የወያኔን “ልማታዊነት” የውሸት ፕሮፖጋንዳን ማምከን አንዱ ሥራችን ነው!!!

በአገዛዞች ተወዳጅ የሆኑት ጉልበት፣ ትዕቢትና ጉራ በተገዢዎች ልብ ውስጥ ፍርሃትን ብቻ ሳይሆን ቂምና የአመፃ ስሜትንም መትከላቸው ፈጽሞ የማይቀር ነገር ነው። በዚህም ምክንያት አገዛዞች ጉልበትንና ትዕቢትን ከማባበልና መደለል ጋር ቀላቅለው ያቀርባሉ። ይህ አገር በቀል አምባገነኖችም ሆኑ ድንበር ተሻጋሪ ቅኝ ገዢዎች ሲጠቀሙበት የኖረ ዘዴ ነው። ፈረንጆች ይህን ዘዴ “ዱላና ካሮት” ብለው ይጠሩታል። ይህ መሰሪ ዘዴ እነሆ ወያኔንም ሃያ አመታት አዝልቆታል።

ይሁንና የወያኔ “ዱላና ካሮት” ከሌሎች አምባገነኖች ዱላና ካሮት የተለየ ባህሪ አለው። የወያኔ ዱላ ያው ዱላ ነው፤ የወያኔ ካሮትም “ካሮት” ተብሎ ይጠራ እንጂ ዱላ ነው። ስለሆነም እኛ ከወያኔ የምናገኘው ከሌሎች አምባገነኖች እንደሚገኘው የዱላ እና የካሮት መፈራረቅ ሳይሆን የዱላ እና የዱላ መፈራረቅ ነው።

ወያኔ በምርጫ ስም ሲፈጽመው የኖረው ዓይን ያወጣ ትዕቢትና ማንአለብኝነት ዱላ ነው። በዋና ዋና የመንግሥት ተቋማት የራሱን ሰዎች ብቻ መሰግሰጉ እና ተቋማቱ ለኢትዮጵያ ሳይሆን ለወያኔ ደህንነትና ምቾች የሚሠሩ መሆናቸው በኢትዮጵያና ሕዝቧ ላይ የተሰነዘረ ዱላ ነው። የፍትህ ተቋሙ እና ፍትህ ሆድና ጀርባ ሆነው በፍትህ ላይ መቀለድም ፍጹም ከሆነ ትዕቢት የሚመነጭ በኢትዮጵያ ላይ የተሰነዘረ ዱላ ነው። ንግዱንም እርዳታውንም መቆጣጠሩ ዱላ ነው። ንፁሃን ዜጎች መጨፍጨፋቸው፤ እስር ቤቶች በንፁሃን ዜጎች መጨናነቃቸው፤ ሕዝብ መተንፈሻ አጥቶ በሥጋት እንዲኖር መደረጉ፤ መረን የለቀቀ ዘረኝነትና ጭካኔ የአገዛዙ መታወቂያዎች ናቸው። ይህ ሁሉ ዱላ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ወራሪ ቅኝ ገዢዎች ይሉት እንደነበረው ሁሉ “ታይቶና ተሰምቶ የማይወቅ ልማትን ይዤ መጥቻለሁ። እነሆ ትምህርት፣ የጤና አገልግሎች፣ መንገድ፣ መብራት፣ ውሃ” ይለናል። ይህ የወያኔ ካሮት መሆኑ ነው። ይህ “ካሮት” የተባለው ነገር ራሱ ዱላ እንደሆነ ባጭሩ እንደሚከተለው እናብራራለን።

አንደኛ፤ በአሁኑ ሰዓት የወያኔ የፕሮፖጋንዳ አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻልበት ሁኔታ ያተኮረው “ልማትን ያመጣሁ በመሆኔ የመግዛት መብት አለኝ የሚል ነው”። ይህ ምን ማለት ነው? ወያኔ ያመጣልን “ልማት” ሰብዓዊ ክብራችን ለማጣታችን የተከፈለን ካሳ ነው ማለት ነው? ይህ “ልማትን” እርም የሚያሰኝ፤ የሚዘገንን ነገር ነው። ይህ ልማት ካሮት ሳይሆን እጅግ የሚያሳምም ዱላ ነው። የሰው ሰውነቱ የሚታወቀው በመብላቱና በመልበሱ ሳይሆን ለሰውነቱ በሚሰጠው ክብር ነው። የወያኔ “ልማታዊ መንግሥት ነኝ፤ ይህም ገና ለብዙ ዘመናት የመግዛት መብት ያሰጠኛል” የሚለው ጉራ “እናንተ እንስሶች ናችሁ፤ የምትበሉትን ካቀረብኩላችሁ ይበቃችኋል። የሰጠኋችሁን ተቀብላችሁ ተገዙ” እያለን መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። በአሁኑ ሰዓት የሚደረጉ የመብት ማስከበር ትግሎች በሙሉ “ፀረ-ልማት” ተብለው በአገዛዙ መፈረጃቸው በዚህ ምክንያት እንደሆነ ማስተዋል ይገባናል። ይህንን አዋራጅ ልማት “አንፈልግም” ማለት መቻል አለብን:: ሁላችንም በአንድ ልብ “እኛ እንስሶች አይደለንም፤ ለእለት እንጀራ ስንል መብቶቻችንን አሳልፈን አንሰጥም!!!!” ማለት መቻል ይኖርብናል ። ይህን ማለት ካልቻልን ግን በእርግጥም ለሰብዓዊ ክብር አልበቃንም ማለት ነው።

ሁለተኛውና አስገራሚው ነገር ነጋ ጠባ “ይህንንና ያንን ሰርቻለሁና ፀጥ ብላችሁ ተገዙ” እየተባልን ያለንበት ልማት የት እንዳለ ያለማወቃችን ችግር ነው። የራሳችንን ጓዳ ስንፈትሽ የተወራለትን ልማት አናገኝም። የት ስላለ ልማት ነው እየተወራ ያለው? አዎ! ወያኔ ራሱንና የራሱን ወገኖች አጥግቧል። የወያኔ ሹማምንት እና ዘመዶቻቸው ሰምተው በማያውቁት ሃብት ተንበሻብሸዋል። እነሱ ግዙፍ ሕንፃዎችን በከተሞች ውስጥ ገንብተዋል። ግና ይኸ ሁሉ ለእኛ ለድሆቹ ኢትዮጵያዊያን ምናችን ነው? ለመሆኑ እጅግ ጥቂት የሆኑ ሰዎች በልጽገው ብዙሃን መደህየታቸው ልማት ነው? የጥቂቶቹ የብልጽግና ምንጭም የኛ ድህነት ያመጣው እርዳታ፣ በአሜሪካ፣ አውሮፓና አረብ አገሮች ከሚገኙ ወገኖቻችን የሚላከው ገንዘብ፣ የመሬትና የሕፃናት ሽያጭ ገቢ መሆኑ እግምት ውስጥ ስናስገባ ወያኔ ጥፋትን “ልማት” እያለ እንደሚጠራ ግልጽ ይሆንልናል። በዚህ ሁኔታ የመጣ ልማት ካሮት ሳይሆን ዱላ ነው።

ሶስተኛው አቢይ ነጥብ ደግሞ በብዛትና በጥራት መካከል ያለው ግኑኝነት ነው። ወያኔ ብዛትን አጥብቆ የሚወድ በመሆኑ ቁጥሮችን በማፍላት ያልተመረተውን ተመረተ፤ ያልተሠራውን ተሠራ ይለናል። ይህ ብቻም አይደለም የእውነት የተመረቱት ነገሮችም ቢሆኑ ለጥራት ቁብ የሌለው በመሆኑ “ባይመረቱ ይሻለን ነበር” የሚያስብሉ ናቸው። “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” እንደተባለው የዘመነ ወያኔ ምርት አረም የበዛበት ነው። ለምሳሌ፤ ተምረው ከኮሌጅ ተመረቁ የተባሉ ወጣቶቻችን እንደገና እንደ አዲስ መጀመር የሚኖርባቸው ደረጃ ላይ እንዲገኙ ተደርገዋል። ከሆስፒታሎችና ክሊኒኮች ድኖ የሚወጣ ሰው ማየት ብርቅ ሆኗል። መብራትና ውሃውም ወሬዓቸው እንጂ እነሱ ራሳቸው የሉም። ገጠር ቀድሞ ለም የነበረው ማሳ በይድረስ ይድረስ ግብርና ወደ ጭንጫነት እየተቀየረ ነው። የተለየ ነገር የሚታየው በመንገዶች ላይ ብቻ ነው፤ እሱም ቢሆን የልጅ ልጅ ልጅ ልጆቻችን መንገዶቹ የተሰሩበትን ዋጋ ብቻ ሳይሆን የወያኔ ባለሥልጣኖች የቀበጡበትንም ጨምረው ይከፍላሉ። በእውነት ይህ ነው ልማት የሚባለው? እንዲ ዓይነቱ ልማት ካሮት ሳይሆን ዱላ ነው።

አራተኛ፤ የወያኔ “ልማት” የብቃት ማነስ ማካካሻ ነው። በአሁኑ ሰዓት ጎልተው የሚታዩ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች በሙሉ “ፈጣን ልማት የፈጠራቸው ችግሮች” ተብለው እንዲታለፉ እየተደረገ ነው። የዋጋ ንረት፣ የሥራ እድሎች እጦት፣ የመኖሪያ ቤት እጥረት፣ የሃኪሞች እጥረት፣ የመድሃኒት እጥረትና ውድነት፣ የውሃ እጦት፣ የመብራት መቋረጥ፣ የቴሌፎን መስመሮች መጨናነቅ፣ የመምህራን እጥረት፣ የትምህርት ክፍሎች መጣበብ፣ የማዳበርያ እጥረት፣ የዘር እህል እጦት ….ወዘተ “ፈጣን ልማት” አመጣቸው የሚባሉ ችግሮች ተዘርዝረው አያልቁም። እንዲህ ዓይነቱ ልማት ካሮት ሳይሆን ዱላ ነው።

በመጨረሻም የወያኔን ሬድዮና ቴሌቪዥንን ብቻ እየሰማ ላለ ሰው በዓለም ላይ እያደገች ያለችው አገር ኢትዮጵያ ብቻ ሊመስለው ይችላል። ነገር ግን በአለፉት አስር ዓመታት ውስጥ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ከዚህ በፊት ባላደጉበት ፍጥነት እያደጉ ነው። አንዳዶች አገሮች እንደወያኔ የውሸት ሳይሆን የእውነት ከአስር በመቶ በላይ አድገዋል። ታድያ ዓይንን ጨፍኖ፤ ጆሮን አደንቁሮ፤ አዕምሮን አደንዝዞ በተፈጠረ ልብ ወለድ ልማት መጨፈር ብልህነት ነው ወይስ ድንቁርና። እንዲህ ዓይነቱ አደንዛዥ ልማት ካሮት ሳይሆን ዱላ ነው።

አምባገነኖች ዱላና ካሮትን ማፈራረቃቸው የተለመደ ነው። እናም አንዳዶች “ካሮቱ በርከት ካለ ዱላውን እንቻለው” እንደሚሉ እናውቃለን። ደቡብ ኮሪያን፣ ቺሊና ቻይናን እየጠቀሱ የሚከራከሩ አሉ። እነዚህ ወገኖች ያልተገነዘቡት ወይም ሊገነዘቡ ያልፈለጉት ሃቅ ግን ወያኔ ዱላና ካሮት ሳይሆን ዱላና ዱላን የሚያፈራርቅ መሆኑን ነው።

ወያኔ በልማት ስም የሚያደርስብንን የፕሮፖጋንዳ ጥቃት ለማምከን ወደፊት ገና ብዙ የምንለው ይኖረናል። ለጊዜው የሚከተሉትን አራት ነጥቦችን አጽንዖት መስጠት እንፈልጋለን።

  1. ልማት ማምጣት ሕዝብን የመግዛት መብት አይሰጥም። እንዲህ ዓይነቱን የቅኝ ገዢዎች አስተሳሰብን አጥብቀን እንዋጋለን፤
  2. የወያኔ ባለስልጣኖችና ዘመዶቻቸው መክበርና የፎቆቻቸው መብዛት የኢትዮጵያን እድገት አያመለክትም። ይልቁንስ ጥቂቶች የአገራችንን ሃብት ምንኛ እየቦጠቦጡ መሆኑ ማሳያዎቻችን ናቸው።
  3. ለቁጥር ብዛት ብቻ በሚደረግ የይድረስ ይድረስ ሥራ በልጆቻችን ትምህርት፣ በጤናችን፣ በአፈራችን እና በዘወትር ሕይወታችን ላይ የሚሰራውን ወንጀል ማስቆም ይገባናል።
  4. በመረጃ እጦት ታፍነን የወያኔን የልማት ቱልቱላ ብቻ የምንሰማበት ዘመን መብቃት ይኖርበታል።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

© 2008-2009