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለመያዘ ወደሚቻልበት ትግል እንዲያዞሩ ማስገደድ ነው። በመሆኑም የፖለቲካ ድርጅቶች ቀደም ብለው በተጠቀሱት በበርካታ ፖሊሲዎች ዙሪያ ስምምነት ማድረግ ሳያስፈልጋቸው ለራሳቸውም ሆነ ለሕዘቡ የዴሞክራሲ መብቶች እንዲረጋገጡ በጋራ ትግል ለማድረግ የሚችሉብትን ሁኔታ ፈጥሯል። ከስልጣን መያዝ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች ከትብብሩ ቀመር መወገዳቸው የመተባበር ሥራችንን አቅልሎታል።
ስልጣንን ለመጋራት የሚደረግ ትብብር እና ስልጣን በዲሞክራሲያዊ መንገድ የሚያዝበትን ሁኔታ በጋራ ለማመቻቸት የሚደርግ ትብብር ለየቅል ናቸው:: ስልጣን የሚያዘው በድርጅቶች መካከል በሚደረግ ድርድርና ትብብር ከሆነ “እኔ ስልጣን አነሰኝ፤ እከሌ ደግሞ በዝቶበታል” የሚል ጭቅጭቅ መቀስቀሱ አይቀሬ ነው። አንድ አይነት የትብብር ስምምነት ከተደረሰም በኋላም የሚገባኝን ስልጣን አላገኘሁም የሚል በሽታ ያገረሻል። ከፍተኛ ስልጣን በእጃቸው ይገባል ተብሎ የሚታሰቡ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን መጠራጠር “ አድብተው ጉድ ሊሰሩን ይችላሉ” ብሎ መስጋት ይኖራል። ይህ ጥርጣሬ በድርጅቶችና መሪዎች መካከል ያለውን መተማመን ገና ከመነሻው ያደፈርሳል።
ስልጣን የሚያዝበትን አግባብ ለማመቻቸት የሚደረገው ትብብር ግን ለእንዲህ ዓይነቱ ጥርጣሬ ሰፊ በር አይከፍትም። የ2002 የወያኔ የምርጫ መልዕክት ስልጣን በምርጫና በዴሞክራሲ ስም ከወያኔ መውሰድ የሚቻለው በወያኔ መቃብር ላይ መሆኑን ግልጽ ማድረጉ ለስልጣን የሚደረግን ትብብር ከፈረሱ የቀደመ ጋሪ አድርጎታል። ይህ እውነታ በማያጨቃጭቁ ጉዳዮች ዙሪያ እንድንተባበር መንገዱን ጠርጎልናል። ካለፉት የትብብር ውድቀቶቻችን ትምህርት መውሰድና ለነበሩት ችግሮች መፍትሄ መስጠት እንችላለን የሚል ድፍረት የሰጠንም የሁኔታዎች መቀየር ነው። ምን ማድረግ ይቻላል?
ባህልን በአጭር ጊዜ መቀየር አይቻልም። የባህል ለውጥ ረጅም ሂደት ነው። ሆኖም ግን ያ የለውጥ ሂደት መጀመር ይኖርበታል፤ መጀመር ያለብንም እኛው ነው። የሚከተሉትን ተግባራት በመከወን ረጅሙን የባህል ለውጥ አሁኑኑ መጀመር ይገባናል።
ከተራ ቁጠር 5.2 እስክ 5.4 የተዘረዘሩት ተግባራት በሚገባ ከተፈፀሙ ከላይ ያቀረብነውን ጥያቄ የመመለሱ ሥራ ከግማሽ በላይ ተጠናቋል ማለት ይቻላል።
ከዚህ ቀጥሎ “ግቡን ሊመታ የሚችል ታላቅ የትብብር እንስቃሴ እንዴት ማስተባበር ይቻላል” በሚል የቀረበውን ግዙፍ ጥያቄ በተለያዩ ንኡስ ርዕሶች በመከፋፈል ለመመለስ እንሞክራለን። እነዚህን ጥያቄዎች በሙሉ በአግባቡ መመለስ ግቡን ሊመታ የሚችል ታላቅ የመተባበር እንቅስቃሴ ለመመስረት ወሳንኝነት ይኖረዋል የሚል እምነት አለን። እነዚህ ጥያቄዎች “የመተባበሩን አጀንዳ በባለቤትነት ማን ያንሳው?” ከሚለው ተራ የሚመስል ጥያቄ አንስቶ የትብብሩን መነሻ፣ መሸጋገሪያና መድረሻ የሚመለከቱ ጥያቄዎችና ምላሾቻቸው በግልጽ የተካተቱባቸው ይሆናሉ። በእነዚህ ጥያቄዎች አማካይነት የትብብር ፍላጎታቸንን ገና ከጅማሮው አንስቶ የመጨረሻው ምዕራፍ እስከሚደርስ ድረስ ሊያደናቅፉት ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ ተግዳሮቶች በሙሉ አስቀድመን እናነሳለን። በእነዚህም የወገናቸን የዘመናት ጥማት የሚያረካና የአገራችንን ፍላጎት የሚያሟላ በምንም አይነት ማደናቀፊያና በማንኛውም ሁኔታ ውሉን የማይስት የትብብር እንቅስቃሴ ለመፍጠር እንችላለን ብለን እናምናለን።
እንደኛው በርካታ የፖለቲካና ፖለቲካዊ-ያልሆኑ ድርጀቶች “በአገራችን ጉዳይ ያገባኛል” ብለው በተነሱባቸውና ውለው አድረውም የተሳካ ትብብር ለማድረግ ከቻሉ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ተመክሮዎች ለመማር እንደምንችለው ሌላው ቀርቶ ስለመተባበር ጉዳይ አንስተው ለመነጋገር የማይችሉባቸው ሁኔታዎች ገጥሟቸው እንደነበር ነው። በድርጅቶች ወይም በመሪዎቸ መካከል ያለው አለመግባባትና ጥርጣሬ አንዱ ለሚያደርገው ጥሪ ሌላው መልስ የማይሰጥበት ሁኔታዎች ይከሰታሉ። “ይህ ግለሰብ ወይም ድርጅት የሚጠራው የመተባበር ስብሰባ አስቀድሞ ለራሱ ድርጅት እንደሚጠቅም ሆኖ የተዘጋጀ ነው” በሚል መነሻ ለጥሪው መልስ አለመስጠት የተለመደ ነው። አንዳንዴም የመተባበር ጥሪውን ያቀረበውን አካል ትንሽና ዝቅተኛ አድርጎ በማየት መልስ መስጠት “የድርጅትን ወይም የመሪውን ክብር ይነካል” በሚል ምላሸ የማይሰጥባቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ። ሌላው በአደባባይ በአንድ ድርጅት ወይም ግለሰብ ለሚጠራ የእንተባበር ጥሪ መልስ መስጠት “ትብብርን ለመፍጠር መንሰፍሰፍን የሚያሳይ ምልክት ይሆናል፤ ይህም በድርድር ወቅት ይጎዳኛል” በሚል እምነት ለትብብር ጥሪ መልስ አይሰጥም።
በፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ሰፊ ልዩነት ያላቸው ቡድኖች በቀጥታ ስለትብብር መነጋገር ስለማይችሉ ንግግር እንዲጀመሩ አማላጅ እስከመላክ የሚያደርስ ፈተና ይገጥማል። ስለዚህም ነው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ኃይሎች ተገናኘተው ተባብረው እንዲሰሩ ለማድረግ ስለመተባበር የሚያደርጉትን የመጀመሪያ ስብሰባ ለመጥራት ሳይቀር ብልህነት የሚጠይቅ ስራ ሊሆን ይገባዋል የምንለው። በዚህ ረገድ የሕዝባዊ ሚዲያ ተቋማት ሚና ከፍተኛ ነው።
እንደኛው በዚህ የመተባበር ጉዳይ ላይ ጨንቋቸው የነበሩ ማኅበረሰቦች ስለመነጋገር ለመነጋገር (talking about talks) ከሚል ዝቅተኛ ደረጃ የሚጀምር የውይይትና የድርድር ሂደት ማካሄድ የሚያስፈለግበት ወቅት እንደሚኖር የሚያስተምሩትም ለዚሁ ነው። ከዚህ በላይ ከተጠቀሰው በመነሳት በሁላችንም ልብ ውስጥ የሚንቦገቦገውን የመተባበር ፍላጎት እንዴት እናስጀምረው? በበኩላችን መልሱ እነሆ።
6.5.1. ለጋራ ትግልና ድል መሠረት የሚጣለው በድርጅቶች መካከል ኅብረት ለመፍጠር የሚደረገውን በጥንቃቄ በመከነወን ሂደት ነው ። ከላይ በ 6.2 የቀረበውን ማሳሰቢያ በጥሞና ማጤን ጠቃሚ ነው።
6.5.2. በድርጅቶች መካከል በተደረጉ ውይይቶች የታየውን ተባብሮ የመሥራት ፍላጎት ዘላቂ እንዲሆን ለመሥራት ፍላጎቱ ያላቸው ድርጀቶች፣ ለራሳቸውም ሆነ በጉጉት ለሚጠብቃቸው ሕዝብ ከየት ተነስተው በምን አቋርጠው የት እንደሚደረሱ በግልጽና በያሻማ ቋንቋ የተቀመጠ የተሟላ እቅድ ( road map ) ሊኖራቸው ይገባል። ይህ የተሟላ እቅድ ድርጅቶቹ እርስ በርስ ቃል ኪዳን የሚገቡበት ብቻ ሳይሆን ለሕዝብም ጭምር ቃል የሚገቡበት መታሰሪያቸው ይሆናል። በዚህ እቅድ ውስጥ በሚካተቱ መሠረታዊ ነጥቦች ላይ አንድ ወጥ የጋራ ስምምንት ሳይደረስ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ሆነ ወይም “ለጥቂት ጊዜ አብረን መስራት እስከቻልን ሌላውን ችግር ጊዜ ይፈታዋል” በሚል የሚደረግ ውለታና ስምምነት ከቶውኑ ሊኖር አይገባም:: በተውሸለሸለ መንገድ በሚፈጠር ትብብር የሕዝብ ቅስም በድጋሚ እንዲሰብር ልንፈቅድ አይገባም። በአገራችን ድርጅቶች መካከል የሚደረግ የስምምነት ውል የሚያፀናው 1) የድርጀቶችና የመሪዎቻቸው ቀና ፍላጎትና አርቆ አሳቢነት፤ 2) በተወሰን ደረጃም ቢሆን በሕዝብ ፊት የተገባ ቃል ኪዳንና ፤ 3) ውሉን በሂደት ለማፍረሰ ሰበብ ሊሆኑ ይቸላሉ ተብለው የሚታሰቡ ማናቸውም ችግሮቸ አስቀድሞ የታሰበባቸውና መፍትሄ የተሰጣቸው ከሆኑ ብቻ ነው። በመሆኑም የተባለው እቅድ የሚከተሉትን መሠረታዊ ነጥቦች ያካተተ ሊሆን የገባዋል።
እነዚህና መሰል ጥያቄዎች ካሁኑ ምላሽ ይፈልጋሉ። እነዚህና ሌሎችም መሠረታዊ ስነዶች በዝርዝር ተዘጋጅተው የትብብሩ ስምምነት ወይም ውል አካል መሆን አለባቸው። በትብብሩ የጋራ ጉዞ የድርጅት ወይም የመሪዎች ጠባብ ፍላጎቶች ሊያደፈሩሱዋችው ብሎም ትብብሩን ሊያመክኑ የሚችሉ መሠረታዊ ጉዳዮች በይደር መታለፍ አይኖርባቸውም። መሠረታዊ የሆኑ ሰነዶች አስቅድመው ገና የትብብሩ ውል በድርጅቶች መካከል ከመፈረሙ በፊት የሚጠናቀቁ በመሆናቸው፣ የሰጥቶ መቀበል የድርድር ውጤት እንጂ ድርጅቶች በመቧደን ወይም በትብብሩ ውስጥ በሚኖራቸው ወንበሮች ቁጥር የሚወሰኑ አይሆንም።
በመሆኑም የወደፊቱ ሥራ ይህ በሙሉ ስምምነት ተቀባይነት ያገኘን ዝርዝር እቅድ (road map) በተግባር ለመተርጎም ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውጭ ድርጀቶችን ሊያጨቃጭቁ የሚችሉ የውሳኔ ጉዳዮች አይኖሩም። ይህ አሠራር ድርጅቶች ብዙ ወንበር ስላላችው ወይም በፖለቲካ ዓላማቸው ስለሚቀራረቡ አንዱ በሌላው ኪሳራ የሚፈልገውን በማስወሰን ችግር ይፈጥርብኛል የሚል ስጋትና ጥርጣሬን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል። በትብብሩ የሥራ ኃላፊነት ቦታዎች ላይ በመቀመጥ ሊገኝ የሚችልን ጠቀሜታ ስለሚያሳንሰው ከየድርጅቶቹ የሚነሳውን የስልጣን ሽኩቻ ይቀንሰዋል። የትብበሩ አካላት ቁጥር ቢበዛ የሚያሰበረግግ አይሆንም። እንዲያውም በርካታ ቡድኖች የትብብሩ አካል እንዲሆኑ፣ ብዙሃኑን ያካተተ፣ ማናቸውም ፈተናዎች የማያኮላሹት ጠንካራ ትብብር እንዲኖር የሚያበረታታ ይሆናል።
በመጨረሻም በአገራችን እውነተኛ የዲሞክራሲ ሥርዓት እንዲመሰረት በጋራ ለመሥራት በሚደራደሩ ድርጅቶች መካከል የሚደረግ ድርድር በንግድ ባላንጣዎች መካከል የተፈጠረን ቅራኔ፣ ወይንም ኑዛዜ ባልተገኘለት ወራሾች መካከል የሚደረግ ድርድር ተደርጎ መታየት የለበትም:: በእነዚህ ድርድሮች እያንዳንዱ አካል የተቻለውንና ያህል ተጠቃሚ የሚያደርገውን ድል ለመቀዳጅት ተግቶ ይሰራል። አንዱ ሌላው የሚፈልገውን እንዳያውቅ የመደራደሪያ ካርዶቹን ማንም እንዳያይበት ደረቱ ላይ ለጥፎ ይቀመጣል። አንዱ ሌላውን አካል የሚያቀርበውን መደራደሪያ በንፉግ መንፈስ ተሸፋፍኖ ያየዋል። በእነዚህ ምሳሌዎች ውስጥ የተጠቀሱት አካላት በድርድር ችግራቸውን መፍታት ካልቻሉ ጉዳያቸው ወደ ህግና ዳኝነት ሄዶ መፍትሄ ያገኛል የሚል እምነት ስላላቸው በድርድር አንድ አይነት ስምምነት ላይ ካልደረሱ የድርድሩን መቋረጥ የሞትና የሽረት ጉዳይ አድርገው አያዩትም።
በአገራችን የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የሚደረግ ድርድር ከላይ በጠቅስናቸው ምሳሌዎች መንፈስ ሊከናወን አይችልም። ድርድሩ ሁሉንም አሽናፊና ተጠቃሚ አድርጎ ሊያውጣ በሚችል መርህ ብቻ ነው ሊመራ የሚችለው። የድርድር ሂደት ቢደናቀፍ ከጋራ ውድመት በስተቀር በገላጋይ የሚተርፈን ጠቀሜታ አይኖርም። “ድርጅቴ ምን ያገኛል? እኔ ምን እጠቀማለሁ?” ከሚል ስሌት በላይ ተሻግሮ ሁላችንም “የዛች መከረኛ አገር ሕዝብ ምን ያገኛል? የመተባበሩን ሥራ እንዲሰምር ድርጅቶች እንዲቀራረቡ ድርጅታችን ምን ማዋጣት ይችላል?” በሚል ቀና መንፈስ የምንቀርበው ብቻ ነው መሆን የሚችለው። አንዳችን በሌላው ኪሳራ ትርፍ የምናገኝበትን ስሌት አስልተን ወደ ትብብር ምሥረታ የምንጠጋ ከሆነ እንኳን የትብብሩን ዒላማ ልንመታ ይቅርና ትብብሩም በእግሩ እንኳን ማቆም እንደማንችል መታወቅ ይኖርበታል።
ይህንን ሃቅ ከምር በመረዳት የግንቦት7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ አገራዊና ሕዝባዊ ለሆነውን የመተባበር ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው። በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የተቀመጡትን እና ከሌሎች ወገኖቻችን ጋር በሚደረጉ ምክክሮች የሚታከሉ ቁምነገሮችን የመተባበሪያችንን መሠረት አድርገን ከተነሳን የተዋጣለት ትብብር በማድርግ የወያኔን ዘረኛና አምባገነናዊ ሥርዓት እድሜ እናሳጥራለን።