ዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ በአፋር በተነኮሰው ግጭት በርካቶች ሞተዋል ተባለ

ዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ በአፋር ክልል በሚተነኩሰው ግጭት በርካቶች እየተገደሉ ነው ሲል የአፋር ህዝብ ፓርቲ በለቀቀው መግለጫ አስታወቀ።

በቅርቡ ባዱ በሚባል አካባቢ በተከሰተ ግጭት 30 ሰዎች ሞተው 50 የሚሆኑ ሴቶች፣ ህፃናት እና አዛውንቶች መቁሰላቸውን ፓርቲው ገልጿል። ከሁለት ወራት በፊትም በክልሉ የጋዋኔ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆነው [...]ግለሰብ ባልታወቁ ሰዎች መገደሉ ታውቋል። የአካባቢው ነዋሪዎች ወያኔ የእርስበርስ ግጭት ለመተንኮስ እና የግንቦቱን ምርጫ የተቃወሙ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን መምቻ ምክንያት ለማግኘት ሲል ሆን ብሎ የፈጸመው ትንኮሳ ነው ብለው እንደሚያምኑ መግለጫው ይናገራል። በአሁኑ ወቅት 20 የሚሆኑ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እና የሃገር ሽማግሌዎች በእስር ላይ እንደሚገኙም ታውቋል።

መግለጫው፥ የወያኔ እኩይ ተግባር የመነጨው አገዛዙ የክልሉን መሬት ለመቆጣጠር እና ከሱ ጋር ትስስር ላላቸው ነጋዴዎች ለመስጠት እያካሄደ ካለው ሩጫ ነው ብሏል። ከብቶች በማርባት የሚተዳደረው ህዝብ ለከብቶቹ ግጦሽነት ይጠቀመው ከነበረው መሬት ያለምንም ካሳ እየተፈናቀለ እንደሆነ እና የአዋሽን ወንዝም መጠቀም የማይችልበት ደረጃ ላይ እንደደረሰም አትቷል።

የአፋር ህዝብ ፓርቲ፥ ወያኔ እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ1976 ባወጣው ማኒፌስቶ የአፋርን ክልል ከትግራይ ጋር የማዳበል እቅድ እንዳለው መግለጹን እና አሁን እየሰራ ያለው ስራም ያንን ለመተግበር የሚያደርገው ዝግጅት አካል ነው ብሏል።

ፓርቲው የአፋር ሽማግሌዎች በአንድነት በመቆም የህዝባቸውን አንድነት እንዲጠብቁ፤ ወጣቶችም ለፍትህ እና እውነት እንዲቆሙ፤ እንዲሁም ሌሎች ኢትዮጵያውያን ከአፋር ወንድሞችና እህቶቻቸው ጎን እንዲሰለፉ ጥሪ አቅርቧል። አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች በክልሉ ውስጥ ግጭቶች እየተካሄዱ ላሉባቸው ቦታዎች ትኩረታቸውን እንዲሰጡ እና አዲስ አበባ የሚገኙ የውጭ አገራት ኤምባሲዎችም ጉዳዩን እንዲመለከቱት ጥሪ አቅርቧል።

© 2008-2009