ገዢው ፓርቲ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ ባካሄደው ግምገማ ከውስጥ ሆነው ስራዬን አበላሽተውብኛል ያላቸውን ካድሬዎቹን ከፓርቲ ማባረሩን አዲስ ነገር ኦንላይን የተባለው ድረ-ገጽ ዘግቧል።
የወያኔ የአዲስ አበባ ቢሮ ሃላፊ በሆነው ሬድዋን ሁሴን በተመራው በዚህ ግምገማ ላይ፥ በሚቀጥለው ምርጫ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በግንቦት 15ቱ የምርጫ ተውኔት ካገኙት ያነሰ ድምጽ በሚያገኙበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደርጓል። ግንቦት 15 ቀን ተቃዋሚዎች በአዲስ አበባ ከሁለት መቶ ሺህ በላይ ድምጽ ማግኘታቸው በአጽንዎት መዳሰሱን ድረ-ገጹ ዘግቧል።
የግምገማው አላማ ወያኔ ከውስጥ ሆነው ስራዬን አበላሽተውብኛል፤ እንዲሁም አድርባዮች ናቸው የሚላቸውን ለይቶ ለማባረር እንደሆነ ዘገባው ያሳየ ሲሆን፤ በዚህም መሰረት ውስጥ ለውስጥ ተቧድነዋል፣ የጥቅም መረብ መስርተዋል ተብለው የተወነጀሉት መባረራቸውን ገልጿል።
የወያኔ አገዛዝ በተለይም ባለፉት አምስት አመታት ድጋፍ ለማግኘት ሲል ሙስና በከፍተኛ ደረጃ እንዲስፋፋ እንደፈቀደ እና በርካታ አድርባዮችን በማዝመት በህዝቡ ላይ ከፍተኛ አፈናን ሲያካሄድ መቆየቱ ይታወቃል። ጉዳዩን በሚመለከት አስተያየታቸውን የለገሱን ግለሰብ፥ “እራሱ እንዲስፋፋ በፈቀደው አድርባይነት አሳቦ እነዚህን ሰዎች መልሶ ማባረሩ በግንቦት 15ቱ ምርጫ ተብዬ የፈለገውን ውጤት ካገኘ በኋላ ሸክም ለማውረድ ነው” ካሉ በኋላ፣ ሁኔታው “አብዮት ልጆቿን ትበላለች” የሚለውን አባባል እንዳስታወሳቸው ገልጸዋል።