ትምህርት የእውቀት አድማስን ካላሰፋ፤ አዳዲስ ክህሎቶችን ካላሳወቀ፤ የእለት ከእለት ኑሮን ካላሻሻለ እና አዎንታዊ የባህርይ ለውጥ ካላመጣ ፋይዳው እምን ላይ ነው?
የወያኔ የትምህርት ሥርዓት ከላይ ከዘረዘርናቸው ውስጥ ለአንዱም የተዘጋጀ አይደለም። ወያኔ ትምህርት ቤቶችንና ዩኒቨርስቲዎችን ከእውቀትን መገበያያነት ይልቅ እጅግ ኋላቀር የሆነ ዘረኛና ጎጠኛ አስተሳሰብ ማራቢያና ማሰራጫ ተቋማት አድርጎዓቸዋል። ዛሬ በወያኔ መዳፍ ውስጥ ባለችው ኢትዮጵያ ውስጥ ተማሪዎች ዘራቸው መታወቂያቸው እንዲሆን ተደርጓል። እንደድሮ ከሰሜኑም ከደቡብም፣ ከምሥራቅም ከምዕራብም የመጡ ወጣቶች የተደባለቁባቸው የጥናትም ሆነ የጨዋታ ቡድኖች በዛሬዎቹ ዩኒቨርስቲዎች ማግኘት አይቻልም። እያንዳንዱ ተማሪ ከጎጡ ልጅ ጋር ብቻ እንዲቧደን፤ ከሌላ አካባቢ የመጣውን የክፍል ባልደረባውን በጥርጣሬ፣ ከዚያም አልፎ በጠላትነት እንዲመለከት ተደርጓል። ከዚህ ሁሉ በላይ አሳሳቢ የሆነው ጉዳይ ደግሞ ወያኔ ከትግራይ ክልል የመጡ ተማሪዎችን ከሌሎች ወንድሞቻቸው ለመነጠል የሚሠራው የተቀናጀ ሥራ ነው። እነዚህ ወጣቶች በሌሎች የክፍል ባልደረቦቻቸው ላይ የበላይነትና የሁሉ-አውቅነት ስሜት እንዲኖራቸው የሚያበረታቱ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል። ይህ በሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በግልጽ የሚታይ ጉዳይ ሆኗል። በየካምፓሱ የተቋቋሙት “የትግራይ ተማሪዎች ማኅበራት” ሥራቸው ይህንን ማስፈጸም ነው። አንድ የትግራይ ወጣት በግል ይህንን ቢቃወም “ብሄራዊ” ግዴታውን እንዳልተወጣ ከሃዲ እንዲታይ ይደረጋል። በአንፃሩ ደግሞ የሌሎች ክልሎች ተማሪዎች የታዘዙትን በፈጸሙ መጠን ጉርሻ እየተሰጣቸው ለታማኝ ሎሌነት ይዘጋጃሉ። ለእነሱም የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የሶማሌ፣ … ወዘተ ማኅበራት ተቋቁመውላቸዋል። የዛሬዎቹ ዩኒቨርስቲዎቻችን ጥቂቶች ገዢነትን፤ ብዙዎች ደግሞ ባርነትን የሚለማመዱባቸው የአገዛዝ ማሰልጠኛ ቦታዎች ሆነዋል።
ከክህሎት አኳያም ቢሆን ወጣቶቻችን የሚማሩት ውሸትን፣ ጉራንና ትዕቢትን ሆኗል። ኑሮን ለማሸነፍ አንድም ከምርጥ ዘር መወለድ አሊያም ለምርጥ ዘር ማደግደግ መቻል እንጂ በትምህርት መጎበዝ ፋይዳ እንደሌለው እዚያው ዩኒቨርስቲ ግቢ ውስጥ የሚያዩት ሃቅ ሆኗል።
አሁን በሥራ ላይ ያለው የትምህርት ሥርዓት ኢትዮጵያን የሚጠሉ፤ በንዋይና ሥልጣን ፍቅር የታወሩ፤ ኢትዮጵያንም በወረራ እንደያዟት አገር በጥላቻ የሚገዙ ወያኔዎች የገነቡት ነው። ይህ ሥርዓት የፈጠራቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም እነዚሁ ሰዎች የሚዘውሯቸው ወፍጮዎች ናቸው። በተለይ አዳዲሶቹ ዩኒቨርስቲዎች ከትምህርት ጋር ፈጽሞ የሚተዋወቁ አይመስልም። ዩኒቨርስቲዎቹ ዘረኝነትን ለማስፋፋት ተብለው የተቋቋሙ ተቋማት ናቸው።
ለዚህም ነው ዛሬ ዛሬ በተማሪዎች መካከል በምንም ጉዳይ ግጭት ቢነሳ ወዲያውኑ በዘር ወደተቧደኑ ቡድኖች ጠብ የሚያመራው። ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ “እከሌ እና እከሌ ተጣሉ” ማለት ተረስቷል። “ትግሬና ኦሮሞ ወይም ትግሬና አማራ ተጣሉ” ነው የሚባለው። ጅማ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ለተሰነዘረ ቡጢ መቀሌ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ምላሽ ይሰጣል፤ ለሱ ደግሞ ሃረማያ ውስጥ አፀፋ ይከተላል። ወዲያውኑ የሃዋሳ፣ የወላይታ፣ የሰመራ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎች የጠቡ አካል ይሆናሉ ። አንድ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የተነሳ ጠብ በአንድ ቀን አገሪቷን ያዳርሳል። የዘመነ ወያኔ የተማሪዎች ጠብ ዘር እንጂ ፊት አይለይም። ይህ አገራችን ወደየት እየሄደች እንደሆነ የሚያሳይ ሁነኛ አመላካች ነው። ዛሬ በዚህ ጉዳይ ላይ እርምጃ ካልወሰድን ነገ ሊረፍድ ይችላል።
ደግሞስ ይኸ ሁሉ መከራ ለየትኛው ትምህርት ነው? የትምህርት ጥራት እጅግ ከመውደቁ የተነሳ “ጭራሹን ትምህርቱ ባይሰጥ ይሻል ነበር?” እሚያስብል ደረጃ ላይ ደርሷል። ወያኔ “ትምህርትን አስፋፋሁ!” ለሚለው ጉራው እና በዚህም ምክንያት ለሚገኘው የእርዳታ እርጥባን ሲል ብዛት ላይ ብቻ ያተኮረ በመሆኑ የትምህርት ጥራትን ጉዳይ ፈጽሞ ቸል ብሎታል። ለወያኔ የጥራት ጉዳይ ደንታው አይደለም። በዚህም ምክንያት “ወጣቶቻችን ምን ተምረው እየወጡ ነው?” የሚለው ጉዳይ በእጅጉ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።
በዘረኛ የትምህርት ሥርዓት አማካይነት በአገራች ወጣት ላይ እየደረሰ ያለው በደል ጠልቆ እንዲሰማን ሁለት ተጨማሪ ነጥቦችን ማንሳት ያስፈልጋል።
አንደኛ፣ የወያኔ ቱባ ባለሥልጣናት ልጆች በምርጥ የግልና የውጭ አገራት ተቋማት ተቀማጥለው የሚማሩ መሆናቸው ነው። ይህ ተግባር ወያኔዎች የገነቡት የትምህርት ሥርዓት ለራሳቸው ልጆች የማይመርጡት መሆኑን ያረጋግጥልናል። በሌላ በኩል ደግሞ በወያኔ እምነት ልጆቻቸው የነሱ ሥልጣን ተረካቢዎች ናቸውና እየተፈጠረልን ያለው አዲስ የገዥ መደብ ምን ያህል ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሃቅ የተነጠለ፤ እንዲያውም ከሌላ ፕላኔት የመጣ የሚመስል እንደሆነ ልብ ይሏል።
ሁለተኛ፣ በክልሎች መካከል ልዮነትን የሚያሰፋ የትምህርት ሥርዓት ያለን መሆኑ ነው። ለምሳሌ የሶስተኛ ሳይክል ትምህርት በትግራይና በሌሎች ክልሎች አንድ አይነት አይደለም። ሂሳብና እንግሊዝኛ ቋንቋ በመጠቀማቸው መጠንም በእጅጉ ይለያያሉ። በዚህም ምክንያት ከተለያዩ ክልሎች የሚመጡ ተማሪዎች ዩኒቨርስቲ ወይም ኮሌጅ ውስጥ ሲገናኙ በተመጣጣኝ ደረጃ ላይ አይደሉም። ይህ ከዘረኝነትም በላይ ነው።
ይህ መርዛማ የሆነ የትምህርት ፓሊሲ ምንጩ የወያኔ ባህርይ ነው። ስለሆነም ወያኔ በሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ እየባሰ ይሄድ እንደሆነ እንጂ ሊሻሻል አይችልም።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ወያኔ እየተገበረው ያለው ዘረኛ የትምህርት ፓሊሲ የሚያመጣውን ዘላቂ ጉዳት በጥልቀት ይረዳል። ይህ የትምህርት ፓሊሲ እስካሁን ያደረሰዉን ጥፋት ለማስወገድ እጅግ ብርቱ ፈተና እንደሚጠብቀንም ያውቃል። ከዚህም በላይ በሥራ ላይ እንዲውል ከፈቀድን ደግሞ ፈጽሞ የማይጠገን ጉዳት ሊያመጣብን ይችላል። ስለሆነም አቋራጩ መፍትሄ ወያኔን አስወግዶ በምትኩ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በእኩል የሚያስተናግድ፤ ሁሉንም የሚጠቅም፤ እውቀትን፣ ክህሎቶችንና መልካም ባህሪያትን የሚያጎናጽፍ የትምህርት ሥርዓት መዘርጋት ነው። ዘረኛ የትምህርት ሥርዓትን ለማስወገድ ዘረኛውን አገዛዝ ከሥልጣን ማባረር ግድ ነው!!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!