ዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ በአራጣ አበዳሪዎች ላይ እያካሄደ ያለው ፍርድ እንደ ወትሮው የአገዛዙ አሰራር በአድሎ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰ ዘገባ አስረድቷል።
የግንቦት 7 ድምጽ ዘጋቢ ከአዲስ አበባ አጠናቅሮ በላከው ዘገባ መሰረት ሰሞኑን አቶ አየለ ደበላ የተባሉ ሰው በአራጣ አበዳሪነት ተከሰው የ22 አመት እስራት እና 12 ሚሊዮን ብር ተፈርዶባቸዋል።
እንደ ዘጋቢያችን ገለፃ በብዙ ቀበሌዎች በርካታ የወያኔ ካድሬዎች አራጣ አበዳሪነትን እንደ ንግድ የሚያካሄዱ ሲሆን፤ አንዳንድ ነጋዴዎች በዚህ ምክንያት እየታሰሩ መሆኑን ካወቁ በኋላ እንኳ ንግዳቸውን አላቆሙም። ይሁን እንጂ ምንም ህጋዊ እርምጃ አልተወሰደባቸውም።
የኢትዮጵያ ህግ አስከባሪ ተቋማት በሙሉ እንደሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ሁሉ በወያኔ ሙሉ ቁጥጥር ስር ያሉ ሲሆን፣ አገዛዙም የራሱን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማስከበር እንደሚጠቀምባቸው ይታወቃል። ከዚህ ቀደም ግብር አልከፈሉም በሚል የታሰሩ ታዋቂ ነጋዴ በዘረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊ ባለቤት አዜብ መስፍን የንግድ ሽርክና ጥያቄ ቀርቦላቸው እምቢ ያሉ እንደሆኑ መዘገባችን ይታወሳል።
በተጨማሪም፥ ንብረትነቱ የወያኔ የሆነውን ኤፈርት ኩባንያ የሚቀናቀኑ ኩባንያዎች ባለቤቶች በተለያዩ ምክንያቶች እየታሰሩ ከንግድ ሜዳው እንዲወጡ እንደሚደረጉ በሰፊው ይነገራል።