ዘረኛውና አምባገነናዊው አገዛዝ በህዝብ ፊት እራሱን እንደ ልማት መንግስት አድርጎ ለመሳል የሚያደርገውን ጥረት አጧጡፎታል ተባለ

የዴሞክራሲያዊ መብት አስከባሪነት ጭንብሉ ሙሉ በሙሉ እንደወደቀበት የተረዳው ዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ፣ እራሱን እንደ ልማት መንግስት ለመቅረጽ የሚያደርገውን ጥረት ማጣጧፉን ከሰሞኑ የሚደርሱን ዘገባዎች አሳይተዋል።

አገዛዙ የኢትዮጵያውያንን አመለካከት እንደ መለስ ዜናዊ ፍላጎት ለመቅረጽ እና ህዝቡ ሁሉ አንድ አይነት አለመካከት ኖሮት አብዮታዊ ዴሞክራሲን እንዲቀበል ለማድረግ የሚያካሄደውን ዘመቻ አጠናክሮ እንደቀጠለ ሐሙስ እለት መዘገባችን ይታወሳል። ከዛ ጎን ለጎን ለዝግጅት ክፍላችን የሚደርሱት ዘገባዎች እንዳሳዩት፥ ወያኔ ወጣቶች እና የመንግስት ሰራተኞች ማህበረሰቦቻቸውን ልማት እንዳለ እንዲያሳምኑ ሲጎተጎት ቆይቷል።

የግንቦት 7 ድምጽ ሪፖርተር ከአዲስ አበባ አጠናቅሮ በላከው ዘገባ፣ እሁድ እለት በመዲናይቱ ለስብሰባ የተጠሩ በርካታ የገዢው ፓርቲ አባላትና ካድሬዎችም ወደየማህበረሰቦቻቸው ሄደው በወያኔ አገዛዝ ስር እድገት እንዳለ ህዝቡን እንዲያሳምኑ ትእዛዝ ተቀብለዋል።

ዘረኛውና አምባገነናዊው ወያኔ ዴሞክራሲ እና የብሔረሰቦችን መብት ማስከበር የሚሉትን ጭንብሎች አጥልቆ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ፤ በተለይም ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ በዚህ ረገድ እውነተኛ ማንነቱ ከተጋለጠ በኋላ እራሱን እንደ ልማት መንግስት ለመሳል የሚያደርገውን ጥረት ማጧጧፉ ይታወቃል። በግንቦት 15፣ 2002ቱ የምርጫ ተውኔት ደግሞ የፓርላማ መቀመጫውን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር በበርካታ ተመልካቾች ዘንድ የአንድ ፓርቲ ስርአትን በአገሪቱ ማስፈኑ ሲነገር፤ የልማት ፕሮፓጋንዳ ዘመቻውን አፋፍሞታል።

ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነት እና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ሐምሌ 8 ቀን ባወጣው ርእሰ አንቀጽ፥ “የወያኔ ባለስልጣኖችና ዘመዶቻቸው መክበርና የፎቆቻቸው መብዛት የኢትዮጵያን እድገት አያመለክትም።” ያለ ሲሆን፥ በአገሪቱ ውስጥ የተረጋገጠ ልማት ቢኖር እንኳ፥ ልማት ማምጣት ሕዝብን የመግዛት መብት እንደማይሰጥ እና ይህንንም የቅኝ ገዢዎች አስተሳሰብ ንቅናቄው አጥብቆ እንደሚዋጋ ገልጿል።

© 2008-2009