የአፋር ህዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አሎ አላዳይስ ከግንቦት 7 ድምጽ ራድዮ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የወያኔ አገዛዝ በፌዴሬሽን ስም የሚነግድ እንጂ እውነት ፌዴሬሽን እንዲሰራ የሚፈልግ አይደለም ብለዋል።
አቶ አሎ እሁድ እለት ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ቃለ መጠይቅ፥ የአፋር ክልል የራሱ የሆነ መንግስት አለው ማለት የማይቻልበት ሁኔታ እንዳለ ገልጸዋል። ተሰሚነት ያላቸው ታዋቂ ግለሰቦች እና ምሁራን ከፖለቲካ ምህዳሩ ተገለው፤ የወያኔ ተላላኪ የሆኑ ካድሬዎች ክልሉን እያመሱት ነው ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት በአፋር ያለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከህዝቡ ተቀምቶ ከወያኔ ጋር ትስስር ወዳላቸው ኢንቬስተሮች ተዛውሯል የሚሉት አቶ አሎ፣ ህዝቡ ከለም መሬቱ እየተፈናቀለ ወደ በረሃ እየተገፋ ነው ብለዋል። ከዚህ ቀደም በእርሻ እና በጨው አምራችነት ይተዳደሩ የነበሩ የአፋር ማህበረሰቦች መሬታቸውን መቀማታቸው፤ ከጦርነት የተነሳ የተስተጓጎለው ንግድ እና ከድርቅ የተነሳ የተዳከመው የእንስሳት እርባታ ተደማምረው ህዝቡን ለረሃብና እንግልት መዳረጋቸው ታውቋል። ይህንን ሁኔታ በሚመለከት ጥያቄ የሚያነሱ ዜጎችም ከነጎሳቸው እንደጠላት እንደሚፈረጁ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል።
አቶ አሎ ጨምረውም፥ የኢትዮጵያ መንግስት በአንድ ብሔረሰብ ቁጥጥር ስር ነው ያሉ ሲሆን፤ በፌዴሬሽን ሊኖር የሚገባው የስልጣን ክፍፍል በአገሪቱ ውስጥ እንደሌለ እና ወያኔ በአፋር ክልል ህዝቡ እራሱን እንዲመራ ሊፈቅድ ይቅርና የህዝቡን ማንነት ለመለወጥ ጥረት እያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።