በአዲስ አበባ የሚገኙ አድባራትና ገዳማት የፓትሪያርክ አቡነ ጳውሎስን 18ኛ ዓመት በዓለ ሲመት ምክንያት በማድረግ 3.4 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ መኪና ሽልማት የሰጡ መሆናቸውን ደጀ ሰላም ኮም ድረ ገጽ ዘግቧል። ደጀሰላም እንደገለጸው ድርጊቱ ከአዲስ አበባ ሐገረ ስብከት ፈቃድ ውጭ በፓትሪያሪኩ ሰዎች መልካም ፈቃድ የተዘጋጀ ከመሆኑም ባሻገር የአድባራቱን አቅም ግምት ውስጥ ያላስገባና እንዲያዋጡ የተጠየቁትን ገንዘብ በምን አይነት ሁኔታ ከሚኖር ሕዝብ እንደሚሰበስቡት ያላገናዘበ መሆኑን አትቷል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም ከዚህ በፊት ተደርጎ በማይታወቅ ሁኔታና የቤተክርስቲያኒቷን ህግና መመሪያ በጣሰ መልኩ ቦሌ በሚገኘው መድሃኔዓለም ቤተክርስቲያን ቅጽር ግቢ ውስጥ ለቅዱስነታቸው ማስታወሻ በሚል ለፓትሪያሪኩ ሐውልት እንዲቆም የተደረገ መሆኑን አክሎ ገልጿል።
ዜናውን ተከትሎ የተለያዩ ግለሰቦች ድረገጹ ላይ በሰጡት አስተያየት ለሐውልቱ የወጣውን ወጭ እና ሊተላለፍ የተፈለገው መልእክት ሲታሰብ ቤተክርስቲያኒቷ ምን ያህል ከሐይማኖታዊ ጥንተ መሰረቷና ተውፊቷ እርቃ እንደሄደች ያሳየናል፤ አንድ አባት እንኳንስ በህይወት እያለ ይቅርና በአጸደ ነፍስ ቢሆን አንኳ ሶስት ገጽ ያለው ምስል ለራሱ ማቆም ጣኦትን እንደማምለክ ስለሚያስቆጥር በጥብቅ የተከለከለ ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደምም እነዚሁ የቤተክርስቲያን አባትና አስተዳዳሪ ነን ባዮች አቡነ ጳውሎስን ለማስደሰት በሚል በየአድባራቱ ትልልቅ ፎቶግራፎቻቸው እንዲሰቀሉ ማድረጋቸውና በአዲስ አበባ በሚገኙ አድባራትና ገዳማትም በያንዳንዳቸው ላይ 10000 ብር እንዲያዋጡ ማስገደጃ ተጥሎ እንደነበር ይታወሳል።
ከዚሁ ዜና ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ጳውሎስ የአስራ ስምንተኛ አመት በአለ ሲመታቸውን ባከበሩበት እለት ለመታሰቢያቸው የተሰራው ሃውልት መመረቁን አስመልክቶ የወጣው ዜና ሰሞኑን በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል።
ለዝግጅት ክፍላችን ቃላቸውን የሰጡና ስማቸው እንዳይጠቀስ የሚፈልጉ የአዲስ አበባ ነዋሪ ይህንን ከሰሙ በኋላ ወደ ቤተከርስቲያን ላለመሄድ መወሰናቸውን ገልጸውልናል። እኒሁ ግለሰብ ከዚህ ቀደም በፓትሪያርኩ ላይ አሉታዊ አመለካከት ያልነበራቸውን ጨምሮ በርካታ የሚያውቋቸው ሰዎች በገንዘብ እጦት የተነሳ ጣሪያቸው የሚያፈስ ቤተክርስቲያኖች እና ብዙ ችግረኞች ባሉበት አገር ፓትሪያርኩ ለራሳችው ሃውልት ማስገንባታቸው አግባብ እንዳልሆነ በቁጣ ሲናገሩ መስማታቸውንም ተናግረዋል።
በተለያዩ ድረ-ገጾች ላይ ጉዳዩን በሚመለከት የተቃውሞ ጽሁፎች የወጡ ሲሆን፤ የአንባብያን አስተያየት መስጫ ሰሌዳዎቹም የቁጣ መግለጫዎች ሆነው ሰንብተዋል። ዳንኤል ክብረት የተባለው የቀድሞ የአዲስ ነገር ጋዜጣ አምደኛ እና “የሁለት ሃውልቶች ወግ” የተሰኘው መጽሃፍ ጸሃፊ፦ “ሰው በቁሙ ሐውልት ለምን ይሰራል?” በሚል ርእስ በድረ-ገጹ ላይ በለጠፈው ጽሁፍ፤ በህይወት ሳሉ ሐውልትን ለራሳቸው የሚያስገነቡ ሰዎች ከሞቱ በኋላ ለነሱ ሐውልት የሚያቆም እንደሌለ የሚያውቁ ናቸው ብሏል።
በጹፉ ስር አስተያየታቸውን ከጣሉት አንባቢዎች ውስጥ አቶ ደረጄ የተባሉ ግለሰብ፥ “ብዙ ጊዜ የቤተክርስቲያናችን የዶግማ እና ቀኖና ህጎች በመሪዎቻችን ሲሰበሩ አፎቻችንን ዘግተን ቆይተናል። እስከመቼስ ይቀጥላል? ይህንን ለማቆም የምንሰራበት ጊዜ አሁን ነው።” ብለዋል።
አቶ አዲሱ የተባሉት ግለሰብ ደግሞ፥ “እንኳን ፓትሪያርኩን እና አቡኑን ቀርቶ፣ ተራ አማኝ ሶስት ገጽ ያለው ሃውልት በቤተክርስቲያናችን ወግ እና ደምብ ውስጥ እንደማይደረግ ያውቃል። የቤተክርስቲያኒቱን ወግ እና ደንብ ማስጠበቅ ያለባቸው ፓትሪያርክ ግን ያንን ለመስበር የመጀመሪያው ሆነዋል።” ብለዋል።
ፓትሪያርክ አቡነ ጳውሎስ ከወያኔ ጋር ጥብቅ የሆነ የጥቅም እና የመንደር ልጅነት ትስስር እንዳላቸው እና ያንንም ተጠቅመው በሳቸው ላይ ሂስ የሚያቀርቡትን ዝም የማሰኘት ልምድ እንዳላቸው ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል።