የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አሁንም በኤሌክትሪክ ሃይል እጥረት ምክንያት እየተንገላቱ መሆናቸው ታወቀ

የወያኔ አገዛዝ የኤሌክትሪክ ሃይልን ለአፈና ተግባራቱ እያባከነ ባለበት ወቅት፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በኤሌክትሪክ ሃይል እጥረት ምክንያት መንገላታታቸው እንደቀጠለ ከመዲናይቱ የደረሰን ዘገባ አመልክቷል።

የግንቦት 7 ድምጽ ዘጋቢ ከአዲስ አበባ አጠናቅሮ በላከው መረጃ፥ ሰሞኑን በየቀኑ በአብዛኛው የከተማይቱ ክፍሎች በቀን ቢያንስ ለአራት ሰአታት የመብራት ሃይል ይቋረጣል።ይህ እጥረት በተለይም መብራትን ለንግድ ስራ የሚጠቀሙ ግለሰቦችን እና ሰራተኞቻቸውን ለአላስፈላጊ ወጪ እና ኪሳራ እየዳረገ መሆኑ ታውቋል።

ምንም እንኳ ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ቀድሞውኑ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት የማያገኙ እና በዚህ የሃይል መቆራረጥ የማይነኩ ቢሆንም፤ የብዙ የከተማ ነዋሪዎች ኑሮ ግን በኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ላይ ጥገኛ መሆኑ ይታወቃል። ፋብሪካዎች፣ ምግብ ቤቶች፣ ቡና ቤቶች፣ ጸጉር አስተካካዮች፣ ሆስፒታሎች እና የመሳሰሉት ድርጅቶች በኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ላይ በከፍተኛ ደረጃ ከሚመረኮዙት ውስጥ ይጠቀሳሉ።

የወያኔ አገዛዝ ከውጭ የሚሰራጩ ገለልተኛ የሬድዮ ጣቢያዎችን፤ እንዲሁም በቅርቡ ስራ የጀመረውን የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ድርጅት ስርጭቶችን ለማፈን ከፍተኛ መጠን ያለው የኤሌክትሪክ ሃይል እንደሚያባክን ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል።

© 2008-2009