ዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ የስልጣን ዕድሜውን ለማራዘም እንዲያስችለው ኢትዮጵያውያን ስለ አገዛዝ ሥርአቱ የልማት መንግሥትነት አንድ አይነት አመለካከት እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚያካሄደውን ዘመቻ አጧጡፎ እንደቀጠለበት ከሰሞኑለዝግጅት ክፍላችን የሚደርሱ ዘገባዎች አሳይተዋል።
ዘረኛውና ነፍሰ ገዳዩ መለስ ዜናዊ ከበርካታ አመታት በፊት፣ የሚመራው ፓርቲ አላማ ኢትዮጵያውያን አንድ አይነት አመለካከት ኖሯቸው የአገዛዙን ፈቃድ ከማይቃወሙበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ማድረግ ነው ሲል መናገሩን ከዚህ ቀደም መጥቀሳችን ይታወሳል። በዚህም አኳኋን ወያኔ በህዝባችን መተፋቱን ካወቀበት የምርጫ 97 ወዲህ ላለፉት አምስት አመታት ቁጥሩ በውል የማይታወቅ ከፍተኛ የአገር ሃብትና ገንዘብ በማፍሰስ ህዝቡ አብዮታዊ ዴሞክራሲን እንዲቀበል ዘርፈ ብዙ ዘመቻ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል።
ይህ ዘመቻ ከለፈው ግንቦት 15ቱ የምርጫ ተውኔት በኋላም ቀጥሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ መምህራን የሙያ ስልጠና ይሰጣችኋል ተብለው ተሰብስበው ለአስራ አምስት ቀናት ስለ አብዮታዊ ዴሞክራሲ መሰበካቸውን ባለፈው ሳምንት መዘገባችን ይታወሳል። የግንቦት 7 ድምጽ ሪፖርተር በዚህ ሳምንት ከአዲስ አበባ አጠናቅሮ የላከው ዘገባ ደግሞ፥ ሰሞኑን በሙያ ስልጠና ስም የተሰበሰቡ የመንግስት ኦዲተሮች ተመሳሳይ እጣ እንደገጠማቸው አሳይቷል።
በተጨማሪም፥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች ለየማህበረሰቦቻቸው አገልግሎትን በመስጠት ስም በአገዛዙ እንደተሰበሰቡ የታወቀ ሲሆን፤ እውነተኛው ስራቸው ግን የገዢውን ፓርቲ ፖለቲካ መግፋት እና በአገሪቱ ውስጥ ልማት እንዳለ ህዝቡን ለማሳመን መጣር እንደሆነ ዘገባው ገልጿል። ከወጣቶቹ ውስጥ የገዢው ፓርቲ አባላት የሆኑት ለዚህ አገልግሎታቸው እንደሚከፈላቸውም መረጃው ያስረዳል። ወያኔ ከምርጫ 97 በፊት 700 000ብቻ የነበሩትን አባላቶቹን ቁጥር በግዴታ ምልመላ 5 ሚሊዮን ማድረሱን በተለያዩ አጋጣሚዎች በመመስከር ላይ ይገኛል።