እሁድ ሐምሌ 4 ቀን በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ የደረሰው ፍንዳታ በአስርት የሚቆጠሩ ሰዎችን ከገደለ በኋላ በአገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በጥርጣሬ አይን እየታዩ መሆናቸውን ዘገባዎች አሳይተዋል።
የፍንዳታው አደጋ ከደረሰባቸው ቦታዎች አንዱ የኢትዮጵያውያን ንብረት የሆነ ምግብ ቤት እንደሆነ መዘገቡ ይታወሳል። ከሟቾቹም ውስጥ አንዱ ኢትዮጵያዊ መሆኑ እስካሁንየተረጋገጠ ሲሆን፤ የቆሰሉም እንዳሉ የተለያዩ ዘገባዎች አሳይተዋል። ይሁን እንጂ የአሜሪካ ድምጽ ሪፖርተር ፒተር ሃይነላይን ከካምፓላ እንደዘገበው፥ በኡጋንዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል።
በአንድ በኩል የኢትዮጵያውያን ምግብ ቤት የተጠቃበት ምክንያት የወያኔ ጦር የሶማሊያን የሽግግር መንግስት በመርዳት በአገሪቱ ያደረገውን ጣልቃ ገብነት እንደ አልሸባብ ያሉ ቡድኖች ኢትዮጵያውያንን በያሉበት በማጥቃት ለመበቀል በመፈለጋቸው ነው ተብሎ ይታመናል። በሌላ ጎን ደግሞ ከዚህ ቀደም በመልካም እንግዳ ተቀባይነት በተንከባከባቸው የኡጋንዳ ህዝብ ፊት በጥርጣሬ አይን መታየት ጀምረዋል። ይህ ሊሆን የቻለበትን ምክንያት ዘገባው ሲገልጽም፣ ለጥቃቱ ሃላፊነቱን የወሰደው የሶማሊያው አልሸባብ እንደመሆኑ ሶማሊዎች በጥርጣሬ መታየት ጀምረዋል። ለብዙ ኡጋንዳውያን ደግሞ፥ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያን እና ሶማሊዎች ስለሚመሳሰሉ አንዱን ከሌላው መለየት አስቸጋሪ ነው።
ፍንዳታውን አስመልክቶ ከካምፓላ ለአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ቃለ መጠይቅ የሰጠው የቀድሞ አዲስ ነገር ጋዜጣ አዘጋጅ አቶ ተስፋለም ወልደየስ በዚህ ምክንያት አንድ ኤርትራዊ በድብደባ መገደሉን ገልጿል። በኡጋንዳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አብዛኞቹ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስደተኞች እንደሆኑ ይነገራል። እስካሁን ከፍንዳታው ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው አራት ኢትዮጵያውያን መታሰራቸው የተዘገበ ሲሆን፤ ሊፈቱ እንደሚችሉ ፍንጮች እንዳሉ የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ተወካዮች መግለጻቸውን የአሜሪካ ድምጽ ዘግቧል።