የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ አለማቀፍ ልማት ዲፓርትመንት አዲስ የድህነት መመዘኛን ስራ ላይ በማዋል ባካሄደው አሰሳ 90 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ድሆች እንደሆኑ ገልጿል።
“መልቲ ዳይሜንሺናል ፑቨርቲ ኢንዴክስ” ወይም ዘርፈ ብዙ የድህነት መመዘኛ የሚባለውን አዲስ ዘዴ በመጠቀም በተደረገው በዚህ ጥናት፣ ይህ በኢትዮጵያ ያለው ድህነት በክፋቱ ከአለምሁለተኛ መሆኑን አስታውቋል። አንደኛውን ደረጃ የያዘችው ምእራብ አፍሪካዊቷ አገር ናይጀር ነች።
ከዚህ ቀደም በስራ ላይ ይውሉ የነበሩ የድህነት መመዘኛዎች፣ የግለሰቦችን የቀን ገቢ ብቻ ከግምት ውስጥ የሚያስገቡ ሲሆኑ፤ አዲሱ መመዘኛ በሰው ልጅ ህይወት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያደርሱ የሚችሉ ዘርፈ ብዙ ጉድለቶችን ከግምት የሚያስገባ ነው። ከነዚህም ውስጥ የትምህርትና የጤና ጥበቃ ሁኔታ፤ እንዲሁም የአጠቃላይ ኑሮ ደረጃን ይለካል። በዚህ መሰረትም፥ ከአስር ኢትዮጵያውያን ዘጠኙ ደሆች ናቸው ሲል ሪፖርቱ ደምድሟል። ጥናቱን ያካሄደው ተቋም ለምርምሩ የተጠቀመው ዳታ ወይም መረጃ የዛሬ አምስት አመት የተሰበሰበ መሆኑንም ገልጿል። በኢትዮጵያ ባለፉት አምስት አመታት፣ በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ ዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ስራ ላይ ያዋለውን ሃላፊነት የጎደለው የገንዘብ ፖሊሲ ተከትሎ፣ ቁጥራቸው የማይታወቅ ኢትዮጵያውያን ቀድሞ ከነበረው ወደ ባሰ ድህነት መሸጋገራቸው ይታወቃል።