ፓትሪያርክ አቡነ ጳውሎስ ከውጭ አገራት ቤተክርስቲያናት ጋር በሚያደርጉት ድርድር የወያኔን ፈቃድ የማስፈጸም ተልእኮ ይዘው እንደተነሱ ታወቀ

የወያኔ አገዛዝ የውጭ አገር ቤተክርስቲያናትን በቁጥጥሩ ስር ለማዋል የያዘውን እቅድ ለማስፈጸም ፓትሪያርክ አቡነ ጳውሎስ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ለቤተክርስቲያኒቱ አመራር ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለግንቦት 7 ድምጽ ሬድዮ በላኩት መረጃ አስረድተዋል።

ከአገዛዙ ጋር ጥብቅ የሆነ የጥቅምና የመንደር ልጅነት ትስስር እንዳላቸው የሚታወቀው አቡነ ጳውሎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ሆነው ከተሰየሙ በኋላ በውጭ አገራት ያሉ አድባራት ከአገር ቤቱ ሲኖዶስ መለየታቸው እና በተሰደዱት አቡነ መርቆርዮስ አመራር ስር መቅረታቸው ይታወቃል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህን ክፍፍል ለማስወገድ እና ቤተከርስቲያኒቱን እንደገና አንድ ለማድረግ ድርድር ተጀምሯል።

በውጭ አገራት እና በአገር ቤቱ ሲኖዶስ ውስጥ ያሉት አንዳንድ አባቶች ይህንን ድርድር የሚያካሄዱት በሙሉ ልብ እርቅን በመሻት ቢሆንም፤ ፓትሪያርክ አቡነ ጳውሎስ ግን አጋጣሚውን በመጠቀም የወያኔን ተልኮ ለማስፈጸም እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናቸው የሚል መረጃ ለዝግጅት ክፍላችን ደርሷል። በዚህም መሰረት ለድርድሩ ከሚመጡት አባቶች ውስጥ አቡነ አትናጢዮስ እና አቡነ ገሪማ በድብቅ የፓርቲያርኩ ተልኮ አስፈፃሚዎች ናቸው ሲሉ የቤተክርስቲያኒቱ ምንጮች ለዝግጅት ክፍላችን በላኩት መረጃ አስታውቀዋል።

ምንጮቻችን መረጃው እንዲታወቅ የፈለጉበት ምክንያት የውጭ አገራቱ አባቶች እንዲጠነቀቁና በተዘጋጀላቸው ወጥመድ ውስጥ እንዳይወድቁ ለማሳወቅ ነው ብለዋል።

ደጀሰላም የተባለው ድረ-ገጽ ድርድሩን በሚመለከት ባለፈው ሳምንት ባወጣው ዘገባ በሲኖዶሱ ተመርጠው ከአዲስ አበባ እንደሚመጡ ከዘረዘራቸው አባቶች ውስጥ አቡነ አትናጢዮስ ያሉበት ሲሆን፤ አቡነ ገሪማ ግን አልተጠቀሱም።

የወያኔ አገዛዝ በውጭ አገራት ሆነው የእግር እሳት የሆኑበትን ኢትዮጵያውያን ለማዳከም በሚል በኢትዮጵያ እንዳደረገው በውጭ አገራትም ቤተእምነቶችን ከቁጥጥሩ ስር ለማዋል እንደሚፈልግ ለማወቅ ተችሏል። የአባ ጳውሎስ እንቅስቃሴም የዚህ እቅድ አካል እንደሆነ ምንጮቻችን ጠቁመዋል።

© 2008-2009