አዲስ አበባን ጨምሮ በበርካታ የአገሪቱ ክፍላት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና የንግድ ድርጅቶቻቸው በኤሌክትሪክ ሃይል እጦት ምክንያት እየተንገላቱ ባሉበት ወቅት የወያኔ አገዛዝ የኤሌክትሪክ ሃይል ለጎረቤት አገሮች ለመሸጥ ዝግጅቶች አጠናቅቄያለሁ ማለቱ ተዘግቧል።
አፍሪካን ፕሬስ ኤጀንሲ የተባለ የዜና አውታር ማከሰኞ እለት ባወጣው ዘገባ፣ እንደታቀደው ከሄደ ለሱዳን፣ ለኬንያ እና ለጅቡቲ የሚደረገው የኤሌክትሪክ ሃይል ሽያጭ በሚቀጥለው የፈረንጆች አመት ይጀምራል። ያንን ለማድረግ የሚያስችለው የኤሌክትሪክ መስመር ግንባታ መፈጸሙን አገዛዙን ጠቅሶ ዘግቧል።
በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አንዳንድ ጊዜ በየቀኑ ለሰዓታት የሚቋረጠው የኤሌክትሪክ ሃይል የንግድ ስራዎችን እያስተጓጎለ እና ዜጎችን ለእንግልት እየዳረገ መቆየቱን በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል። በአገር ቤት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል እጥረት እያለ አገዛዙ ለውጭ አገራት ለመሸጥ የተነሳበትን ምክንያት አስመልክቶ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የጋበዝናቸው ግለሰብ፥ ምናልባት አገዛዙ አገር ውስጥ ላለው ህዝብ አገልግሎቱን በማቅረብ ከሚያገኘው ገንዘብ ይልቅ ለውጭ አገራት በመሸጥ ሊያገኝ የሚችለውን የውጭ ምንዛሬ በማሰብ እንደሆነ ግምታቸውን ገልጸዋል።
ግለሰቡ ጨምረውም፥ “ምንም እንኳ ይህ ከላዩ ሲታይ የበለጠ ትርፍ ለማግኘት የሚፈልግ ማንኛውም አካል የሚያደርገው ነገር ቢመስልም የአንድ አገር መንግስት ነኝ ከሚል አካል ግን የማይጠበቅና ሃላፊነት የጎደለው፤ ቀድሞውኑ ቀጫጫ የነበረውን የአገሪቱን ኢንዱስትሪ የሚያመነምን እና የሚያጠፋ ነው” ብለዋል። “ይህ ድርጊት አገዛዙ እንደሚለው ከተሳካ፣ ወያኔ በአገሪቷ ላይ የሚያካሄደው ዘረፋ አካል ተደርጎ መታየት አለበት፤ ለአገዛዙ በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንዘብ የማሰባሰብ እንጂ ኢትዮጵያን የመጥቀም አላማ ይዞ የተነሳ አይደለም” ብለዋል።