እንደ ወያኔ ያሉ አፋኝ አገዛዞች የህዝብ ገንዘብ በመጠቀም በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ተጽእኖ እያደረጉ ነው ተባለ

ኒውስዊክ የተባለው ታዋቂ የአሜሪካ ጋዜጣ ሰሞኑን ባወጣው ጽሁፍ እንደ ወያኔ ያሉ አፋኝ አገዛዞች ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ በማፍሰስ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ተጽእኖ እያደረጉ ነው ብሏል።

የተለያዩ አምባገነናዊ አገዛዞች በአሜሪካን አገር የሚገኙ የሎቢ ድርጅቶችን በከፍተኛ ገንዘብ በመቅጠር የአሜሪካ ህግ አውጪ አካል እና አስተዳደር እነሱን በሚመለከት ጠንካራ አቋሞች እንዳይወስዱ ሲያመክኑ ቆይተዋል ብሏል ጋዜጣው በድረ-ገጹ ባወጣው ትንታኔ። እነዚህ አገዛዞች ከፍተኛ መጠን ያለው የህዝብ ገንዘብ እየተጠቀሙ የሚሟገቱላቸው ድርጅቶች ሲቀጥሩ፤ በየአገሮቻቸው እነሱን የሚቃወሙት ድምጾች ግን ያንን የሚቋቋም ጉልበት ለማሰባሰብ አይችሉም። የዚህ ውጤትም የወንበዴዎች በዋሽንግተን ሰሚ ማግኘት እና የተቃዋሚዎቻቸው ድምጽ መታፈን ሆኗል ሲል ኒውስዊክ ገልጿል።

ጋዜጣው፥ በዚህ ትንታኔው የወያኔ አገዛዝ ቅጥረኛ የሆነውን ዲ.ኤል.ኤ. ፓይፐር የተባለ ድርጅት ጠቅሷል። አብዛኛው ህዝቧ በድህነት የሚማቅቀውን ኢትዮጵያን በጉልበት ተቆጣጥሮ ያለው ወያኔ ዲ.ኤል.ኤ. ፓይፐር በአሜሪካ ዋና ከተማ ዋሽንግተን ዲሲ ሆኖ እንዲሟገትለት በሃምሳ ሺህ ዶላር ወርሃዊ ክፍያ እንደቀጠረው ይታወቃል። በእንግሊዝ አገር በሚገኘው ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ይፋ የተደረገ የድህነት መመዘኛ፤ በኢትዮጵያ ከመቶ ሰዎች ዘጠናዎቹ ድሆች ናቸው ማለቱን መዘገባችን ይታወሳል።

© 2008-2009