በጂጂጋ ከተማ አንድ ወጣት ዜጋ በወያኔ ጦር ተገድሎ መንገድ ላይ መጣሉ ተዘገበ

ሐምሌ 14፣ 2002 ቀን በጂጂጋ ከተማ አንድ ወጣት ልጅ በአካባቢው በሚገኘው የወያኔ ጦር ተገድሎ በከተማው በሚገኝ እስር ቤት ፊት ለፊት መጣሉን ኦጋዴን ኦንላይን የተባለው ድረ-ገጽ ዘግቧል።

ሃሰን የሱፍ አሊ የተባለው ወጣት ከሶስት አመታት በፊት ደገሃቡር ከሚገኝ ቡድህሌ የተባለ መንደር ተወስዶ እስር ቤት እንደቆየ ድረ-ገጹ የገለጸ ሲሆን፤ ከመገደሉ በፊት በወያኔ ጦር ሰፈር መታየቱንም አስታውቋል። ወጣቱ የተገደለው ታንቆ እንደሆነ የሚያሳይ ምልክት ከአስከሬኑ ጋር መታየቱንም ኦጋዴን ኦንላይን ጠቅሷል። የአካባቢው ሰዎች አስከሬኑን እንዳይቀብሩ መከልከላቸውን እና ይህም በርካቶችን ማስቆጣቱን ድረ-ገጹ አክሎ ገልጿል።

የዚህን ዜና ጥቆማ ለዝግጅት ክፍላችን ያደረሱ ስማቸው እንዳይጠቀስ የሚሹ ኢትዮጵያዊ፣ ይህ ሁኔታ የደርግን ዘመን እንዳስታወሳቸው ተናግረዋል። የቀድሞው ወታደራዊ አገዛዝ አብዮት ጠባቂዎች፥ ጸረ አብዮት የሚሏቸውን ኢትዮጵያውያን እየገደሉ በየመንገዱ እንደሚጥሉ እና ሰዎች እንዳይቀብሯቸው እንደሚከለክሉ ይታወሳል።

የዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ ጦር የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባርን (ኦብነግ) በመዋጋት ስም በሶማሌ ክልል ንጹሃን ዜጎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ረገጣን እንደሚፈጽም ይታወቃል። ከሶስት አመታት በፊት ኦብነግን በመዋጋት ስም ወደ ክልሉ የገባው ጦር የጦር ወንጀል መፈጸሙን ሂውማን ራይትስ ዋች የተባለው የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ቡድን መግለጹ ይታወሳል።

© 2008-2009