ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ሐምሌ 4 ቀን 2002 ዓ.ም. በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ በደረሰው የአጥፍቶ ጠፊዎች ጥቃት ሕይወታቸውን ላጡ፤ የአካልና የስነልቦና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችንና ቤተሰቦቻቸው የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ይገልፃል። ግንቦት 7 በዚህ ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸውን የኡጋንዳና የሌሎች አገራት ዜጎችም ሃዘን ይጋራል።ንቅናቄዓችን ፓለቲካዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ዓላማን ለማሳካት ሲባል በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚደረግ ጭፍጨፋን አጥብቆ ያወግዛል።
በአገራችን በኢትዮጵያ ከተንሰራፋው ህገ-አልበኝነት እና ዘረኛ አገዛዝ በመሸሽ ሕይታቸውን ለማትረፍ የተሰደዱ ወገኖቻችን የጥቃቱ ዒላማ መሆናቸው ሃዘናችንን እጥፍ ድርብ አድርጎታል። ወያኔ በሶማሊያ ውስጥ ለተከተለው ጀብደኛ ፓሊሲ ምስኪን ኢትዮጵያዊያን ዋጋ መክፈላቸው እጅግ አሳዛኝ ጉዳይ ነው። የወያኔ ጀብደኝነት አገራችንን ከማትወጣበት አጣብቂኝ ውስጥ ሊከታት እንደሚችል በተደጋጋሚ ሲገለጽ የቆየው ምን ያህል እውነት እንደሆነ የሰሞኑ የካምፓላው አሳዛኝ ክስተት ግልጽ አድርጎልናል። ወያኔ ገና ለብዙ ዓመታት የምንዳክርበት የሶማሊያ ማጥ ውስጥ ከቶናል።
ከዓመታት በፊት የአካባቢው አገሮች በሶማሊያ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት እንዲታቀቡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያሳለፈው ውሳኔ በወያኔ ግንባር ቀደም አዝማችነት ከተጣሰ ወዲህ የሶማሊያ ሁኔታ እያደር እየባሰ ለአካባቢው አገሮች በሙሉ ፈተና እየሆነ መጥቷል። ወያኔ በሶማሊያ ጉዳይ አዛዥ ልሁን ባለ መጠን አፀፋው የከፋ እንደሚሆን፤ የሶማሊያ ለዘብተኛ ዜጎች ሳይቀሩ በኢትዮጵያ ላይ ቂም እንዲቋጥሩ መደረጉ በዓይናችን እያየነው ያለ ጉዳይ ነው። ይህ የወያኔ ጀብደኛ ጣልቃ ገብነት የሶማሊያ ችግር ተባብሶ ዓለም ዓቀፍ ገጽታ እንዲኖረው በማድረጉ እነሆ ዛሬ በጎረቤት አገር ጠለላ ሥር የሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሕይወት አደጋ ላይ ሊወድቅ ችሏል። ሶማሊያ የዘመተው የወያኔ ጦር የሶማሊያን የውስጥ ችግር እቤታችን ድረስ ጎትቶ ስላመጣዉ ችግሩ በዚህ የሚቆም አይመስልም። ሰሞኑን የወያኔ ወዳጅ ነኝ ባዩ የሼክ ሸሪፍ አህመድ አገዛዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለግብፅ ጋዜጣ “ኦጋዴን ኢትዮጵያ የቀማችን የሶማሌ ግዛት ነዉ” ብሎ የተናገረውን ላስተዋለ ስጋታችን የበለጠ ይገባዋል ብለን እናምናለን።
የዓለም ዓቀፉ ኅብረተሰብም የወያኔ ዓይነቱ የወንበዴ ቡድን በሌላ አገር ሰላምና መልካም አስተዳደርን ያሰፍናል ብሎ መገመቱ አንድም የዋህነት አሊያም ግድየለሽነት ነው። አገሩን በዘር ከፋፍሎ እያመሰ ያለ ቡድን ቀድሞውኑ በዘር የተከፋፈለን የጎረቤት አገር ሕዝብ አስማምቶ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ይረዳል ማለት ከእባብ እንቁላል እርግብን መጠበቅ ነው።
ግንቦት 7 የሶማሊያ ችግር አሳሳቢ እንደሆነ ይረዳል። በዚያው መጠን ደግሞ ወያኔ ሶማሊያን አስመልክቶ የተከተለውን ፖሊሲ አጥብቆ ይቃወማል። የሶማሊያ ችግር መፍትሄ የሚያገኘው በዋነኛነት በራሳቸው በሶማሊያውያን መሆን ይኖርበታል። ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ውስጥ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት መኖር ለአካባቢው ሁሉ ሰላም መሠረት እንደሆነ አስረግጠን እንናገራለን።
ኢትዮጵያን ለማዳን መረባረብ በአስከፊ ሁኔታ እየተበጠበጠ ላለው የአፍሪቃ ቀንድ ሰላም ዘላቂ መፍትሄ አስተማማኙ መንገድ ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያዉያን የተሸከምነው ኃላፊነት ክብደቱ ሊሰማን ይገባል እንላለን።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!